“ሀገርን ማን ይምራ?” ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ

(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና

የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

በአንድ ወቅት በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሶስት ሰዎች ስለሀገራቸው ነባራዊ ኹኔታ እጅጉን ቢጨነቁና ቢጠባቸው እርስ በራስ ሲወያዩ የውይይታቸው ሂደት ሄዶ ሄዶ ጥያቄዎችን እንዲያነሡ ግድ አላቸው፡፡ “ሀገርን ማን ይምራ?”፤ “ሀገር በማን ብትመራ ውጤታማ ትኾናለች?”፤ “እንዴትስ ብትመራ ዘላቂና አስተማማኝነት ያለው ኹለንተናዊ ስኬትን ታመጣለች?” የሚሉ ዋነኛ ጥያቄዎችን አነሡ፡፡

እነዚህ ሶስት ሰዎች በዕድሜ – ወጣት፣ ጎልማሳና አረጋዊ ሲኾኑ የከተማ ነዋሪዎችና ስለወቅታዊ ነባራዊ የሀገራቸው ነባራዊ ኹኔታ በቂ ግንዛቤ ያላቸው ናቸው፡፡

በውይይታቸው ወጣቱ “እኔ ሀገር መመራት ያለባት በወጣት ነው፡፡ ምክንያቱም የሀገራችንን አብዛኛውን ቁጥር የሚይዝው ወጣቱ ነው፡፡ – -” ገና ሳይጨርስ ጎልማሳው አቋርጦት “መሪ እንጂ አማሪ እኮ አላልንም፡፡ ደሞ – – -” ወጣቱ እየተናደደ አቋርጦት “ኸረ ባክህ ዲሞክራሲ ማለት እኮ የአብዝሃ አመራር ነው፡፡ እኛ ደሞ ብዙ ነን፡፡”

ጎልማሳው “ኸረ ውሸት!! የፈጣሪ ያለህ! ዲሞክራሲ የአብዝሃ ፍላጎት ይመራል – የጥቂቶች መብት ይከበራል፤ የአብዝሃ ሃሳብ ገዥ ይኾናል – የጥቂቶች ሃሳብ ይከበራል፤ የአብዝሃ ድጋፍ ያገኘ ይመራል – የጥቂቶች ነጻነት ይከበራል፤ እንጂ በፍጹም ብዛት ያለው ይመራል አይልም፡፡ ደሞ እኮ – እኛም ወጣት ነበርን፡፡ መቼ መራን? እናንተም በጊዜ ሂደት ከወጣትነት ትርቃላችሁና ከዚህ ፍሩሽ ሀሳብ ብትወጣ ይሻላል፡፡”

ወጣቱ ለጥቂት ደቂቃ ዝም ካለ በኃላ “እሺ – ባልከው ሀሳብ ተስማማሁ!!! ነገር ግን ወጣቱ ጉልበት፣ ዕውቀት እንዲሁም የመስራት ትልቅ ፍላጎት ስላለውና የአብዝሃን ፍላጎት ስለሚረዳ ሀገር መመራት ያለበት በወጣት ነው፡፡”

ጎልማሳው እየሳቀ “ወጣቱ ልምድ የለውም፡፡ አብዛኛው ወጣት ገና በትምህርት ዓለም ላይ ያለ ነው፡፡ የተመረቁትም ቢኾኑ ገና ሥራ መጀመራቸው ነው፡፡ ደሞ አብዛኛዎቹ  ከመዝናናት፣ ስለጾታዊ ፍቅር ከማሰብ፣ ገና ራሳቸውን እንኳ ያልቻሉ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ጥገኛ የጥገኛ ናቸው፡፡”

ወጣቱ “እና ማን ይምራ?”

ጎልማሳው “ጎልማሳው ነዋ!!!”

ወጣቱ “ኸረ ባክህ! ጎልማሳው አስመሳይና ዳተኛ ነው!!!”

ጎልማሳው “እንዴት?”

ወጣቱ “ይኸው አብዛኛዎቻችሁ ስለራሳችሁ፣ ስለቤተሰቦቻችሁ እንጂ ስለሀገር ለማሰብ ጊዜ የላችሁም፡፡ አንተ ራስህ ለስሙ የተማርከው ትምህርት ስለሕዝብ ኾኖ የምትሰራው የግል ድርጅት ውስጥ ነው፡፡ ደሞ ትዳርና ልጆች ስለሚይዛችሁ መስዋዕትነት አትከፍሉም፡፡”

ጎልማሳው አንገቱን ደፍቶ ዝም አለ፡፡ እውነታውን በራሱ ሕይወት የተመለከተው በመኾኑ ለመመለስ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ዝምታን መረጠ፡፡፡

