“ህወሓት በኃይል ወስዶት የነበረውን የአማራ ርስት፣ ራያና ወልቃይት ጠገዴን አሳልፎ የሚሰጥ ድርድር የሚደረግ ከሆነ እጅግ አድርገን እናወግዘዋለን ስምምነቱም ተቀባይነት የለውም።” ሲሉ በኒውዝ…

“ህወሓት በኃይል ወስዶት የነበረውን የአማራ ርስት፣ ራያና ወልቃይት ጠገዴን አሳልፎ የሚሰጥ ድርድር የሚደረግ ከሆነ እጅግ አድርገን እናወግዘዋለን ስምምነቱም ተቀባይነት የለውም።” ሲሉ በኒውዝላንድ ሀገር የሚገኙ የአማራ ማህበራት አስታወቁ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 16 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በኒውዝላንድ ሀገር የሚገኙ የአማራ ማህበራት ለአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) በላኩት መግለጫ “ህወሓት በኃይል ወስዶት የነበረውን የአማራ ርስት፣ ራያና ወልቃይት ጠገዴን አሳልፎ የሚሰጥ ድርድር የሚደረግ ከሆነ እጅግ አድርገን እናወግዘዋለን፤ ስምምነቱም ተቀባይነት የለውም።” ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል። “ሰላም የሁሉ በጎ ነገሮች ሁሉ መሰረት ነው።ጥሩ ጦርነት፣ መጥፎ ሰላም የለም። ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለተፈጥሮ የተሰጠ ትልቅ ጸጋ ቢኖር ሰላም ነው።” ያሉት ማህበራቱ ነገር ግን የህዝቡን ቁስል በመነካካትና እንደ እባብ ተስለክልኮ ከሚኒልክ ቤተመንግስት የገባው ህወሓት የተሰኘው የባንዳወች ስብስብ አገሪቱን በቋንቋ ፌደራሊዝም በክልል ከፋፍሎ በመከለል መለያዬትን እና ጥላቻን አብዝቶ ስለመስበኩ፣ በዚህም አገሪቱንም ደም እንዳለበሳትና ህዝቡንም እንዳደኸየው በመግለጫቸው አስፍረዋል። “ታላቋ” ያሏትን “ትግራይ” ለመመስረት ይዘውት የተነሱትን፣ ህልማቸውን እውን ለማድረግም የወልቃይትና የራያ አማራን ቀደምት ርስት ለም መሬቶች ቡድኑ ስልጣኑን በመጠቀም ካርታ ሁሉ በመስራት በኃይል ወደ ትግራይ በማካለል በአማራ ላይ ዘርፈ ብዙ ጥቃት ስለመፈጸሙ ጠቅሰዋል። ህወሓት ኢህአዴግ ከደደቢት በርሀ ይዞት በመጣው ማኒፌስቶው “አማራ ጠላቴ ነው” ብሎ ያቀደውን እኩይ አላማ እውን ለማድረግም በአማራ የአስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ ጸረ አማራ አመለካከት ያላቸውን ባንዳወችን በመሾም አያሌ ግፍ እና በደል ስለማድረሱም በመግለጫቸው አካተዋል። አሁንም ቢሆን ስር ነቀል ለውጥ ባለመደረጉ እንደ ቫይረስ ራሳቸውን ቀይረው ብልጽግና ነን ብለው እየተገላበጡ ህዝቡ ነጻነቱን እንዳያገኝ እያደረጉትና መከራውን እያበዙበት ይገኛሉ ብለዋል። አሸባሪው ትሕነግ ጥቅምት 24/2013 በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ እና በመቀጠልም በአማራ እና አፋር አካባቢዎች ባካሄዳቸው ተከታታይ የወረራ ጦርነቶች በርካታ የአማራ እና የአፋር ነዋሪዎች በግፍ ተረሽነዋል፣ ሴቶች በጅምላ ተደፍረዋል፣ሀብት ንብረታቸውን ተዘርፈዋል፣ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ የህዝብ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል። በግንባር የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት፣የአማራ ልዩ ሀይል፣የአማራ ሚሊሻ፣ፋኖና እንዲሁም የአማራ አረሶ አደሮች ውድ ህይወታቸውን ሰውተዋል። በዚህ ጦርነትም አሜሪካና ምዕራባዊያን አሻንጉሊታቸውን ህወሓት ዳግም ከመንበሩ ለመመለስ ከፍተኛ የሆነ ቁሳዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ አይናቸውን ጨፍነው እገዛ ሲያደርጉለት ቆይተዋል ሲሉ ገልጸዋል። በተያያዘም ህወሓት የወለደው ኦነግ ሸኔ በኦሮሚያ ክልል የሚያደርገው ያለ ከልካይ የአማራን ዘር የማጽዳት ዘመቻ እንዲሁም ስርዓቱ በመሐል አገር ለአገርና ለነጻነት የሚዋጋውን ፋኖና ቤተሰቦቹን ከበሩ ድረስ አድፍጦ በመግደልና በሽህዎች የሚቆጠሩ የአማራ ፋኖወችን እስር ቤት ማጎር ሌላ ገና ትግል እና ፍትህ የሚጠይቅ ጉዳይ ስለመሆኑም አመላክተዋል። በመጨረሻም በጦርነትም ሆነ በሰላም አማራጭ ህወሓትን የሚወገድበትን መንገድ፣ የጦርነቱን የመጨረሻ መቋጫ የሚያመጣና ጉዳዩ የሚመለከተው የአማራ ተወካዮችን ያላገለለ ከሆነ እንደግፈዋለን ብለዋል። ይሁን እንጅ በድርድሩ ችግሩ በቀጥታ የሚመለከተው አማራ ካልተወከለበት ግን እንደስልጣን ድርድር እንደሚያዩት እና ዘላቂ መፍትሔም ያመጣል ብለው እንደማያምኑ አቋማቸውን አስታውቀዋል። የጋራ ማህበሩ ህወሓት በኃይል ወስዶት የነበረውን የአማራ ርስት፣ ራያና ወልቃይት ጠገዴን አሳልፎ የሚሰጥ ድርድር የሚያደርግ ከሆነ እጅግ አድርገን እናወግዘዋለን ፤ ስምምነቱም ተቀባይነት የለውም፤ አንድ አንድ በብልጽግና ውስጥ የተሰገሰጉ የአብን አመራሮችና አባላትም አማራ በድርድሩ መወከል የለበትም የሚሉትን አመለካከት አጥብቀን እናወግዛለን ሲሉ በጋራ መግለጫቸው አስፍረዋል። ለሰላም ድርድሩም የአማራ ልዑካን ቡድንን የሚመሩት:_ 1/አቶ ቴወድሮስ ትርፌ፣ 2/ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ፣ 3/ዶክተር ወንደሰን አሰፋ እና 4/ጄኔራል ተፈራ ማሞ መሆናቸውን እንደሚቀበሉት የገለጹት:_ 1/የአማራ ቤተሰቦች ማህበር በሊንግተን 2/የአማራና የአማራ ቤተሰቦች ኢትዮጵያን ማህበር በኦክላንድ 3/የአማራ ተራድዖና መልሶ መቋቋም ማህበር በከርይስት ቸርች ኒውዚላንድ ናቸው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply