ሃማስ ሁለት አሜሪካዊያንን ለቀቀ

https://gdb.voanews.com/0bda96a2-b164-484f-8870-dc3c92b41d3a_cx0_cy11_cw0_w800_h450.jpg

ሃማስ ካገታቸው ሲቪሎች ሁለት አሜሪካዊያንን ለቅቄአለሁ ማለቱን ሮይተርስ ዘገበ።

በዘገባው መሠረት ቻነል 23 ኒውስ የሚባል የእሥራዔል ዜና አውታርም ሁለቱ ሰዎች መለቀቃቸውን አረጋግጧል።

ሁለቱ አሜሪካዊያን እናትና ልጅ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን ሃማስ ሰዎቹን የለቀቃቸው “በሰብዓዊነት ምክንያቶች” እና እሥራዔል ጋዛ ውስጥ እያካሄደች ላለችው ጦርነት “ጠንካራ ድጋፍ እየሰጡ ላሉት ፕሬዚዳን ጆ ባይደን መልዕክት ለማስተላለፍ” እንደሆነ ማስታወቁን ዘገባው ጠቁሟል።

ከሃማስ እገታ የተለቀቁት አሜሪካዊያን አሁን በዓለምአቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ እጅ መሆናቸውን ቅርበት ያለው ምንጭ እንደነገረው ሮይተርስ ገልጿል።

ከሃማስ ቃል አቀባይ አቡ ኡባይዳ እንደወጣ የተዘገበ መግለጫ “ታጋቾቹ የተለቀቁት ለካታር የማደራደር ጥረት ምላሽ ለመስጠት፣ ስለ ሰብዕና ሲሉና ለአሜሪካና ለዓለም ህዝብም ባይደንና ‘ፋሽስት’ – ሲል የጠራው – አስተዳደራቸው የሚናገሩት ሃስትና መሠረተ ቢስ መሆኑን ለማሳየት ነው” እንደሚል የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

ከታጋቾቹ ብዙዎቹ በህይወት ያሉ መሆኑን የእሥራዔል ጦር ዛሬ ረፋድ ላይ ያስታወቀ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ አማካሪ ማርክ ራጌቭም ይህንኑ ለሲኤንኤን አረጋግጠዋል።

ጋዛ ሰርጥ ውስጥ 2.3 ሚሊየን ሰው ያለ ምግብ፣ ያለመድኃኒትና ያለነዳጅ በሙሉ ከበባና መነጠል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ሰርጡን እያስተዳደረ ያለውን ሃማስን ሙሉ በሙሉ እደመስሳለሁ የምትለው እሥራዔል እጅግ የበረታ ድብደባ እያካሄደች እንደምትገኝ ተዘግቧል።

ጋዛ ውስጥ እስካሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ ህፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 4 ሺህ 137 ፍልስጥዔማዊያን መገደላቸውንና 13 ሺህ ሰው መቁሰሉን የፍልጥዔምን የጤና ሚኒስቴር የጠቀሰው ሮይተርስ አክሎ ዘግቧል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ያለመጠለያ መቅረታቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply