ʺቤተሰቦቼን በበረሃ ዋሻ ውስጥ ጥዬ ነው የመጣሁት” ከዳህና ደብረ ማርቆስ ለመማር የመጣችው ተማሪ ጥቅምት 19/2014 ዓ.ም (አሻራ ሚዲያ) የሞቀ ቤታቸው የጎደለባቸው፣ ሳቅና ጨዋታ የናፈቃ…

ʺቤተሰቦቼን በበረሃ ዋሻ ውስጥ ጥዬ ነው የመጣሁት” ከዳህና ደብረ ማርቆስ ለመማር የመጣችው ተማሪ ጥቅምት 19/2014 ዓ.ም (አሻራ ሚዲያ) የሞቀ ቤታቸው የጎደለባቸው፣ ሳቅና ጨዋታ የናፈቃቸው እልፎች ናቸው፤ ዓይናቸው እንባ እያፈሰሰ፣ ልባቸው በሐዘን እየተላወሰ የሚኖሩትም እልፍ ናቸው፡፡ ብዙዎች ተፈናቅለዋል፤ ብዙዎች ህይወታቸው አልፏል፤ ብዙዎች በረሃብ አለንጋ ተገርፈዋል፤ ከሞቀ ቤታቸው፣ ከሞላ ንብረታቸው ወጥተው የሰው እጅ እያዩ እንዲያድሩ ተገደዋል፡፡ ሌሎችም የት እንደገቡ ሳይታወቁ ቀርተዋል፤ ግፍና ጭካኔን ለመራቅ ዋሻ ውስጥ ልጆቻቸውን ሰብስበው፣ ዛሬ ይገድሉብን ነገ እያሉ በርካታ የጭንቅ ሌሊቶችን አሳልፈዋል፡፡ ሕጻናት በአሳደጋቸው ቀዬ፣ በኖሩበት መንደር እንዳይቦርቁ ተከልክለዋል ፤ እንቦሶች አይቦርቁም፤ ላሞች እንዳሻ መስክ አይሰማሩም፡፡ በሜ…ዳው መቦረቅ የለመዱት ልጆች፣ ከከብቶቻቸው ኋላ ኋላ እየተከተሉ፣ ዋሽንታቸውን እያንቆረቆሩ የሚያዜሙት እረኞች፣ እንጨት ለቀማ ውኃ ለመቅዳት የሚወርዱ ልጃገረዶች፣ ከንፈር ወዳጆች ከቀያቸው ርቀው፣ በዋሻ ውስጥ ተደብቀው ከክፉዎች እጅ ለመዳን ቀናትን እየቆጠሩ ነው፡፡ አዝመራ በሚሰበሰብበት፣ ልጆች ወደ ዕውቀት ገበያ በሚያቀኑበት፣ እሸት በሚቀመስበት፣ ማር በሚቆረጥበት፣ ወተትና ቅቤ በሚሞላበት፣ በሬዎች በሚያገሱበት በዚህ ወቅት ከእሸቱ ከወተቱ ርቀው የሚኖሩት ብዙዎች ናቸው፡፡ ወርቅ ጌጡ ትባላለች፡፡ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዳህና ተወልዳ፤ ከብቶች አግዳ፣ ፍየሎች ጠብቃ ነው ያደገችው፤ ከዚህ ሥራዋ ጎን ለጎን ወደ ትምህርት ቤት እየዘለቀች 11ኛ ክፍል ደርሳለች፤ ጎበዝ ተማሪ ናት፡፡ ወርቅ አባቷ ሞተውባት እናትም አባትም ሆነው እያሳደጓት የሚገኙት እናቷ ናቸው፡፡ አባቷን ካጣቻቸው ረጅም ጊዜ አልሆነም፡፡ ሐዘኑ አለቀቃትም፣ መከታዋን፣ አለኝታዋን፣ አሳዳጊዋን መኩሪያዋ አባቷን አጥታለችና ልቧን ሐዘን ጎድቶታል፡፡ ያም ይሁን ከመጽናት ውጭ አማራጭ የለምና አዲሱ ዓመት ሲመጣ፣ መስከረም ሲጠባ ትምህርቷን ልትቀጥል፣ ከክፍል ጓደኞቿ ጋር ልትገናኝ ጓጉታለች፣ ተምራ እናቷን ልታሳልፍላቸው፣ ለዘመዶቿ መኩሪያ ልትሆናቸው ቸኩላለች፡፡ በመካከል ግን ያልጠበቀችው ነገር ተከሰተ፡፡ ከትግራይ የተነሳው ወራሪና አሸባሪው የትህነግ ቡድን አካባቢያቸውን ያዘው፤ ወርቅና ቤተሰቦቿ ነብሳቸውን ሊያተርፉ ወደ በረሃ ወረዱ፡፡ በዚያውም ሰነበቱ፤ በዋሻ ውስጥ ተጠልለው አንጀታቸውን አስረው መኖር ጀመሩ፡፡ መማር የሚለው ቀርቶ መኖር የሚለው ተተካበት፡፡ ከመማር መኖር ይቀድማልና ነብሷን ታድን ዘንድ በዋሻ ውስጥ ተጠለለች፡፡ በአካባቢው የገባው ጠላት ተቋማትን አውድሟል፤ ዘርፏል፤ መማሪያ ትምህርት ቤቶቻቸው ፈራርሰዋል፤ ተዘርፈዋል፡፡ የትምህርት ጊዜውም ደረሰ፤ ወርቅ ትምህርቷ እንዲቋረጥ አልፈገችም፤ ቀን እስኪወጣ ድረስ ዝምታን መረጠች፤ አንዲት ብርቱ ጓደኛ አለቻት፡፡ ሀገር እንዴት እንደዋለ፣ ምንስ ተባለ የሚለውን የምታቀብላት፡፡ የጭንቅ ቀን አናጋሪዋ፣ ወሬ ነጋሪዋ ራዲዮኗ፡፡ ራዲዮኗ ከአጠገቧ ነበረች፤ የቀኑን ሁሉ እየነገረች፣ የሆነውን እያስደመጠች የምታጽናናት፡፡ አንድ ቀን ሊኮሰምን የደረሰውን የወርቅን ተስፋ የሚያለመልም ቃል ኪዳን በዚያች የክፉ ቀን አነጋጋሪዋ፣ መረጃ ሰጭዋ፣ ራዲዮ ሾልካ ከጀሮዋ ደረሰች፡፡ ልቧ በሀሴት ሲሞላ ተሰማት፡፡ ደስም አላት፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ዞን በሽብርተኛው ትህነግ ወረራ የተፈናቀሉ ተማሪዎችን ለማስተማር ቃል መግባቱን ነበር የሰማችው፡፡ ወርቅ ሕልሟ እውን ወደ ሚሆንበት፣ ተስፋዋ ከፍ ወደሚልበት አካባቢ ትሄድ ዘንድ አሰበች፡፡ ግን ደግሞ ከባድ ነው በበረሃ ያሉት ቤተሰቦቿ ጉዳይስ? ከሐሳቧ ጋር ተሟገተች፡፡ መሄድ የሚለው ሐሳቧ አሸነፈ፡፡ ወርቅም አደረገችው፣ እናቷንና ሌሎች ዘመዶቿን በበረሃ ጥላ ተምራ ልትደርስላቸው ተሰናብታቸው ተነሳች፡፡ ከጠላት ዓይን እንዳትገባ የጠላትን መውጣት ጠብቃ ወደ አምደ ወርቅ ከተማ አቀናች፡፡ ወደ እብናትም ተጓዘች፡፡ ከድካም በኋላ ደብረ ማርቆስ ከተማ ደረሰች፡፡ ወርቅ ደብረ ማርቆስ ከመግባቷ አዲስ ቤተሰብ አግኝታለች፤ ሕልሟን ትኖር ዘንድ ጉዞ ጀምራለች፡፡ ወርቅን በስልክ አግኝቻታለሁ፡፡ ስለነበረችበት ሁኔታም ነግራኛለች፡፡ ʺበረሃ ውስጥ ነበርን፤ ዋሻ እየፈለግን ነበር የምንኖረው፤ ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ ነው ወደ ዋሻ የሄድነው፤ ወጡ ሲባል እየሄድን ምግብ እናመጣለን፤ ቤተሰቦቼ በረሃ ውስጥ ነው ያሉት” ነው ያለችኝ፡፡ የነገውን ተስፋ በማድረግ የምትወዳቸውን የምትሳሳላቸውን ቤተሰቦቿን በበረሃ ጥላቸው፣ በልቧ እያሰበቻቸው፣ በእንባ ተሰናብታቸው መጥታለች፡፡ ያስጨንቃል፤ ግን ምን ይደረጋል? ʺጓደኞቼ ልንሄድ ነው ሲሉ የሆነ ስሜት ተሰማኝ፤ ደግሞ አባት የለኝም፤ አባቴ ሞቶብኛል፤ አባቴ እኔን የማስተማር ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ ነበር፤ ያለችኝ እናቴ ብቻ ናት፤ እኔ ደግሞ በጣም ተናደድኩ፤ እናቴም እንደጓደኞችሽ ሁኚ ሂጂ አለችኝ፤ ብርም አልነበረኝም፤ ከአምደ ወርቅ እስከ እብናት አንድ መኪና በነጻ አመጣኝ፡፡ ከእብናት ደብረ ማርቆስ ድረስ ከጓደኞቼ ጋር መጣሁ፡፡” እያለች ነበር ጉዞዋን በሲቃ የነገረችኝ፡፡ ወርቅ ከቤተሰብ ናፍቆት ተነጥላ፣ ተምራ ያልፍላት ዘንድ ዕውቀት ፍለጋ ነው አመጣጧ፡፡ የችግር ጊዜ ቢሆንም ያለችውን እድል መጠቀም እንዳለባት ገብቷታል፡፡ ለዛም ነው ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጣ የሄደችው፡፡ ወርቅ ሌሎች መማር የሚፈልጉ፣ ትምህርት ቤት የናፈቃቸው ልጆች እንዳሉም ነግራኛለች፡፡ ነገር ግን በዚያው ቀርተዋል፡፡ ወርቅ በደብረ ማርቆስ አዲስ ቤተሰብ አግኝታለች፡፡ አዲስ እናት፣ እህት ሁሉንም ነገር ሊሆኗት የተቀበሏት ደግሞ ወይዘሮ ትዕግስት የኔአባት ናቸው፡፡ ወይዘሮ ትዕግስት የኔአባት የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ናቸው፡፡ ወርቅም ደስ በሚያሠኝ ሁኔታ እንደተቀበሏት ነው የነገረችኝ፡፡ ሰላም እስኪመጣና ትምህርት በአካባቢው እስኪጀመር ድረስ ከእነርሱ ጋር እቆያለሁም ነው ያለችኝ፡፡ ወይዘሮ ትዕግስት “እድለኛ ነኝ፤ ጎበዝ ተማሪ ተቀብዬ ላስተምር ነው” ብለውኛል፡፡ “ማገዝ ባለብኝ ደረጃ አግዠ ማስተማር እንዳለብኝ አምን ነበር፤ ለማስተማር ዝግጁ ነኝ፤ የሚያስፈልጋትን ሁሉ አሟልቻለሁ፤ ሰኞ ትምህርቷን ትጀምራለችʺ ነው ያሉኝ፡፡ ወይዘሮ ትዕግስት “ፈቃደኛ ከሆነች መማር እስከምትፈልግበት የትምህርት ደረጃ ለማስተማር ዝግጁ ነኝ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ብትገባም እቀጥላለሁ፣ ራሷን ችላ ቤተሰቦቿን እስከምትረዳ ድረስ ከእኔ ጋር መቆዬት ከፈለገች ለማቆዬት ዝግጁ ነኝ” ነው ያሉኝ፡፡ ለቤሰተቦቿ ደኅንንቷ ተጠብቆ እንደምትማር መረጃ መስጠታቸውንም ነግረውናል፡፡ ቤተሰተብ ጥላ ስለመጣች ጭንቀት ቢኖርም ሰላም ነችም ነው ያሉኝ፡፡ ወይዘሮ ትዕግስት “እንደ ልጄና እንደ ታናሽ እህቴ አድርጌ የሚያስፈልጋትን እያሟለሁ፣ ነገ ቤተቦቿን፣ ሀገርና ሕዝብን የምትጠቅም ልጅ እንድትሆን አድርጌ ነው የማስተምራት” ብለዋል፡፡ ወይዘሮ ትዕግስት በሰላማዊ የክልሉ አካባቢዎች ያሉ ሁሉ አንድ አንድ ልጅ ማስተማር አለባቸው ብለዋል፡፡ ከክልሉ ውጭ ያሉ የክልሉ ተወላጆችና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ችግር ማለፍ ስላለብን አንድ ዓመት አይደለም አንድ ቀን ትምህርት መስተጓጎል ስለሌለበት ሁሉም ሰው አንድ አንድ ልጅ ተረክቦ፣ ይሄን ጊዜ እንድንሻገረው እፈልጋለሁ ነው ያሉት ወይዘሮ ትዕግስት፡፡ በተጎዱ አካባቢዎች ያሉ ተማሪዎች ብዙ ችግሮች ስላዩ በሥነ ልቦና ጠንካራ እንዲሆኑ መምከር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ እናታቸው በደስታ እንደተቀበሏትም ነግረውናል፡፡ ከቤት ውስጥ ሥራ እንድትሠራልን ሳይሆን፣ እንደ ልጅ አድርገን ለማስተማር ነው በደስታ የተቀበልናት ብለውኛል፡፡ አንተስ? አንቺስ? እናንተስ? ይሄን ቀን ለማለፍ ምን አደረጋችሁ ነው? ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም :- https://t.me/asharamedia24 ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- https://t.me/asharamedia24 Facebook :- https://www.facebook.com/asharamedia24 ዩትዩብ:- https://bit.ly/33XmKro

Source: Link to the Post

Leave a Reply