“ሀሳብን የጋራ ማድረግ እንጂ በጋራ ማሰብ ፈጽሞ አይቻልም!!!” ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ

(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና

የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

የሀገራችንን ነባራዊ ወቅታዊ ኹኔታ መኾን ካለበትና ሊኾን ከሚገባው ይልቅ እየኾነ ካለው ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ አንጻር ስንመለከት እጅግ በጣም የተለያየ፣ ፈጽሞ ሊቀራረብ የማይችል፣ አብሮ ሊያሰራ የማይችል፣ ፍጹም ተቃራኒ ሀሳብና አቋም ያላቸው ኃይሎችና አካላቶች ሕብረት ፈጥረውና ሕብረት ፈጥረናል ብሎም ተስማምተናል ሲሉ መስማት የተለመደ ኾኗል፡፡

ለአብነት፡- ከሕገ መንግሥቱ አንጻር ሕገ መንግሥቱን ፈጽመው ከአመጣጡ አንሥቶ የሚቃወሙ፣ አንቀበልም የሚሉ፣ መሻሻል አለበት የሚሉ፣ መለወጥ አለበት የሚሉ፣ እንደወረደ ተግባር ላይ መዋል አለበት የሚሉ፤ ከሥርዓት አንጻር የሥርዓቱን መሠረት የሚቀበሉና የማይቀበሉ፤ ከባንዴራ አንጻር ያለውን የሚቀበሉ፣ የማይቀበሉ፣ የራሳቸውን የሚሹ፤ በርዕዮተ ዓለም እጅግ የተራራቀ፣ የተቃረነ እንዲሁም የተደራጀና ትርጉም ያለው ርዕዮት የሌላቸው ኃይሎችና አካላት፤ ከአሰራር አንጻር ሥርዓቱ እንዳለ እንዲቀጥል የሚሹ፣ እንዲሻሻል የሚሹ፣ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የሚሹ ኃይሎችና አካላት፤ ከለውጥና አካሄድ አንጻር ደግሞ መጠነኛ ማሻሻያ ማድረግ የሚሹ፣ የጎላ ለውጥ ማድረግን የሚሹ እንዲሁም መሠረታዊ ለውጥ የሚሹ አካላት፤ ከታሪክ አንጻር የነበሩ ትግሎችን እንደየዕይታቸው በተለያየ ዐውድ የሚያዩ ኃይሎች – – – ወዘተ በአንድነት “በሰላማዊ ሰልፍ” ላይ እንዲሁም በሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ይታያሉ፡፡

ሀገራችን ዛሬ ያለችው እጅግ የተለያየ ፍላጎትና አቅም ያላቸው ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች በለውጥ አስፈላጊነት ላይ የተስማሙ ቢኾንም ምን አይነት? አድማሱ እስከምን የደረሰ? በማን የሚመራ? በምን ዓላማ? ለምን? የሚለው ላይ ትርጉም ባለው መንገድ የጋራ መግባባት ያለ አይመስልም፡፡

መግባባት ያለ ሚመስለው በስሜት (Emotion) እና በአስተያየት (Opinion) እንጂ ትርጉም ባለው ሀሳብ (Idea) ፣ ዕሳቤ (Thought) እና ርዕዮት /ርዕዮተ ዓለም/ (Ideology) ላይ እንዳልኾነ ግልጽ ነው፡፡

ይህም ይኾን ዘንድ ያደረጉ ብዙ ውስብስብና ሰፊ ጉዳዮች መኖራቸው ጥሬ ሃቅ ቢኾንም ከማዕቀፍ አንጻር ባሕሪያዊና ጠባያዊ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ኾነው ከጊዜ ማዕቀፍ አንጻር፡-

አንደኛ፡- በኹለንተናዊ (ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ) ጉዳዮች ሀገራችን ትላንት ምን ላይ ነበረች? መኾኗንንስ የተለያዩ ኃይሎች እንዴት ያዩታል?

ሁለተኛ፡– በኹለንተናዊ (ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ) ጉዳዮች ሀገራችን ዛሬ ምን ላይ ነች? የተለያዩ ኃይሎች ይህን ነባራዊ ኹነት እንዴት ያዩታል?

ሶስተኛ፡– በኹለንተናዊ (ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ) ጉዳዮች ሀገራችን ነገ ምን ላይ እንድትኾን እንሻለን?

ይህም የዕይታ፣ የትንታኔ፣ የትርጓሜ፣ የአቀማመጥ፣ የግንዛቤ – – – ልዩነቶች እንደተጠበቁ ኾነው ቢያንስ መሠረታዊ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ ያደረግነው ሀሳብ ባይኖር እንኳ በጋራ ለመወያየትና ለመረዳዳት የሚያስችል ምቹ ኹኔታ ከመፍጠር፣ ከመጠቀምና ከማስተናገድ አንጻር ምን ላይ ነን? የሚለውን መመልከት እጅግ አስፈላጊ ይኾናል፡፡

ሀገራችንን ለረዥም ዓመታት ወደ ኃላ ካስቀሯት ዐቢይ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው በጋራ ካላሰባችሁ – የዚህም መገለጫ ‘እንደኔ ካላሰባችሁ’፣ ‘እኔ እንደምለው ካልኾናችሁ’፣ ‘የኔ መንገድ ብቻ’፣ ‘ያለኔ ሌላው መንገድ ኹሉ መጥፎ ነው!’ – – –  የሚል የገዥዎቻችንና ገዥ ለመኾን የሚሹ ኃይሎች ብቻ ሳይኾን ተገዥዎችም ብንኾን መስማት የምንፈልገውን ብቻ የመስማት፣ ማንበብ የምንሻውን ብቻ የማንበብ፣ የኛ ጀግኖችና የምናደንቃቸው – በአመክንዮና በዕሳቤ ላይ ተመርኩዘን ሳይኾን በአብዛኛው እኛን የሚመስሉንና መምሰል የምንሻቸው፣ የውስጣችንን የሚነግሩን – እሱን ስለነገሩን የምንደሰትባቸው መኾናቸው፡ ምንም እንኳ የሰው ልጅ ባሕሪና ጠባይ ለዚህ ተጋላጭ መኾኑ ዕውነት (Truth) እና እውነታ (Reality) መኾኑን ባንዘነጋ ምክንያታዊነትና ዲሞክራሲያዊ ዕሴትን ባሕል ከማድረግ አንጻር ተቃርኖው ጎልቶ ይታያል፡፡

ስለኾነም ዛሬ ኹላችን ልንጠይቅ የሚገባቸው ወሳኝ ጥያቄዎች፡-

1ኛ. በተጨባጭ ሀገራችን ምን ላይ ነች? ከማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኹለንተናዊ መለኪያዎች አንጻር ምን ላይ ነች?

2ኛ. በተጨባጭ በሀገራችን አኹን ምን እየተከናወነ ነው?

3ኛ. የተለያዩ ኃይሎች ፍላጎት እንዴት ሊስተናገድ ይችላል? ዕውን በተጨባጭ ፍላጎቶች ትርጉም ባለው መንገድ ተለይተው ተቀምጠዋል? የተቀመጡትንስ ማስተናገድ የሚያስችል የንቃተ ህሊናና ምቹ ኹኔታ አለን? መፍጠርስ ይቻላል?

4ኛ. እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች ነገ እና ከነገ ወዲያ ከሚኖራቸው ተጽዕኖ በመነሣት ተቋማዊና የተቋማዊነት ሂደታቸው – ዘላቂና አስተማማኝ ሊኾኑ ይችላሉን?

5ና. ዕውን ለውጥ እንደሚያስፈልግ ኹላችን ላይ እንዳለው ባሕሪያዊና ጠባያዊ የለውጥ ፍላጎት – እንደግለሰብ፣ እንደቡድንና እንደተቋም ራሳችንን ትርጉም ባለው መንገድ በእምነት (በአስተሳሰብና አመለካከት)፣ በእውቀት (በስልትና ስትራቴጂ) እና በድርጊት (በተግባር) – – – – ለውጠናልን?

በጥቅሉ ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማስተዋል፣ ትዕግስትና ጥበብ በእጅጉ በሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ትገኛለች፡፡ ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ልዩነትን ማስተናገድ የሚያስችል ልቦና ያላቸው ገዥዎችም ኾነ ተገዥዎች ያስፈልጓታል፡፡ ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ከትላንት ይልቅ ነገን ማዕከል አድርገው ዛሬ ላይ የሚንቀሳቀሱ ትላንትን ደግሞ ከነገ አንጻር የሚመለከቱ አስተዋዮች ያስፈልጓታል፡፡

ከኹሉ በላይ ስሜት (Emotion)፣ አስተያየት (Opinion)፣ ሀሳብ (Idea)፣ ዕሳቤ (Thought) እና ርዕዮት /ርዕዮተ ዓለም/ (Ideology) በአንድ ሀገር ኹለንተናዊ ያለፈ፣ ያለና የሚኖር እንቅስቃሴ ውስጥ የማይነጣጠል፣ ተያያዥና ተደጋጋፊ ሚና ያላቸው ቢኾንም በስሜት (Emotion) እና በአስተያየት (Opinion) የምትገዛ ሀገር ወደ ኃላ እንደምታመራ – አርቴፊሻልና የማስመሰል ስራዎች እንደሚበራከቱባት! ሴረኛነት እንደጥበብ ተቆጥሮ እንደሚከበርባት! ከኹሉ ጭራ እንደምትኾን! ዘወትር ለተከታይነት እንደምትሰራ! ባርነት እንደነጻነት ባደባባይ የሚሰበክባት እንደምትኾን!!!

በአንጻሩ ትርጉም ባለውና ዘመኑን በዋጀ ሀሳብ (Idea) ፣ ዕሳቤ (Thought) እና ርዕዮት /ርዕዮተ ዓለም/ (Ideology) ከርዕዮተ ሀገር ጋር የምትመራ ሀገር ወደ ፊት እንደምትጓዝ! – መሠረታዊ ለውጥም እንደምታመጣ! – ተወዳዳሪ እንደምትኾን! – ለቀዳሚነትም እንደምትሰራ ቆሞ ማስተዋል – አርቆ ማሰብ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው፡፡

የሰው ልጅ ሀሳብን ጨምሮም ኾነ ቀንሶ ሀሳብን የጋራ ማድረግ እንጂ በምንም ተዓምር በፍጹም በጋራ ማሰብ አይችልምና!!! እንደሀገር በጋራ ልንቆምለት የምንሻው ትርጉም ያለውና ዘመኑን የዋጀ ሀሳብ (Idea) ፣ ዕሳቤ (Thought) እና ርዕዮት /ርዕዮተ ዓለም/ (Ideology) ምን አለን? በምንስ ይገለጻል?፤ “ሀሳብን የጋራ ማድረግ እንጂ በጋራ ማሰብ ፈጽሞ አይቻልም!!!” ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

This Post Has One Comment

  1. selam

    really a very powerful article – wow!!!

Leave a Reply