ዘወትር እንደለመዱት እጅግ በጭቅጭቅ፣ በእልህና በአልሸነፍ ባይነት ሲከራከሩ ቢቆዩም ከላይ የተነሡትን ጥያቄዎች ካነሡ ወዲህ መቀዛቀዝ አለ፡፡ እስካሁን አንዳች ያልተነፈሱትን አረጋዊ ወጣቱና ጎልማሳው ሲመለከቱ እሳቸውን እንደሚጠብቁ የገባቸው አረጋዊ ጉሮሯቸውን አጽድተው “ጥያቄው ከባድ ነው፡፡ ለኔ ለራስህ አደላህ እንዳትሉኝ እንጂ ሀገር በአረጋዊ ብትመራ መልካም ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ህጻንነትንም፣ ታዳጊነትን፣ ወጣትነትንም ኾነ ጎልማሳነትን በደንብ ስለሚያውቁትና ስለሚረዱት አረጋውያን ቢመሩ መልካም ይመስለኛል፡፡”

ጎልማሳው “እኔ ግን አረጋውያን ለለውጥ ብዙም አይተጉም፡፡ ራሳቸውን ከነገ ይልቅ ከትላንት ጋር ስለሚያነጻጽሩ፣ ዘመኑን ለመዋጀት ዳተኞች ስለኾኑ ለውጥ ያመጣሉ ብዪ አላስብም፡፡”

ወጣቱ “እኔም እንደዛ ነው የማስበው፡፡ ብዙ ጊዜ ከአረጋዊ ጋር ቁጭ ስል የሚያወሩት ወሬ ኹሉ ታሪክ – ታሪክ – ታሪክ ነው፡፡ ብዙም አዲስ ነገር ለማምጣት፣ ለመፍጠርና ከጊዜው ጋር በፍጥነት መሮጥ አይችሉም፡፡”

ጎልማሳው “እውነት ነው፡፡ አረጋውያን ብዙም ለነገሮች ስለማይጓጉ መሪነት ከሚጠይቀው ትዕግስት፣ ዕውቀት፣ ልምድና ጥበብ ያላቸው ቢኾንም ከዛ በተጨማሪነት ወሳኝ ወቅታዊነት፣ ከታሪክ አውጊነት ይልቅ ታሪክ የመስራት ቁጭትና ትጋት፣ ኹነትን የማንበብና ራስን በእጅጉ ከማድመጥ ባሻገር ሌላውን የማድመጥ ችግር አለባቸው፡፡ እኔ ብቻ ልክ ነኝ! እኛ ያልነው ካልኾነ! የማለትና ሌላውንም ይንቃሉ፡፡ ደሞ ለራሳቸው የተጋነነ ምስል አላቸው፡፡”

ወጣቱ “በጣም! ብዙ ጊዜ እነሱ በሚሉትና መሬት ላይ ባለው ጥሬ ሃቅ መሐከል እጅግ የሰፋ ልዩነት አለ፡፡”

አዛውንቱ “ታድያ ሀገራችንን ማን ይምራ? ወጣቱ ስሜታዊና ልምድ አልባ ነው፡፡ ጎልማሳው ደሞ በኑሮ ተወጥሮና የኑሮ እስረኛ ነው፡፡ አረጋዊ ግን በብዙ መለኪያዎች የተሻለ ነው፡፡ ዕውቀት፣ ልምድና ትዕግስት አለው፡፡ ደሞ ከኹሉ በላይ ኔትወርክ አለው፡፡” ሲሉ መልስ የሚሰጥ ጠፋ፡፡ ዝም ዝም ኾነ፡፡

እንደሌላው ጊዜ ውይይታቸው ሊረዝም አልቻለም፡፡ ልዩነታቸው ጎራ ለይቶ የግድ ይሄ መኾን አለበት ለማለት ሳያስችላቸው ቀረ፡፡ ረዥም ሰዓት ወስደው ተራ በተራ ሀሳባቸውን ቢገልጹም ዞሮ ዞሮ ቀድመው ካነሡት የተለየ አልኾን ሲላቸው ወጣቱ “እኛ መስማማት አልቻልንም፡፡ ለምን ታላቁ መምህር ጋር ሄደን አንጠይቃቸውም?” ሲል በሀሳቡ ተስማምተው – ተነሡ፡፡

በመንገድ ሲሄዱ በየራሳቸው ሀሳብ ነጉደው አረጋዊው ከመሐከል ጎልማሳው በቀኝ – ወጣቱ ደግሞ በግራ ኾነው በፍጥነት ሲራመዱ ለተመለከታቸው እጅግ ለአስቸኳይ ጉዳይ የሚፈጥኑ ይመስላሉ፡፡ አረማመዳቸው የኾነ የቸኮሉበት ጉዳይ እንዳለ በግልጽ ያሳብቃል፡፡

እጅግ የታወቁትና የሚፈሩት መምህር ብዙ ጊዜያቸውን በማንበብና በማስተማር የሚያሳልፉ ታላቅ በሕብረተሰቡ ዘንድ የሚከበሩ በገዥዎች ደግሞ በቀጥተኛና በደፋር አንደበታቸው የተነሣ የሚጠሉና የሚፈሩ ኹለገብ አዋቂ ቢኾኑም በዋናነት የሃይማኖትና የፍልስፍና ሊቅ ናቸው፡፡ የዕውቀትና ጥበብ ጉዳይ ከተነሣ እሳቸው በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ ይጠራሉ፡፡ ይገኛሉ፡፡ እሳቸው ያሉት “እንዲህ እኮ አሉ” ተብሎ በብዙዎች ዘንድ ይጠቀሳል፡፡

ታላቁ ምሁር ዘንድ ሲደርሱ መምህር ከተማሪዎቻቸው ጋር ቁጭ ብለው ስለሰው ልጅ ሕይወት ምንነትና ግንኙነት እየተነተኑ “- – – ሰው ከራሱ፣ ከፈጣሪው፣ ከመሰሉ፣ ከአካባቢውና ከተፈጥሮው ጋር የማይቋረጥ ግንኙነት አለው፡፡ ይህ ጤናማ፣ ሰላማዊ፣ ፍቅር፣ ትዕግስትና ትጋት የተሞላበት እንደኾነ የስኬት ኑሮ ይኖራል፡፡ ካልኾነ የመከራና የስቃይ ኑሮና አኗኗር ይኖራል፡፡ ያኗኑራል፡፡ – – ” ያስረዳሉ፡፡ ትምህርታቸውንም ሲጨርሱ በጸሎት ዘግተው ተማሪዎቻቸው ጉልበት እየሳሙ ሲሄዱ ሶስቱ ሰዎች ቀርበው በመሳለም የአክብሮት ሰላምታ ሰጥተው አጠገባቸው ቁጭ አሉ፡፡

ሰላምታ ተለዋውጠው ዝም ዝም ሲባባሉ ወጣቱ “መምህር የመጣነው ጥያቄ ለመጠየቅ ነው፡፡”

መምህር ”መልካም – ስለምን” አሉ ፊታቸው እንደኹል ጊዜው በፈገግታና በፍቅር ተሞልቶ፡፡ ወጣቱ “ስለሀገር ጉዳይ ስናነሣ ሶስት ዋነኛ ጥያቄ አነሣን፡፡ 1ኛ. ሀገርን ማን ይምራ? 2ኛ. ሀገር በማን ብትመራ ውጤታማ ትኾናለች? 3ኛ. እንዴትስ ብትመራ በኹለንተናዊ መንገድ ውጤታማ ትኾናለች? የሚሉ ናቸው፡፡ እኛ መስማማት ስላልቻልን እርሶን ለመጠየቅ መጣን፡፡”

መምህር “መልካም – ጎበዞች! ሰው በዚህ ዘመን ስለራሱና ስለራሱ ብቻ በሚያስብበት ጊዜ ቦታ ሰጥታችሁ፣ ጉልበታችሁንና ስሜታችሁን ስለሀገር ጉዳይ ሰጥታችሁ መወያየታችሁና ረዥም ርቀት ተጉዛችሁ መምጣታችሁ – ዕውነት የታላቅነታችሁ መገለጫ ነው፡፡ ለመኾኑ እናንተ ምን መለሳችሁ?”

ሶስቱም እርስ በራስ ተያይተው፡፡ አንተ – አንተ ሲባባሉ ቆይተው፡፡ አረጋዊው ጀምረው – ጎልማሳው በመቀጠል በስተመጨረሻ ወጣቱ በዝርዝር የተነጋገሩበትን በየራሳቸው አንደበት በስፋት ሀሳባቸውን ገለጹ፡፡

በጥሞና ሲያደምጡና በአዎንታ ራሳቸውን እየነቀነቁ የቆዩት መምህር “ሀገር በምንድነው

የምትመራው? በሀሳብ ወይስ በዕድሜ?”

ሶስቱም ደንግጠው በአንድነት “በሀሳብ! በሀሳብ! በሀሳብ!” አሉ፡፡

መምህር “ስለኾነም የተደራጀ፣ የጠራና ዘመኑን የዋጀ ሀሳብ ያለው ሀገርን ቢመራ መልካምና ውጤታማ ያደርጋታል፡፡ ይህም ወጣቱ፣ ጎልማሳው አልያም አረጋዊው ጋር ሊኖር ይችላል፡፡ ይህንንም የያዘና በባለቤትነት መያዝ የሚችል የመሪነቱን ቦታ ሊያገኝ ይገባል፡፡” ብለው ዝም ሲሉ ሶስቱም በመልሳቸው ተደንቀው፡፡ በነሱ አለማስተዋል አፍረው – ዝም አሉ፡፡

መምህር ከከፍታው ቤታቸው ሩቅ ያለ አድማስ ላይ አተኩረው እየተመለከቱ “ወዳጆቼ ሀገራችን ዛሬ መሪ ብቻ ሳይኾን ጥሩ ተመሪም አጥታለች፡፡ የሰው ልጅ ታሪክን ስንመለከት – መሪም ተመሪም የሌለበት፣ ገዢነት በተመሪነት ላይ ለመሠልጠን የተጋበት፣ ገዥነት የሠለጠነበት፣ ገዥነት ወደ መሪነት በተመሪዎች ትግል ያደገበት፣ ተመሪነት በዝቅጠት የተሞላበትና ተመሪና መሪ ድንበር አልባ የኾነበት፣ ተመሪ መሪን መምራት የቻለበት – መሪ በራሱና በሚያስፈልገው ሳይኾን በተመሪዎች ፍላጎት የተመራበት፣ ጭራሽ ዛሬ መሪነትም ኾነ ተመሪነት ዝቅጠት ውስጥ ያለበት ዘመን ነው፡፡” አሉ፡፡

ከረዥም ጸጥታ በኃላ ወጣቱ “መምህር መፍትሔው ምንድነው?”

መምህር “አይ ልጄ – መፍትሔ እንዲሁ በቀላሉ የሚነገር ቢኾን ገና ድሮ መፍትሔ ይኖር ነበር፡፡ ትልቁ ስህተታችን እጅግ ሰፊ፣ ውስብስብና ተለዋዋጭ ኹለንተናዊ ለኾነው የሀገራችን ችግር እንደቀላል መፍትሔው ይሄ ነው! ብለን መግለጻችን ነው፡፡ የሀገር ችግር እንደምናወራው፣ እንደምንጽፈው፣ እንደቃል ምንገባው፣ እንደሚነገረውና እንደሚባለው ቀላል አይደለምና የሀገር መሪነት ከቀላል ሰዎች እጅ መውጣት፤ እንዲሁም በተመረጡ አካላት በኩል ሰፊ ኹለንተናዊ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡” አሉ፡፡

በታላቅ ተመስጦ ሲያደምጡ የቆዩት ሶስቱም የተመካከሩ ይመስል በደስታ፣ ፊታቸው ፈክቶ፣ ውስጣቸው ሰላም አግኝቶ በአክብሮት ተነሥተው ሲቆሙ፡፡ መምህር በእርጋታ ከወንበራቸው ተነሥተው እያሳለሙ – በእቅፋቸው ውስጥ አስገብተው በፍቅር ሳሟቸው፡፡ ሶስቱም በአንድነት አመስግነው ሲራመዱ

መምህር ”ወዳጆቼ ሀገር የህጻናት፣ የታዳጊም፣ የወጣትም፣ የጎልማሳና የአረጋዊ ነች፡፡ አንዱን ያጎደለች እንደኾነ ጎዶሎ ትኾናለች፡፡ ደሞ እንዳትረሱ ሀገራችን የኹላችንም ናት!!! እንዳትረሱ ሀገራችን የኹላችንም ናት!!! በዕድሜ ብቻ ሳይኾን በግብርና በምግባርም ወጣት ሳሉ እንደአረጋዊና ጎልማሳ የሚያስተውሉ፤ ወጣት ሳሉ የህጻን፣ ጎልማሳ ሳሉ እንደህጻን፣ አረጋዊ ሳሉ የህጻንነትን ጠባይ የያዘውም ጭምር፤ የደጎቹ ብቻ ሳይኾን የክፉዎቹም፤ የእውነተኞቹ ብቻ ሳይኾን የሀሰተኞቹም፤ የሀብታሞቹ ብቻ ሳይኾን የድሃዎቹም፤ የየዋህና ቅኖቹ ብቻ ሳይኾን የመሰሪዎቹና የአስመሳዪቹም፤ የባለራዕዮች ብቻ ሳይኾን የዓላማ ቢሶችም፤ የጌቶች ብቻ ሳይኾን የአሽከርና ባሪያዎችም ጭምር ናት!!! በግብር የሚመሳሰሉ በአንድነት ያለ-ሌላው ተመሳሳይ ብቻ የሚኖርበት ሀገር ከሕይወት ህልፈት በኃላ ነው፡፡” ሲሉ ሶስቱም በአዎንታ ራሳቸውን እየነቀነቁ በታላቅ አክብሮት ዝቅ ብለው የስንብት ሰላምታ ሰጥተው ወደ መውጫው አመሩ፡፡

ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

Leave a Reply