ʺክብር የሚገባቸው ክብሩን ወስደዋል”! ነሐሤ 21/2014 ዓ.ም (አሻራ ሚዲያ) የሚያከብሩት ይከበራሉ፣ የሚወድዱት ይወደዳሉ፣ ስለ እውነት የቆሙት የእውነት ይመሰገናሉ፣ እርሳቸው ለምድራዊት…

ʺክብር የሚገባቸው ክብሩን ወስደዋል”! ነሐሤ 21/2014 ዓ.ም (አሻራ ሚዲያ) የሚያከብሩት ይከበራሉ፣ የሚወድዱት ይወደዳሉ፣ ስለ እውነት የቆሙት የእውነት ይመሰገናሉ፣ እርሳቸው ለምድራዊት ክብር ብለው አልሠሩም ለታይታም አልኳተኑም፣ ስለ እውነት፣ የእውነት እና ለእውነት አገለገሉ እንጂ፡፡ ጨለማ በበዛበት፣ የሞት መላእክ ነጋሪት በሚጎሰምበት፣ ረሃብና ጥም በነበረበት፣ ቀበሮ በጎችን ለመብላት በተሰለፈበት፣ ተኩላው ባሰፈሰፈበት በአስቸጋሪው ወቅት የበጎች እረኛ ሳያንቀላፉ፣ ዓይናቸውን ከበጎቻቸው ላይ ሳያነሱ በትጋት ጠበቁ፡፡ መጠጊያ ላጡት መጠለያ ኾኗቸው፣ ለጨለመባቸው በጨለማው ውስጥ ብርሃን አሳዩዋቸው፣ ይህ ቀን አያልፍም ያሉትን እንደሚያልፍ አበረቷቸው፣ አጠነከሯቸው፣ ያዘኑትን አጽናኗቸው፣ የተከዙትን አረጓጓቸው፣ ምንም የለንም ያሉትን ብዙ ነገር እን…ዳላቸው አሳዩዋቸው፡፡ በመከራ ቀን አብዝቶ መበርታትን፣ በመከራ ቀን ጸንቶ ማመንን፣ ተግቶ መሥራትን፣ ተስፋ ማድረግን አስተማሯቸው፡፡ በጎቻቸውን ከተኩላ አፍ አዳኗቸው፣ ከቀበሮ ጠበቋቸው፣ በረሃብ እንዳይሞቱ መገቧቸው፣ ጥም እንዳይገድላቸው አጠጧቸው፣ ተስፋ እንዳይቆርጡ ተስፋ ኾኗቸው፣ ማዕበሉን እየከፈሉ አሻገሯቸው፡፡ በጾምና በጸሎት በርትተው አበረቷቸው፣ ሳያቋርጡ ለአምላካቸው ምልጃና ጸሎት እያቀረቡ ከከፋው መከራ አወጧቸው፡፡ እረኛው ከበጎቼ ርቄ አልሄድም፣ በጎቼን በዱርና በገደል አልበትንም፤ ሞቴም ድኅነቴም ከበጎቼ ጋር ነው አሉ፡፡ ያሉትን አደረጉት፣ ቃላቸውን ፈጸሙት፣ መከራውን በአንድ እጃቸው መስቀል በሌላኛው እጃቸው ምርኩዝ ይዘው ተሻገሩት፡፡ እርሳቸው ምድራዊት ዓለምን አይፈልጓትም፣ ጠብና ጥላቻ የበዛባትን ምድር አይወዷትም፣ ሐሰት በበዛበት ዓለም ውስጥ እውነትን መሰከሩ፣ በመከራ ቀን አብዝተው ጠነከሩ፣ በልጅነታቸው ተመርጠዋል፣ በወጣትነታቸው ዘመን አምላካቸውን አስበዋል፣ በመልካሙ መንገድ ተመላልሰዋል፡፡ በክፉ ቀን መጠጊያ ጥላ ኾነዋል፡፡ የሞት ጥላ አላስፈራቸውም፣ የጥይት እሩምታ አላስደነገጣቸውም፣ ሞት በበዛበት፣ ረሃብ በጠነከረበት በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ደጋፊና አቃፊ ኾነው መርከቧን ከማዕበል ታደጓት፣ ምድሯን በመልካም ሥራቸው አረጋጓት፣ ተስፋ ያጣችውን ምድር ተስፋ ሰጧት፣ ጥላ ኾነው አስጠለሏት፡፡ ገዳዮች ከሕዝብ ላይ አፈሙዛቸውን እንዲመልሱ አደረጓቸው፣ በአባታዊ ተግሳጽ ገሰጿቸው፡፡ እኒያ የወልድያ እናቶች መከራው ጽንቶባቸው፣ ችግሩ በርትቶባቸው ነበር፡፡ ወልድያ መብራቷ ጨልሞ በጨለማ ውስጥ ተዘፍቃለች፣ ያቺ ለወትሮው ደማቅ የሆነችው፣ ሳቅና ጨዋታ የመላባት፣ ደስታና ፍቅር የተትረፈረፈባት ከተማ ጎዳናዎቿ ጭር ብለዋል፡፡ ወራሪዎቹ የሽብር ቡድኑ አባላት ያቺን የተራራ ሥር እመቤት ስቃይዋን አበዙባት፡፡ አጉርሰው የሚያድሩት እነዚያ ደጋግ ሰዎች ራባቸው፣ የተጠማውን አጠጥተው የሚያረኩት እነዚያ መልካም ሰዎች ጠማቸው፡፡ የተከዘውን የሚያረጋጉት፣ ያዘነውን የሚያጽናኑት ሐዘን በዛባቸው፡፡ ማን ይደርስልናል እያሉ በሚጨነቁበት፣ በሚያለቅሱበትና በሚተክዙበት በዚያ ጊዜ ታዲያ ሕዝብን ሁሉ ይጠብቁ ዘንድ አስቀድመው የተመረጡ አባት ነበሩና ደረሱላቸው፡፡ ከአንደበታቸው በሚወጣው መልካም ንግግር አበረቷቸው፣ በጾምና በጸሎታቸው ጠበቋቸው፣ ወልድያ ባዘነች ጊዜ መልካም አባት ጣለላት፣ ተስፋ አየች፣ ድልን ናፈቀች፣ ጨለማውን ገፍፋ ለብርሃን እንደምትበቃ አመነች፡፡ እኒያ በጎቻቸውን በታማኝነት የጠበቁት፣ ከክፉ መከራ ያተረፉት፣ ከበላተኛ መንጋጋ ያላቀቁት አባት በየጎዳናዎች እየተመላለሱ ሕዝባቸውን አበረቱ፡፡ ቀናት ሳምንታትን፣ ሳምንታት ወራትን እያተካኩ ሄዱ፡፡ እሳቸው ግን ሳይደክማቸው ኳተኑ፡፡ የሚያምኑት፣ የሚመኩበትና በብጽዕና የሚያገለግሉት አምላካቸው ጠበቃቸው፣ ጸሎትና ምልጃቸውን ሰማቸው፡፡ በአደራ የሰጠኸኝን በጎች በትጋት እጠብቅ ዘንድ አበርታኝ አሉት አበረታቸው፣ እንዳልዝል ደግፈኝ አሉት ደገፋቸው፣ እንዳልደክም እርዳኝ አሉት ረዳቸው፡፡ ቅን አገልጋይ፣ ጠቢብ መሪ ናቸውና የሚሹትን ሁሉ አደረገላቸው፡፡ እሳት በሚነድበት መሐል ሕዝብ እየመሩ እንዲያሻግሩ ብርታት ሰጣቸው፡፡ ብዙ ሕዝብ ይከተላቸዋል፣ ወደ ባዕታቸው እየሄደ በአጠገባቸው ይሰበሰባል፡፡ አባቴ ኾይ ራበኝ፣ ጠማኝ፣ ሕመም ሊገድለኝ ነው ይላቸዋል፡፡ ልጆቼን የማበላው አጣሁ፣ ተቸገርኩ፣ የሚላቸው ብዙ ነው፡፡ ጧሪ የሌላቸው፣ ችግር የበዛባቸው እርሳቸው ወዳሉበት ይሄዳሉ፡፡ የጠየቃቸውን ሁሉ የለኝም አይሉትም፡፡ ለተጠየቁት ሁሉ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ለራበው ምግብ፣ ተስፋ ላጣው ተስፋ፣ መድኃኒት ላጣውም መድኃኒት ይሰጣሉ፡፡ ቀንና ማታ በጸሎትና በትጋት የሚከተላቸውን ሕዝብ ሁሉ ይጠብቃሉ፡፡ ተስፋ በታጣበት ዘመን ተስፋ መሆን ምንኛ መታደል ነው? በጨለመ ዘመን ብርሃን ኾኖ ማሻገርስ ምን አይነት መመረጥ ነው? ሳይሰለቹ መጠበቅስ ምን አይነት ጸጋ ነው ? ብጹዕ አቡነ ኤርምያስ ይሄን አደረጉት፡፡ ጥቂት ያለው ምንም ለሌለው እንዲሰጥ እየለመኑ ሕዝብ አተረፉ፡፡ ከወራት በኋላ ወልድያ ነጻ ወጣች፣ ፍቅርና ደስታዋ ተመለሰላት፡፡ በመከራው ዘመን ጥላ የነበሩት፣ ማዕበሉን ያሻገሩት አባት አባ አባ እየተባሉ ተነሱ፣ ተመሰገኑ፡፡ ሥራቸውና ድካማቸውስ ለምድራዊ ምስጋና አይደለም፡፡ ድካማቸውና ሩጫቸውስ ለሰማዩ ቤታቸው ነው፡፡ እሳቸው ሃይማኖት አልመረጡም፣ አካባቢም አለዩም፣ ሰው የሆነን ሁሉ አበረቱ፣ ረዱ እንጂ፡፡ ከተራራ የገዘፈ ተጋድሎ የፈጸሙት አባት በስማቸው ተራራ ተሰየመላቸው፡፡ እኒህ ለመልካም ነገር የተዘጋጁት፣ በብጽዕና የሚኖሩት አባት ሌላ ክብር ይገበወታል ተብለዋል፡፡ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ሕዝብ በተጨነቀበት ዘመን እውነተኛ አባት ኾነው ተገኝተዋልና ክብር ሁሉ ለእርስዎ ይገባል ሲል የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል፡፡ ክብር የሚገባቸው አባት ክብሩን ወስደውታል፡፡ ኢትዮጵያ ተስፋ የሚያስቆርጡ ጠላቶች በተነሱባት ዘመን ተስፋን የሚሰጡ አባቶችን ለሕዝቧ ትሰጣለች፡፡ መጠጊያ የጠፋ በሚመስልበት ዘመን መጠጊያ ትወልዳለች፡፡ ድንበር የሚገፋ በተነሳ ዘመን ጀግና ልጆቿን ታስነሳለች፡፡ የደጋጎች እናት ማሕጽኗ አይደርቅም፣ ደግ እየወለደች ደግነትን ታስተምራለች፣ ጀግና እየወለደች ጀግንነትን ታሳያለች፣ በጀግንነትና በደግነት ትጠበቃለች፡፡ ተስፋ ላጠው ሰው ሁሉ ተስፋ ትሆናለች፡፡ የደጎቹ ሰዎች መልካምነት የክፉዎችን ክፋት ታጠፋለች፣ ጨለማውን ትገፍፋለች፡፡ ለትውልድ ሁሉ በረከትንና ደስታን ታመጣለች፡፡ ©አሚኮ ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24

Source: Link to the Post

Leave a Reply