ህወሃት በትግራይ ክልል መሰረታዊ አገልገሎቶች እንዲጀመሩ ለሚመደቡ ሠራተኞች የደኅንነት ዋስትና እንደሚሰጥ ገለጸ

ዕረቡ ሐምሌ 27 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት (ዶ/ር) ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል በትግራይ ክልል የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀምሩ፤ ወደ ክልሉ ገብተው የጥገና ሥራ እንዲሰሩ ለሚመደቡ ሠራተኞች የደህንነት ማረጋገጫ የሚሰጥ ደብዳቤ በዓለማቀፍ ማህበረሰቡ ተወካዮች በኩል ለፌደራል መንግሥት መላካቸው ተገለጸ።

ይህም ደብዳቤ እንደ ስልክ፣ ባንክ፣ መብራት እና የመሳሰሉትን መሰረታዊ አገልግሎቶች ወደነበሩበት ለመመለስ እና አገልግሎት እንዲጀምሩ ለማድረግ ወደ ክልሉ ገብተው ለሚሰሩ አካላት የደህንነት ማረጋገጫ የሚሰጥ መሆኑን የአውሮፓ ህብረት በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልእከተኛ ማይክ ሀመር፣ በአፍሪካ ቀንድ የአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ አኔት ዌይበር፣ የተባበሩት መንግስታቱ ድርጅት ተወካይ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ጉዳይ አስፈፃሚ፣ የካናዳ እና ጣልያን አምባሳደሮች፣ ተወካዮች እንዲሁም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፤ ትናንት ሐምሌ 26 ቀን 2014 ወደ ትግራይ ክልል በመጓዝ ከህወሃት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመቀለ ተወያይተዋል።

የውይይታቸውም አላማ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሃት) መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የፖለቲካ ውይይት እንዲጀመር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ለማበረታታት ነው።

የአውሮፓ ህብረት ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የባንክ እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች በአስቸኳይ ወደነበሩበት መመለሳቸው ለትግራይ ህዝብ አስፈላጊ መሆኑን ከፌደራል መንግስት ጋር ተወያይቶ ሥምምነት ላይ መደረሱን ማስታወቁ ይታወሳል።

ነገር ግን የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ የተቋረጡትን መሠረታዊ አግልግሎቶች መልሶ ለማስጀመር ዋነኛው እንቅፋት ለጥገና የሚሰማሩ ሠራተኞች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ነው በማለት ሲገልጽ ቆይቷል።

የአውሮፓ ህብረትም፤ የልዩ መልዕክተኞቹን የትናንትና ጉብኝት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የተቋረጡትን መሠረታዊ አግልግሎቶች መልሶ ለማስጀመር ለጥገና ለሚሰማሩ ሠራተኞች የሚሰጠውን የደኅንነት ማረጋገጫ በተመለከተ ለፌደራሉ መንግሥት ደብዳቤ መላካቸውን አስታውቋል።

በዚህም የክልሉ መንግስት መሠረታዊ አገልግሎቶቹን መልሰው ሥራ ለማስጀመር ለጥገና ወደ ትግራይ ክልል ለሚሰማሩ ሠራተኞች የደኅንነት ዋስትና እንደሚሰጥ በደብዳቤው መመላከቱ ተገልጿል።

በተጨማሪም ህብረቱ በመግለጫው “በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለመቋጨት ፖለቲካዊ ውይይት አስፈላጊ ነው” ያለ ሲሆን፤ ኹለቱም ተዋጊ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር ለመፍታት ያሳዩት ጥረት በማድነቅ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የሚካሄደውን ንግግር ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

የልዑኩ ቡድኑ በጦርነቱ ለተጎዱት በትግራይ፣ በአማራ እና አፋር ክልሎች ውስጥ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚሹ አካላት በአፋጣኝ እርዳታ ማቅረቡ ወሳኝ መሆኑንም አሳስቧል።

በተጨማሪም በነዳጅ፣ በጥሬ ገንዘብ እና በማዳበሪያ ላይ ተጥሎ ያለው ክልከላ መነሳት አለበት ያለው የህብረቱ መግለጫ፤ ኹለቱም ወገኖች ከጥላቻ እና ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ንግግሮች እንዲቆጠቡ ጠይቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply