ሁለት የአሶሴትድ ፕሬስ ጋዜጠኞች በዋስትና ከእስር እንዲወጡ ተፈቀደላቸው

በሃሚድ አወል

የአሶሴትድ ፕሬስ ዘጋቢ አሚር አማን እና የካሜራ ባለሙያ ቶማስ እንግዳ እያንዳንዳቸው በ60 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተለቅቀው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ በፍርድ ቤት ተወሰነላቸው። የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 20 ውሳኔውን ያስተላለፈው “ምርመራው ካለበት አልተንቀሳቀሰም” በሚል ነው። 

ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ቀጠሮ ይዞ የነበረው፤ የፌደራል ፖሊስ በሁለቱ ጋዜጠኞች ላይ እያደረገው ላለው ምርመራ በፈቀደው 11 ተጨማሪ ቀናት የተከናወኑ ተግባራትን ለማድመጥ ነበር። ፖሊስ በተፈቀዱለት ቀናት የሁለቱን ተጠርጣሪዎች እና የአንድ ምስክርን ቃል መቀበሉን ለፍርድ ቤት አስረድቷል። 

በጽህፈት ቤት በኩል በተከናወነው የዛሬ የችሎት ውሎ ፖሊስን ወክለው የተገኙት መርማሪ፤ “የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ያስፈልገናል” በሚልም ተጨማሪ 14 ቀናት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። ጋዜጠኞቹ የተጠረጠሩበትን ወንጀል “ልዩ ባህሪ ከግምት ውስጥ በማስገባት” ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን ሲፈቅድ መቆየቱን ያስታወሰው ፍርድ ቤቱ፤ ሆኖም የምርመራው ሂደት ከዚህ በፊት ከነበረበት ለውጥ አለማሳየቱን በመግለጽ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውድቅ አድርጓል።

ይህን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ በጋዜጠኞች ጠበቃ በኩል የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ መቀበል፤ ተጠርጣሪዎቹ እያንዳንዳቸው የ60 ሺህ ብር የዋስትና ገንዘብ በማስያዝ ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም ጋዜጠኞቹ ከአገር እንዳይወጡ የጉዞ እገዳም አስተላልፎባቸዋል።  

ለአራተኛ ጊዜ የተካሄደውን የዛሬውን የፍርድ ቤት ውሎ፤ የጋዜጠኞቹ የትዳር አጋሮችን ጨምሮ አምስት የቤተሰብ አባላቶቻቸው በጽህፈት ቤት በአካል ተገኝተው ተከታትለዋል። ልትወልድ ሁለት ሳምንት የቀራት የጋዜጠኛ አሚር ነፍሰጡር ባለቤት፤ ጋዜጠኞቹ በዋስትና እንዲወጡ በፍርድ ቤት ከተወሰነ በኋላ ደስታዋን በእንባ ስትገልጽ ታይታለች። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

The post ሁለት የአሶሴትድ ፕሬስ ጋዜጠኞች በዋስትና ከእስር እንዲወጡ ተፈቀደላቸው appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply