ህወሃት ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለሚደረገው ድርድር ተደራዳሪዎችን መሰየሙን አስታወቀ

ሐምሌ 12 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተውን የእርስ በርስ ጦርነት በሰላም ለመፍታት ለሚደረገው ድርድር የሰላም ቡድን መቋቋሙን የህወሃት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ።

የፌዴራል መንግሥት ለዚሁ ይደረጋል ለባለው ድርድር ተደራዳሪ ኮሚቴ በማቋቋም ሥራ መጀመሩን መግለፁ ይታወሳል።

ይህንም ተከትሎ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ”ለድርድር የሚሆን ልዑክ ወደ ናይሮቢ ለመላክ ዝግጁ እንሆናለን” ሲሉ መናገራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ቃላ አቀባዩ ተደራዳሪ ቡድኑ ውስጥ እነማን እንደተካተቱና ቁጥራቸውን በተመለከተ ያሉት ነገር ባይኖርም፤ በከፍተኛ ሥልጣን ደረጃ የሚገኙ አባላት ያሉት ኮሚቴም መቀቋቋሙን ግን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሃት ጋር የሚደረገው ምንም አይነት ድርድር ሊመራ የሚችለው በአፍሪካ ህብረት ብቻ መሆኑን አቋሙን ያስታወቀ አስታውቋል። ይህንንም ተከትሎ የህወሃት አመራሮች በህብረቱ ላይ ያላቸውን ቅሬታ በማንሳት ድርድሩ በህብረቱ ጥላ ሥር ብቻ እንዲሆን እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።

“ኹሉንም የድርድር ሂደቶች ለአፍሪካ ኅብረት መስጠቱ ለእኛ በጣም ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው” ያሉት ጌታቸው፣ ማንኛውም ድርድር በሰላም ጥረት ውስጥ ንቁ ሚና የተጫወቱትን ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ማካተት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

ቃል አቀባዩ በተጨማሪም በአማራ ክልል ዘንድ የይገባኛል ጥያቄ ያለበትና፤ በአሁኑ ወቅት በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ያለው ምዕራብ ትግራይ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም በማለት መናገራቸውን ኤኤፍፒ ዘገባው አስነብቧል።

ከህወሃት ከምዕራብ ትግራይ በተጨማሪ የመሰረተ ልማት ጥያቄ ለድርድር አይቀርብም በሚል በተደጋጋሚ መናገሩ የሚታወስ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ግን እስካሁን የተቀመጠ ቅድመ ሁኔታ የለም።

የፌዴራል መንግሥት ከህወሃት አመራሮች ጋር የሚያደርገው ውይይት መቼ እንደሚጀመርም ሆነ፣ የት እንደሚደረግ ከኹለቱም ተደራዳሪ ወገኖች በኩል እስካሁን የተገለጸ መረጃ ባይኖርም፤ በህወሃት በኩል የኬንያ መዲና ናይሮቢ ትሁን የሚል ሃሳብ ቀርቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply