ህብረት ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር ለትናንሽ ንግዶች ማበረታቻ ሊያደርግ ነዉ፡፡ህብረት ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በጋራ በመተባበር ለትናንሽ ንግዶች ማበረታቻ ለማድረግ የኢ-ኮሜ…

ህብረት ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር ለትናንሽ ንግዶች ማበረታቻ ሊያደርግ ነዉ፡፡

ህብረት ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በጋራ በመተባበር ለትናንሽ ንግዶች ማበረታቻ ለማድረግ የኢ-ኮሜርስ የክፍያ መፍትሄ ይዞ መምጣቱን ገልጿል፡፡

በማስተር ካርድ የክፍያ ጌትዌይ የሚሰራው “ሕብር ኢ-ኮሜርስ” በኢትዮጵያ የሚገኙ የንግድ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን በኦንላይን ለዓለም አቀፍ ደንበኞች እንዲሸጡና አዳዲስ ደንበኞችንም እንዲያገኙ የሚያስችል ነዉ፡፡

“ሕብር ኢ-ኮሜርስ” በኢትዮጵያ የሚገኙ የንግድ ተቋማትና ነጋዴዎች በማስተር ካርድና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ካርዶች ክፍያ ከኢትዮጵያ ውጭ ካሉ ደንበኞች መቀበል እንዲችሉ የሚረዳ መሆኑም ነዉ የተገለጸዉ፡፡

ህብር ኢ-ኮሜርስ ሻጮች በኦንላይን በሚገበያዩበት ወቅት ከዚህ በፊት የነበረዉን ዓይነት ረጅም ዉስብስብ ሂደት ዉሰጥ ሳይገቡ በዉጭ ሀገራት ገንዘብ ክፍያ እንዲከፈላቸዉ የሚያደርግ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የክፍያ ስርዓቱ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲያድግም አስተዋፅኦ ያደርጋል ነው የተባለው፡፡

የሕብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ከበደ÷ የሕብር ኢ-ኮሜርስ ተግባራዊነት ከባንኩ ስትራቴጂ 2030 ጋር የሚጣጣምና በዓለም አቀፍ የክፍያ ስርዓት ውስጥ በካርድ ባንኪንግ ለሚገበያየው ደንበኛ እና ለነጋዴው ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡

የማስተር ካርድ የምስራቅ አፍሪካ ካንትሪ ማኔጀር ሺኸርየር ዓሊ በበኩላቸው ÷“ሕብር ኢ-ኮሜርስ” ነጋዴዎች ደህንነቱ የተጠበቀ የኦንላይን የክፍያ ጌትዌይ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችላቸውና ክፍያቸውን መቀበል፣ የደንበኞቻቸውን ቁጥርና ገቢያቸውን ማሳደግ እንደሚያስችላቸው ጠቁመዋል፡፡

በሀገራችን በባንክ ኢንዱስትሪዉ ረገድ የመጀመሪያዉ እንደሆነ የተነገረለት ይህ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አገልግሎት የሀገር ዉስጥ ንግዶች አዳዲስ ገበያዎችን እንዲያገኙ እንዲሁም ለሀገርም የሚገባዉን ገቢ እንዲያመጡ የሚያደርጋቸዉ ነዉ ተብሏል፡፡

በእስከዳር ግርማ

ህዳር 03 ቀን 2015 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply