ህወሀት በራያ አላማጣ እና ራያ አዘቦ ነዋሪዎች ላይ “አሀዳዊ መንግስት ሊወረን ስለሆነ ለውትድርና ልጃችሁን ስጡን” በማለት ማህበረሰቡ ተረጋግቶ እንዳይኖር እያስቸገረ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ተናገ…

ህወሀት በራያ አላማጣ እና ራያ አዘቦ ነዋሪዎች ላይ “አሀዳዊ መንግስት ሊወረን ስለሆነ ለውትድርና ልጃችሁን ስጡን” በማለት ማህበረሰቡ ተረጋግቶ እንዳይኖር እያስቸገረ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ተናገሩ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 21 ቀን 2013 ዓ.ም… አዲስ አበባ ሸዋ ከራያ ለአማራ ሚዲያ ማዕከል የደረሰው መረጃ እንዳመለከተው ህወሀት/ትህነግ “አሀዳዊ መንግስት ሊወረን ነው” በሚል ከአማራ በሀይልና በፖለቲካዊ ሸፍጥ ወደ ትግራይ ባካለላቸው የራያ አላማጣ እና ራያ አዘቦ አካባቢዎች ቅስቀሳውን አጠናክሮ መቀጠሉን ያመለክታል። የትህነግ አመራሮች ካሁን ቀደም”ማዕከላዊ መንግስት ሊወረን ስለሆነ በሚል ውትድርና የሚሰለጥን አንዳንድ ልጅ ስጡን፤ ወዳችሁና ፈቅዳችሁ የማትሰጡን ከሆነ ግን እኛ አስገድደን አፍሰን እንወስዳለን” ሲሉ የራያ አላማጣ አካባቢ ማህበረሰብን ሰብስበው መናገራቸውን ምንጫችን አውስቷል። በአብዛኛው የአማራ ተወላጆች የሚገኙበት የራያ አላማጣና የራያ አዘቦ አካባቢ የፌደራል መንግስት ሊወረን ነው በሚል ጫና እየፈጠረ የሚገኘውን የትህነግ ፕሮፖጋንዳ አልተቀበለውም ያለው የአካባቢው ነዋሪ ይህን ተከትሎም ትህነግ ከሰሞኑ ሌላ ስትራቴጅ ቀይሯል ነው ያለው። አገዛዙ ለኮብል ስቶን እና ለጥቃቅን ስልጠና በሚል ስራ አጥ ወጣቶችን ስጡን በማለት አግ ወደተባለ ማሰልጠኛ መውሰድ ጀምሯል ሲልም አክሏል። ይሁን እንጅ ስልጠናው የእጅ አዙር ነው፤ ሆነተብሎ ለወታደራዊ ስልጠና ነው ሲሉ ነዋሪዎች ገልፀዋል። ከወቅቱ አንጻር ለልማት ስልጠና በሚል ስም ወጣቶችን ከቤተሰብ ነጥለው ከወሰዱ በኋላ በአስገዳጅነት የውትድርና ስልጠና እንደሚሰጧቸው እየተነገረ ስለመሆኑም ተገልጧል። በተያያዘም ወደ አካባቢው ለእረፍት የመጡ የትግራይ የልዩ ሀይል አባላትንም እረፍታቸውን ሳይጨርሱ ሰልጣኞች እየመጡ ስለሆነ በአስቸኳይ ግቡ የሚል የስልክ ጥሪ እንደደረሳቸው መረጃ ደርሶናል ብለዋል የመረጃ ምንጮቻችን። ከራያ አላማጣና ራያ አዘቦ የደረሰን ቅሬታ ለእናንተስ ደርሶአችኋል ወይ? ስንል የራያ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢን መ/ር አለባቸው መኮንን አነጋግረናል። እውነት ነው ቅሬታው ደርሶናል ያሉት መ/ር አለባቸው “አሀዳዊ መንግስት ሊጨፈልቃችሁ መጣባችሁ!” እያሉ ማህበረሰቡን በተለይ ደግሞ ወጣቱን እረፍት ነስተውታል ሲሉ ተናግረዋል። ለልማት ብለው ከወሰዱ በኋላ ወደ ወታደርነት መቀየራቸው የተነቃ መሆኑን ተከትሎ ልጆቻቸውን ያሸሹ ወገኖች እንዳሉም እናውቃለን ብለዋል። መንግስት ማህበረሰቡን እየሰማውና ለስቃዩ እየደረሰለት ባለመሆኑ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ስለመኖሩና ቅሬታውንም ኮሚቴው እንደሚጋራው መ/ር አለባቸው ተናግረዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply