ህወሓት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በደቡብ አፍሪካ እንዲደራደር በአፍሪካ ኅብረት የቀረበለትን ጥሪ መቀበሉን አስታወቀ

ሐሙስ መስከረም 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ህወሓት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በደቡብ አፍሪካ እንዲደራደር በአፍሪካ ኅብረት የቀረበለትን ጥሪ መቀበሉን ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ለህብረቱ ሊቀንበር ሙሳ ፋኪ በፃፉት ደብደቤ አስታውቀዋል።

ዶ/ር ደብረፅዮን በፃፉት ደብዳቤ፤ “ግጭት ማቆም” ዋናው የድርድሩ የአጀንዳው አካል ተደርጎ ስለመያዙ ጠይቀዋል።

አክለውም “ተደራዳሪዎቻችን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጁ ነን” ያሉ ሲሆን፤ ነገር ግን “ግብዣው ቀደም ብሎ ያልተማከርንበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ቢሰጠን” ሲሉ ኅብረቱን ጠይቀዋል።

በዚህም፤ በሰላም ውይይቱ ተጨማሪ ተዋናይን እንደ ተሳታፊዎች፣ ታዛቢዎች ወይም ዋስትና ሰጪዎች ተጋባዥ ስለመሆናቸውና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለሚኖረው ሚና ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም፤ የህወሓት ተደራዳሪ ቡድን የሎጅስቲክስ፣ የጉዞ እና የደህንነት ዝግጅቶችን በተመለከተ እንዲብራራላቸው ዶ/ር ደብረፅዮን ለፋኪ በላኩት ደብዳቤ ጠይቀዋል።

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር ለመፍታት መንግሥት ሰኔ 20/2014 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሰብሳቢነት የሚመሩት በአጠቃላይ ሰባት አባላት ያሉት የሰላም አማራጭ ዐቢይ ኮሚቴ መሰየሙ ይታወሳል።

ህወሓት በበኩሉ በድጋሚ ከተቀሰቀሰው ጦርነት በኋላ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ሥር ለመደራደር ፍቃደኝቱን በመግለጽ፤ ለዚህም ጌታቸው ረዳን እና ጄነራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤን ያካተተ ተደራዳሪ ቡድን መሰየሙን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ “የአፍሪካ ኅብረት ግብዣ መንግሥት ከዚህ በፊት ያቀረባቸውን አቋሞች የጠበቀ ሆኖ ተገኝቷል” ያለ ሲሆን፤ ኅብረቱ የሰላም ውይይቱ እንዲጀመር ያቀረበውን ይፋዊ ጥሪ እንደተቀበለ ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

The post ህወሓት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በደቡብ አፍሪካ እንዲደራደር በአፍሪካ ኅብረት የቀረበለትን ጥሪ መቀበሉን አስታወቀ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply