ህወሓት ከሽብርተኝነት መዝገብ ተሰረዘ

⚫ 61 የፓርላማ አባላት የውሳኔ ሃሳቡን ተቃውመዋል

በሃሚድ አወል

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከሽብርተኝነት መዝገብ መሰረዙን፤ 61 የፓርላማ አባላት ተቃወሙ። አምስት የፓርላማ አባላትም ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል።

የፓርላማ አባላቱ ተቃውሞ እና ድምጸ ተዐቅቦ የተመዘገበው፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህወሓት ላይ አስተላልፎት የነበረውን የሽብርተኝነት ፍረጃ ለመሰረዝ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 13፤ 2015 ባካሄደው “ልዩ ጉባኤ” ላይ ነው። 280 የፓርላማ አባላት በተገኙበት በዛሬው “ልዩ ጉባኤ” በመንግስት ተጠሪ የቀረበው ህወሓትን ከሽብርተኝነት የመሰረዝ የውሳኔ ሃሳብ፤ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 መቀመጫዎች፤ በተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በግል ተመራጮች የተያዙት 16ቱ ብቻ ናቸው። ገዢው ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ መቀመጫውን በያዘበት ፓርላማ ያሉ ተወካዮችን፤ ከዛሬው “ልዩ ጉባኤ” አንድ ቀን አስቀድሞ ሰብስቦ ውይይት ቢያካሄድም ከራሱ አባላት ጭምር ተቃውሞን ከማስተናገድ አልዳነም። 

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን በተገኙበት በትላትናው ስብሰባ ላይ፤ ህወሓትን ከአሸባሪነት የመሰረዝ አስፈላጊነት በተመለከተ ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎች ቀርበው እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል። በዚሁ የውይይት መድረክ፤ “ህወሓትን ከአሸባሪነት ከተሰረዘ በኋላ ምን ማስተማመኛ አለ?” የሚለውን ጨምሮ ስጋት ያዘሉ ጥያቄዎች ቀርበው ነበር ተብሏል። 

በዛሬው የፓርላማ ልዩ ጉባኤም በተመሳሳይ መልኩ፤ ከገዢው ፓርቲ የፓርላማ ተመራጮች “ጠንከር ያሉ” አስተያየቶች መቅረባቸውን ስብሰባውን የታደሙ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ይታከልበታል]

The post ህወሓት ከሽብርተኝነት መዝገብ ተሰረዘ appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply