ህወሓት በአማራ ክልል ላይ “በሙሉ አቅሙ” ወረራ መፈጸም ጀምሯል- የአማራ ክልላዊ መንግስት

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከስህተቱ መማር “የተሳነው” ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) “የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል” በማለት አስታወቀ። 

አዲስ ማለዳ የተመለከተችው የክልሉ መንግስት መግለጫ መጋቢት 16 ቀን 2016በርካሽ ፖለቲካዊ ብያኔና ፍረጃ በጊዜያዊ አሥተዳደሩ ካቢኔ አማካኝነት የአማራ ክልል ተማሪዎችን መማሪያ መጽሐፍ እንደ ሰበብ ተጠቅሞ በይፋ ጦርነት” አውጇል፤ “በሙሉ አቅሙ ወደ ጦርነት ገብቷል” ይላል። 

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ትላንት በምክትል ፕሬዝዳንቱ ታደሰ ወረደ በኩል በሰጠው መግለጫ “የአማራ ታጣቂዎች” ያቋቋሟቸውን አስተዳደሮች ለማፍረስ ከፌደራል መንግስት ጋር ተስማምተናል ማለቱን አዲስ ማለዳ መዘገቧ አይነጋም። 

የአማራ ክልላዊ መንግስት ከባህር ዳር ዛሬ ባወጣው መግለጫ “የማንነት ጥያቄ ያለባቸውን የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረምና ዛታ አካባቢዎች ላይ” ህ.ወ.ሓ.ት ወረራ ፈጽሟል ያለ ሲሆን ወረራው የተፈጸመው የአማራ ክልል መንግስት ከፌደራል መንግስት እና ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ለማድረግ ጥረት እያደረገ በሚገኝበት ወቅት ነው ተብሏል። 

የማንነትና የራስ አሥተዳደር ጥያቄ ያለባቸውን አካባቢዎች በጉልበት ተገፎባቸው የነበረውን ራሳቸውን የማሥተዳደር ነጻነት “የህወሓት የጥፋት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን አሰቃቂና ታሪክ ምንጊዜም የማይዘነጋው የባንዳነት ተግባር ተከትሎ በተቀሰቀሰው ጦርነት” ሳቢያ መቀዳጀት ችለዋል መባሉን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች።

የአማራ ክልል መንግስት ለክልሉ የፖለቲካና የጸጥታ መዋቅር “እንደ ትናንቱ በፅናትና በቁርጠኝነት ሕዝቡን በማደራጀት አካባቢያችሁን” ጠብቁ ያለ ሲሆን ለክልሉ ሕዝብም “ጠላቶቻችን የከፈቱብንን ጥቃት ለመመከት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከመንግሥት ጎን” እድኒሰለፉ ጥሪ አቅርቧል። 

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት “ይህን እብሪተኛ ቡድን” በአጭር ጊዜ ከወረራቸው አካባቢዎች እንዲያስወጣ እና ሕዝቡን ከጥፋት በመታደግና “የሀገራችንን ሉዓላዊነት” ያስከብር ሲል የአማራ ክልላዊ መንግስት ጠይቋል። የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብም “ህ.ወ.ሓ.ት የፈጸመውን” ወረራ በጥብቅ እንዲያወግዝ ሲል የክልሉ መንግስት መጠየቁን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር “የመጀመሪያው እርምጃ በየአካባቢው የታጠቁ ቡድኖችን ማፍረስ እና የተቋቋሙትን ህገ-መንግስታዊ ያልሆኑ አስተዳደሮችን ማፍረስ ነው” ያለ ሲሆን “የፍትህ ስርዓቱን ወደነበረበት መመለስ” በተከታይነት ይሰራል ማለቱ ይታወሳል። 

Source: Link to the Post

Leave a Reply