You are currently viewing ʺየተከዜ ዳር ማዕበሎች፣ የበረሃ መብረቆች”  ባሕር ዳር:-የካቲት 21/2014 ዓ.ም                 አሻራ ሚዲያ የበረሃ መብረቆች፣ የኢትዮጵያ ቀኞች፣ የጀግንነት መሠረቶች፣ የጽናት…

ʺየተከዜ ዳር ማዕበሎች፣ የበረሃ መብረቆች” ባሕር ዳር:-የካቲት 21/2014 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ የበረሃ መብረቆች፣ የኢትዮጵያ ቀኞች፣ የጀግንነት መሠረቶች፣ የጽናት…

ʺየተከዜ ዳር ማዕበሎች፣ የበረሃ መብረቆች” ባሕር ዳር:-የካቲት 21/2014 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ የበረሃ መብረቆች፣ የኢትዮጵያ ቀኞች፣ የጀግንነት መሠረቶች፣ የጽናት ተምሳሌቶች፣ የማይደፈሩ፣ በትግል ውስጥ የሚኖሩ ጀግኖች፡፡ ለማንነት፣ ለአንድነት፣ ለኢትዮጵያዊነት፣ ለክብርና ለፍቅር ሲሉ አያሌ በደሎችን አሳልፈዋል፡፡ ቤትና ንብረታቸውን ጥለው በበረሃ ውስጥ ደረቆት እየበሉ፣ በጠብታ ውኃ እየዋሉ ዓመታትን ተጉዘዋል፡፡ አንቺ ተከዜ የከበበሽ፣ መስጠት የማይሰለች መሬት የታደለሽ፣ ወርቅ የሚታፈስብሽ፣ ፈሪ የማይሰነብትብሽ፣ ጀግና የሚወለድብሽ፣ ደፋር የሚኖርብሽ፣ ጀግነነት ያከበረሽ፣ በአሸናፊነት የኖርሽ ወልቃይት ኾይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ እያሉ ለማንነታቸው ለእርሳታቸው ተንገላቱላት፣ ቆሰሉላት፣ ሞቱላት፡፡ ስመሽ ሲጠራ በዙፋን የነበረው የደነገጠልሽ፣ ገፍተው የማይጥሉሽ፣ ምሰው የማይቀብሩሽ፣ ችለው የማይለውጡሽ፣ አንድ ማንነት፣ የጸና ጀግንት፣ የማይናወጽ ኢትዮጵያዊነት፣ የማይፈታ አንድነት ያለበሽ ወልቃይት ኾይ ምስጢርሽ ምን ይኾን? ዓይኖች ኹሉ የሚያዩሽ፣ ጀሮዎች ኹሉ ለመስማት የሚመርጡሽ፣ ልቦች ኹሉ የሚያስቡሽ፣ አንደበቶች ኹሉ የሚናገሩልሽ፣ ጀግኖች የሚወለዱብሽ። ተተኩሶ የማይሳትብሽ፣ ሀብትና በረከት የመላብሽ ወልቃይት ኾይ የመወደድሽ ነገር ምንድን ነው? አንቺን የነኩት ኹሉ ወድቀዋል፡፡ ከከፍታሽ ሊያወርዱሽ የከጀሉት ቀድመው ወርደዋል፣ ያለ ማንነት ማንነት ሊሰጡሽ የከጀሉት ሁሉ አልቀዋል፡፡ በጉያሽ ውስጥ ባለው ሀብት የከበሩት፣ በልጆችሽ እንባ ደስታቸውን የሸመቱት፣ በጸጋሽ ሸማ የሸመኑት ሁሉ አይገባቸውም ነበርና ከክብራቸው ወርደዋል፣ ሳቃቸውን ተነጥቀዋል፣ ሸማቸውን ጥለዋል፡፡ ክብራቸውን ተገፍፈዋል፡፡ ዙፋናቸውን ተነጥቀዋል፡፡ ʺወልቃይት” በሚል ስም የተነሳው ማዕብል ኢትዮጵያን አጥለቀለቀ፣ በንጹሐን ደምና እንባ የተቆለለውን ዙፋን አጨናነቀ፣ ለረጅም ዓመታት ይኾናል ተብሎ የተገነባው የክፋት ግንብ ወዳደቀ፣ ከዙፋን ላይ የነበረው ክፉ መንፈስ ለቀቀ፡፡ ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ያሉት፣ ከስሟና ከክብሯ ጋር ቃል ኪዳን ያሰሩት ሁሉ ሞትን ናቁት፣ ደረታቸውን ለጥይት፣ አንገታቸውን ለስለት አሳልፈው ሰጡ፡፡ ወልቃይት የሚለውን ማዕበል የሚያስቆም መገደቢያ ጠፋ፡፡ ታፍኖ የኖረው