ህ.ወ.ሓ.ት በድጋሚ የፖለቲካ ፓርቲ እውቅና ሊያገኝ የሚችልበት አዋጅ እንዲጸድቅ ለፓርላማ ተላለፈ 

ዓርብ ግንቦት 23 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የትግራይ ሕዝባዊ ነጻነት ግንባር ት.ሕ.ነ.ግ/ህ.ወ.ሓ.ት በድጋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ እንዲሾም ሊፈቅድለት የሚችል ረቂቅ አዋጅ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ ‘የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ’ እንዲሻሻል ወስኖ ለፓርላማው አስተላልፏል።

አዲስ ማለዳ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ባገኘችው መረጃ እንደተገለጸው የቀደመው አዋጅ እንደ ህ.ወ.ሓ.ት ያሉ ከሕጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የማያስችል በመሆኑ አሁን “መልሶ” ሕጋዊ መሆን የሚችሉበት ስርዓት በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ተካቷል።

የዛሬው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ከኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ማሻሻል በተጨማሪ፤ የንብረት ማስመለስ አዋጅ፣ በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አድርጎ ስለማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ሥርዓት ለመደንገግ የቀረበ አዋጅን በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተላልፈዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply