ʺየንፁሐን ደም በግፍ ፈሰሰ፣ ከተማዋ በዋይታ ተመላች” ባህርዳር :- የካቲት 12/2014 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ባሕር ዳር: የካቲት 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ)…

ʺየንፁሐን ደም በግፍ ፈሰሰ፣ ከተማዋ በዋይታ ተመላች” ባህርዳር :- የካቲት 12/2014 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ባሕር ዳር: የካቲት 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ነገሥታቱ፣ መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ሊቃውንቱ፣ ወይዛዝርቱ፣ ጎበዛዝቱ በክብር የተመላለሱባት አምሳለ አበባ የሆነች፣ በፈካ አበባ ስም የተሰየመች፣ በብርሃን ኢትዮጵያ በታላቋ እመቤት የተመሠረተች ከተማ የደም ማዕበል አለባሳት፣ ዋይታ በዛባት፣ ዓለም የታየባት፣ ግርማ ሞገስ ያለባት፣ ነገሥታቱ የኖሩባት ያቺ ከተማ ድብዝዝ አለች፡፡ የክፉዎች በትር በንፁሐን ላይ አርፏልና፣ ደጎች በግፍ አለፉ፡፡ ብዙዎች ያለ ቀናቸው ተቀሰፉ፡፡ በክብር የማይደራደሩት፣ በአንድነት የሚነሱት፣ በጀግንነት የሚታወቁት ኢትዮጵያውያን ጠላታቸውን ለማጥፋት ዱር ቤቴ ብለዋል፡፡ በዚያ በውቧ ከተማ በየአቅጣጫው የሚተኮሰው ተኩስ ነዋሪዎች እንዳይረጋጉ አድርጓቸዋል፡፡ ከአሁን አሁን የኢትዮጵያ አርበኞች ዋጡኝ እያለ የሚሰጋው የጠላት ሠራዊት በቀልቡ መኖር አቅቶታል፡፡ ጀግኖች አርበኞች በየአቅጣጫው በጠላት ላይ ጥቃት እያደረሱ ያስጨንቁት ነበርና፡፡ አርበኞች በከተማዋ ያሉ ጠላቶችን ለመደምሰስ፣ በጠላት የረከሰችውን ለመቀደስ ተጋድሎ ላይ ናቸው፡፡ አርበኞቹ ጠላት ባላሰበውና ባልጠበቀው መንገድ እየሄዱ ስለነበር የጠላት ስጋት ከፍ ያለ ነበር፡፡ ወረሃ የካቲት ደርሷል፡፡ በዚያ ጊዜ የኔፕልስ ልዕልት ወልዳ በኢጣልያ የጦር መሪዎች በኩል ደስታ ሆኗል፡፡ ግራዚያኒም በልዕልቷ መውለድ በመደሰቱ ገንዘብ እሰጣለሁ ብሎ ቃል ገብቷል፡፡ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ ሰዎች እንዲሰባሰቡ አዘዘ፡፡ በዚያም ውስጥ የኢጣልያ ሹማምንትና እና መኳንንቱ ነበሩ፡፡ እንዲሰበሰቡ ለተደረጉት ድሆች ለእያንዳንዳቸው ሁለት ማርትሬዛ ብር እንዲሰጣቸው ተወስኗል፡፡ የኔፕልስ ልዕልት መውለድ ለኢትዮጵያውያ ምናቸው ነው? በሀገራቸው ጠላት እያለ የልዕልቷ መውለድ ለእነርሱ ምን ይፈይድላቸዋል? እነርሱ የወለዷቸው ልጆች እየተጨነቁ፣ የእነርሱ ልጆች ከጠላት ጋር እየተፋለሙ፣ ከጠላት መንደር ልዕልቷ ወልዳለችና ኑ ደስታዬን ተጋሩ ብሎ ማክበረስ ምን ፋይዳ አለው? የእነርሱ ደስታቸው ሀገራቸው ነጻ ወጥታ፣ ንጉሡ በዙፋኑ ሲጸኑ፣ ሕዝቡም ሰላም ሲሆን መሆኑን ግራዚያኒ አላወቀም፡፡ ያም ኾኖ የኔፕልስ ልዕልትን መውለድ ምክንያት በማድረግ ግራዚያኒ በጠራው ጥሪ ውስጥ ብዙዎች ተሰባስበዋል፡፡ የዚህን ድግስ ጉዳይ አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ሰምተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ለሀገራቸው ነጻነት ሲሉ በዱር በገደል እየተጋደሉ የኔፕልስ ልዕልት ወልዳለች በሚል ሰበብ የጠላት መፈንጠዝ አበሳጭቷቸዋል፡፡ ንዴታቸው በቤት ውስጥ ኾኖ ስለጉዳዩ ከመነጋገር ያለፈ ነበር፡፡ ግራዚያኒ በጠራው የደስታ ድግስ ላይ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ተስማሙ፡፡ የኢጣልያ ወራሪ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሰው ግፍ በእጅጉ አስከፍቷቸዋል፡፡ ቀኑ ደርሷል፤ አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ወደ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት አቅንተዋል፡፡ በኪሳቸው ቦንብ ይዘዋል፡፡ ቦንቡን እንዴት መወርወር እንዳለባቸው አስቀድመው ተለማምደዋል፡፡ ማርሻል ግራዚያኒ ለተሰበሰበው ሕዝብ ንግግር እያደረገ ነው፡፡ ኢጣልያን ከፍ እያደረገ ይናገራል፡፡ አብርሃምና ሞገስ ኪሳቸውን ዳበሱት፡፡ ግራዚያኒ በኩራት እየተናገረ ነው፡፡ ንዴታቸው ገንፍሏል፡፡ በኪሳቸው የያዙትን ቦንብ አወጡት፡፡ አመቻችተው ወረወሩት፡፡ አካባቢው በድንጋጤ ተዋጠ፡፡ የተሰማው ድምጽ ከሰማይ ይሁን ከመሬት አልታወቀምና ድንጋጤው ከባድ ነበር፡፡ ቦንቦች ተደጋግመው ተወረወሩ፡፡ ግራዚያኒ ቆሰለ፡፡ አብርሃምና ሞገስ የልባቸውን አድርገው ሲወጡ ስምኦን አደፍርስ መኪና ይዞ እየጠበቃቸው ነበርና በእርሷ መኪና ከአካበቢው ተሠወሩ፡፡ አካባቢው ድብልቅልቁ ወጣ፡፡ የቦንብ ፍንዳታው ጋብ እንዳለ አድፍጠው የነበሩ ወታደሮች ተነሱ፡፡ ካርቴሲ የወገቡን ሽጉጥ መዝዞ ወደ ኢትዮጵያውያን መኳንንት አዙሮ ተኮሰ፡፡ የአለቃቸውን ምሳሌ ያዩ ካራቢኔሪዎችና ወታደሮቹ ከየአቅጣጫው ይተኩሱ ጀመር፡፡ ለሰዓታት ያለ መቋረጥ ጥይት እንደ በረዶ ወረደ፡፡ ባዶ እጃቸውን የነበሩት ንፁሐን መሄጃው ግራ ገባቸው፡፡ የኢጣልያ ጥቁር ሸሚዞችና ሌሎች በእቴጌ ከተማ በአዲስ አበባ እየዞሩ ሕዝቡን ይጨፈጭፉት ጀመር፡፡ በደል ያልተገኘባቸው፣ በውስጣቸው ክፋት የሌላቸው ንፁሐን መከራው በዛባቸው፡፡ የጥይት በረዶ ወረደባቸው፡፡ የክፉዎች እጅ በላቸው፡፡ አስከሬኖች በዙ፡፡ አዲስ አበባ በወረሃ የካቲት በበጋ ወቅት የደም ጎርፍ አላበሳት፡፡ ከዳር ዳር አጥለቀለቃት፡፡ አቤቱ ምንኛ ይከብዳል፡፡ እንዴትስ ይጨንቃል፡፡ ጳውሎ ኞኞ የኢትዮጵያና የኢጣልያ ጦርነት በሚለው መጽሐፋቸው አንጄሎ ዴል ቦካን ዋቢ አድርገው ሲገልጹ ʺወደ ማታ ገደማ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ስንገናኝ ያ ጓደኛዬ ቦንብ ስጥል የዋልኩበት እጄ ዝሏል ብሎ ነገረኝ፡፡ አንዱ ኢጣልያዊ ሲያጫውተኝ በአንዲት ትንሽ ጣሳ በያዝኩት ቤንዚን አስር ቤቶች አቃጠልኩበት አለኝ፡፡ በዋናው ጦርነት ጥይት ተኩሰው የማያውቁ ጣልያኖች ሁሉ በዚያን ቀን ሲተኩሱ ዋሉ” ማለቱን አሥፍረዋል፡፡ ጣልያኖች በኢትዮጵያውያን ላይ የግፍ ግፍ ሥራ ሠሩ፡፡ ደም እንደ ውኃ በየጎዳናዎች እንዲፈስ አደረጉ፡፡ ከተማዋን ሐዘን ዋጣት፡፡ የሞት ጽልመት ከበባት፡፡ ሐንጋሪያዊው ሐኪም ደግሞ ያን ጊዜ ሲገልጸው ʺኃይለኛና ተገቢ ያልሆነ ጭፍጨፋ ነበር፡፡ ሽማግሌዎች፣ አይነ ሥውራን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ድሆች እናቶች ከእነ ልጆቻቸው ነበሩበት፡፡ ባለ ጥቁር ሸሚዞች በግቢው እየተሯሯጡ በሕይዎት ያለ ኢትዮጵያዊ ይፈልጉ ነበር፡፡ ከሬሣዎቹ መሃልም የሚተነፍስ እንዳለ እያሉ እየመረመሩ ይገድሉ ነበር፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ባለ ጥቁር ሸሚዞች፣ ካራቢኔሪዎችና የጦር ወታደሮች በከተማው ውስጥ ይሯሯጡ ጀመር፡፡ ሱቆች ሁሉ እንዲዘጉ አደረጉ፡፡ የውጭ ሀገር ሰዎችም ከቤታቸው እንዳይወጡ አዘዙ፡፡ መንገዱ ሁሉ ጭር አለ፡፡ የፖስታና የስልክ አገልግሎት ተቋረጠ፡፡ በቤተ መንግሥቱና በአካባቢው ያሉት መንገዶች በሙሉ በሬሳ ተሸፈኑ” ንፁሐን እያቃሰቱ ወደቁ፣ እናት ከልጇ ጋር ሞተች፣ ቆመው የሚመርቁ፣ ለሰላምና ለፍቅር የሚጸልዩ አረጋውያን በግፍ አለቁ፡፡ ደም ፈሰሰ፡፡ ስቃዩ ከፋ፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆኑትና በገዳዮቹ ፊት የተገኙት ሁሉ ያለ ምህረት ተገደሉ፡፡ ደማቸው በግፍ ፈሰሰ፡፡ አጥንታቸው ተከሰከሰ፡፡ ስጋቸው ተቆራረሰ፡፡ ʺምን አይነት አጨካከን ነው? ደም እንደ ውኃ ሲፈስስ በየመንገዱ ላይ ያየሁት የዛን ጊዜ ነው፡፡ የወንዶች፣ የሴቶችና የልጆች ሬሣ በያለበት ተኝቷል፡፡ ወዲያውም ከባድ የቃጠሎ ጭስ ተነስቶ ከተማዋን አጨለማት፡፡ የሕዝቡ ቤት ከተፈተሸ በኋላ ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉ ቤቱ በእሳት ይቃጠላል፡፡ ቃጠሎው ቶሎ እንዲያያዝም ቤንዚን ይጠቀሙ ነበር፡፡ ሰው እሳቱን እየሸሸ ከቤቱ ሲወጣ በመትረጌስ ይገድሉታል፡፡ ሌሊቱንም ሲገድሉና ሲያቃጥሉ አደሩ፡፡ የማረሳው ነገር በዚያ ሌሊት የኢጣልያ መኮንኖች በሚያማምር አውቶሞቢላቸው ከሚስቶቻቸው ጋር ሆነው ብዙ ሬሳ ከተከመረበትና ብዙ ቃጠሎ ከሚታይበት ቦታ በሰው ደም ላይ እየቆሙ ያን እልቂት እየተመለከቱ ይስቃሉ” ሲል የሐንጋሪው ሐኪም ዶክተር ላዲስላስ ላቭ ጽፈዋል፡፡ የሐንጋሪው ሐኪም በተለያዩ ጦርነቶች ተካፍሎ እንደሚያውቅ ይገልጻል፡፡ እንደ አዲስ አበባው አይነት እልቂት ግን አይቶ እንደማያውቅ ነው የመዘገበው፡፡ መከራ የማይበግራቸው፣ ሞትና መሰደድ ከሀገር ፍቅር ዝቅ የማያደርጋቸው ኢትዮጵያውያን ግን እየሞቱም ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር ይሉ ነበር፡፡ በዚያች ቀን በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተቀደሰችው ሀገራቸው ደማቸውን አፈሰሱ፡፡ ከግድያ የተረፉትም በወራሪዎቹ እተያዙ ወደ እስር ቤት ተወሰዱ፡፡ በእስር ቤት ውስጥ እያሉ መከራቸው በዛ፡፡ አያሌ ግፍ ተፈፀመባቸው፡፡ ይህም የሆነው የካቲት 12/1929 ዓ.ም ነበር፡፡ መገፋት የሚያጠነክራቸው ኢትዮጵያውያን አንገት ይደፋሉ ሲባሉ የበለጠ ቀና ብለው፣ ሞትን ንቀው፣ ጠላትን እያሳደዱ ተበቀሉት፣ መውጫ መግቢያ አሳጡት፣ በየአገኙበት አጋጣሚ ሁሉ ረሸኑት፡፡ ሕዝብ ጨርሶ ሀገር መምራት ያማረው የኢጣልያ ሠራዊት ጨነቀው፣ አብዝቶም ጠበበው፣ የአርበኞች ተጋድሎ እንደ ቀትር እሳት ተንቀለቀለ፡፡ ኢጣልያም ዳግም ሽንፈት ቀመሰች፣ ኢትዮጵያም ነጻ ሆነች፣ ንጉሡ በአስፈሪው ዙፋን ተቀመጡ፡፡ ጠላቶች አንገታቸውን አቀረቀሩ፣ ጀግኖች አርበኞች ደግሞ በአሸናፊነት ተኩራሩ፡፡ ወዳጄ ኢትዮጵያ በደም የጸናች፣ በአጥንት የቆመች ሀገር ናት፡፡ አባቶች እየሞቱ ያኖሯት፣ መከራ እየበዛባቸው ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር እያሉ የጠበቋት ድንቅ ሀገር ናት፡፡ የማትመረመር ምስጢር ናት፡፡ የማይደርሱባት ረቂቅ ናት፡፡ በደም መሠረት የተቀበልካትን ሀገር አብዝተህ ጠብቃት፤ ኢትዮጵያ ለዘላለም እንድትኖር የጠየቀችህን ሁሉ ሁንላት፡፡ አሚኮ ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም :- https://t.me/asharamedia24 ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- https://t.me/asharamedia24 Facebook :- https://www.facebook.com/asharamedia24 ዩትዩብ:- https://bit.ly/33XmKro

Source: Link to the Post

Leave a Reply