ድምጽ፣ ለዓመታት የተፈጸመው የንጹሐን ሞት ደምና እንባ እየገነፈለ ወጣ፡፡ ያን ስሜት የሚቆጣጠረው አልገኝ አለ፡፡ መላ ተፈለገለት፣ ዘዴ ተዘየደለት፣ ዘዴውም የወልቃይትን እውነት ማጥፋት ነበር፡፡ ዳሩ የወልቃይትን እውነት መቀበል እንጂ፣ የወልቃይትን እውነት ማፈን የማይቻል ኾነ፡፡ ተንኮለኞቹ ደግሞ የወልቃይትን እውነት የመቀበል አቅም አልነበራቸውም፡፡ የወልቃይት እውነት ደግሞ የማይሻር፣ የማይሸረሸር ኃያል ነበርና ሊክዱት የፈለጉትን ካዳቸው፣ ሊያጠፉት የከጀሉትን አጠፋቸው፣ የወልቃይት እውነት ነጠረ፣ የክፉዎች ሃሳብ ተቀበረ፡፡ ደም የፈሰሰበት፣ አጥንት የተከሰከሰበት፣ ትክ የለሽ ሕይወት የተገበረበት ነበርና ወልቃይት የሚለውን አስቀድሞ የመጣውን ማዕብል የሚገታው፣ ከፍጥነቱ የሚያስቆመው አልገኝ አለ፡፡ እውነተኛውን ማዕበል ማስቆም ያማራቸው ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ እያሉ በሚወጡት ላይ ጥይት ተኮሱ፣ አስለቃሽ ጭስ አጨሱ፤ የማዕበሉን መነሻ በር ግን መዝጋት አልቻሉም ነበርና ማዕበሉ ባሰባቸው፣ አጥለቀለቃቸው፣ መውጫ መግቢያ አሳጣቸው፡፡ እነዚያ ከተከዜ ወንዝ ተጎንጭተው፣ ዋኝተው፣ በጀግኖች አባታቶቻቸው ጀግንነት ተቃኝተው ያደጉት የስሜን በጌምድር ጀግኖች ያለ ማንነት ማንነት ተሰጥቷቸው፣ በእርስታቸው ባዳ ኾነው እንዲኖሩ ተፈርዶባቸው ነበርና በቁጭት ተነስተዋል፡፡ ያለ ድል ላይመለሱ ቃል ገብተዋል፡፡ በዚያ ጊዜ መንግሥት የነበረው የክፉ ሀሳብ ጠንሳሹ ማዕበሉን ለማስቆም ጥረት አደረገ፡፡ ግን አልተሳካለትም፡፡ ወልቃይት የሚለው ወጀብ ቤተ መንግሥቱን አናወጸው፣ ዙፋኑን አማታው፣ የባለ ጊዜዎችን ጀንበር አጠለቀው፡፡ በቀላል ነገር አይደፈረም ብለው ሰርተውት የነበረው ሁሉ ፈራረሰባቸው፣ የሰበሰቡት ተበተነባቸው፣ ያቆሙት ወደቀባቸው፣ ያመኑት ዘመን ከዳቸው፣ ዝም ያለው ሕዝብ ተነሳባቸው፣ ከበነዋል ያሉት ሁሉ ከበባቸውና መውጫ መግቢያ ጠፋባቸው፡፡ ወልቃይት፣ ወልቃይት፣ ወልቃይት እያለ እየደገጋመ አቃጨለባቸው፡፡ ወልቃይት የሚለው ስም እንቅልፍ ነሳቸው፡፡ የወልቃይት ስም ከፍ እያለ፣ የዚያ ዘመን መሪዎች ስም ደግሞ እየኮሰመነ ሄደ፡፡ ወልቃይት ነጻነት አመጣች፣ ወልቃይት አዲስ ሥርዓት አሳዬች፣ ወልቃይት የክፉዎችን ግንብ አፈረሰች፣ ወልቃይት ቀባሪዎቿን ቀበረች፣ ወልቃይት አንረሳሽም ያልዋትን አከበረች፣ ከፍ አድርጋ ስማቸውን ጻፈች፣ ወልቃይት በኢትዮጵያ ምድር ከፍ ብላ ተጠራች፣ ወልቃይት ለነጻነት የሚተጉትን ቀሰቀሰች፣ ወልቃይት ክፉዎችን አሳደደች፣ ወልቃይት ወደ ቀደመው ተመለሰች፡፡ ከወደ ወልቃይት የፈነጠቀው ጮራ በመላ ኢትዮጵያ አበራ፣ በዚያ ተኩሶ መሳት በማይታወቅበት፣ ወርቅ በሚታፈስበት፣ ወተትና ማር በማይታጠባት፣ ጀግና እንደ ውኃ በሚፈልቅበት፣ አያሌ ታሪክ በተሰራበት ምድር ሌላ ታሪክ ተሠራ፡፡ የስሜን በጌምድር ጀግኖች ጀብዱ የሰሩበት፣ ሞት የማይፈሩ አርበኞች የተመላለሱበት፣ ለሀገራቸው ቃል ኪዳን የገቡበት፣ በየዘመኑ የተነሳውን ጠላት የቀጡበት ያ ምድር ምስጡሩ ብዙ ነው፡፡ ያቀፈው እውነት እልፍ ነው፡፡ እነሆ የወልቃይት እውነት በመላው ኢትዮጵያ አዲስ ነገር አሳይቶ የበለጠ ከፍ ብሏል፡፡ ከዓመታት በፊት ወልቃይት ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ ያሉት ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተው፣ በኖሩባት ምድር ክብር ተክተው አልፈዋል፡፡ ወልቃይትን መርሳት ከቀኝ ጋር መጣላት፣ ወልቃይትን መርሳት እውነትን መርሳት ነው ሲሉ ቃል ኪዳን ትተዋል፡፡ ከተከዜ ዳር ዳር የበቀሉት፣ በተከዜ ውኃ ዋኝተው ያደጉት፣ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ እትብታቸውን ያስቀመጡት የተከዜ ዳር ማዕበሎች፣ የበረሃዎቹ መብረቆች፣ የማይደፈሩ አናብስቶች፣ ቀደም በእውነታቸውና በቃል ኪዳናቸው ያደረሱትን፣ በአትንኩኝ ባይነታቸው አንድ ያደረጉትን ሕዝብ ዛሬ በአካል እየተገኙ የበለጠ አንድ እያደረጉት፣ እውነታቸውን እየሰጡት፣ እውነቱን እየነገሩት ነው፡፡ የስሜን በጌምድር ባለ እርስቶች፣ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ልጆች፣ የጎንደር አማራዎች በጎጃም፣ በሸዋና በወሎ እየተዘዋወሩ ዘመዶቻቸውን እየጠየቁ፣ ፍቅራቸውን እያጠበቁ ነው፡፡ በሕመማቸው አብረው የታመሙላቸው፣ በደስታቸው ቀን አብረው የተደሰቱላቸው የጎጃም፣ የሸዋና የወሎ ዘመዶቻቸውም እልል እያሉ ተቀብለዋቸዋል፡፡ አፈር ስሆን እያሉ አጉርሰዋቸዋል፣ በሚያጌጡበት አስጊጠዋቸዋል፣ አንለያይም ሲሉ የማይሻረውን ቃል ኪዳናቸውን ሰጥተዋቸዋል፣ የፀናውን ቃላቸውን በጋራ አጽንተዋል፡፡ ʺክብሩ ሲመለስ ማንነቱ የሰው ትንሽ ትልቁን ደስታ አስለቀሰው” እንዳለ ዘፋኙ በወልቃይት ደስታ ሁሉም በደስታ አልቅሷል፡፡ የወልቃይት መንፈስ ሁሉንም እያዳረሰ ከፍ እያለ ነው፡፡ ወልቃይት ምንጩ ላይደርቅ የገነፈ ማዕበል ነውና የሚያስቆመው የለም፡፡ የወልቃይት እውነት በልጆቿ አማካኝነት ከዳር ዳር እየደረሰ ነው፡፡ እውነት፣ አንድነት፣ ጀግንት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ አይደፈሬነት፣ ጽናት፣ አልሞ መችነት፣ አሸናፊነት ሁሉ አብሯቸው አለ፡፡ አብሯቸውም ይኖራል፡፡ የማይሻር ቃል ኪዳን ነውና ሳይሻር ይኖራል፣ በትውልድ ቅብብሎሽ ይከብራል፣ ይከበራል፣ ማዕበሉም ሳያቋርጥ ይፈስሳል፣ ክፉውን ያፈርሳል፣ መልካሙን ያረሰርሳል ሲል አሚኮ ዘግቧል ። ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም :- https://t.me/asharamedia24 ዩትዩብ:- https://bit.ly/33XmKro ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- https://t.me/asharamedia24 Facebook :- https://www.facebook.com/asharamedia24 ዩትዩብ:- https://bit.ly/33XmKro

Source: Link to the Post

Leave a Reply