ሀብት የሚያሸሹ ግለሰቦችን ለመቅጣት የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑ ተነገረ

የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሀብት ከአገር የሚያሸሹ ግለሰቦች ላይ አስፈላጊውን ቅጣት ለመጣል የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ይህን የገለጸው 15ኛው የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች ማኅበር ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በተካሄደ መድረክ ሲሆን፣ ከሁሉም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በአገር ውስጥ ያለውን የሙስና ወንጀል ትግል እንደሚመራ የገለጹት የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ፣ ‹‹ከአገር የሚሸሸውን ሀብት ለመቆጣጠር ሥራዎች መጠናከር ይገባቸዋል፡፡ ለዚህም ተገቢውን ቅጣት ለመጣል የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አዋጁ ያካተታቸው ዝርዝር ጉዳዮች ወደፊት ይፋ እንደሚደረጉ የገለጹት ዶ/ር ሳሙኤል፣ የፍትሕ ሚኒስቴርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን አንድ ላይ በመሆን በዋናነት አዋጁን እያዘጋጁ መሆናቸውንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም እየተሳተፉበት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር፣ ፖሊስ፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎትና ሌሎችም ተቋማት በጋራ በመሆን የሚሸሹ ሀብቶችን ለመከላከል የጋራ ኮሚቴ መቋቋሙንም አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀረ ሙስና ስምምነትና የአፍሪካ ኅብረት የፀረ ሙስና መዋጊያ ስምምነትን ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን፣ ከዚህ ባለፈም ወንጀሉን ለመከላከል በቀጣናው ውስጥ ያሉ አገሮች በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡

ከአገር የሸሸ ሀብትን ከማስመለስ አኳያ አገሪቱ ያላት ቁጥጥር ደካማ በመሆኑ ድርጊቱ መበራከቱን፣ የፍትሕ ዘርፉ ከተጠናከረ ግን በርካታ የሀብት ማስመለስ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡ ይህም በብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ እየታየ ያለው አንደኛው ጉዳይ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

(ሪፖርተር)

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply