ለህልውና ዘመቻ ሲደረግ እንደቆየው ድጋፍ ሁሉ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋምም እንደሚገባ የባህርዳር ሀገረ ስብከት አሳሰበ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 20 ቀን 2014…

ለህልውና ዘመቻ ሲደረግ እንደቆየው ድጋፍ ሁሉ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋምም እንደሚገባ የባህርዳር ሀገረ ስብከት አሳሰበ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የባህርዳር ሀገረ ስብከት መጭውን የልደት(የገና) በዓልን ምክንያት በማድረግ የትግራይ ወራሪ ቡድን ባደረሰው ጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች ማቋቋሚያ የሚውል የ4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ዻዻስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፅዕ አቡነ አብርሃም እንደገለፁት ሰው በችግር ጊዜ መረዳዳት በጨነቀ ጊዜ ማጽናናት ከእግዚአብሔር የተሰጠን ፀጋ በመሆኑ በሀገረ ስብከቱ ስር ያሉ 40 የሚሆኑ ገዳማትና አድባራት ከነ አገልጋዮች በማስተባበር ካሁን በፊት ሲያደርግ ከቆየው ድጋፍ በተጨማሪ ከሀገረ ስብከት እስከ ታችኛው አጥቢያ ቤተክርስቲያን ድረስ የሚገኙ ምዕመናንና ምዕመናትን የተሳተፉበት ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል። ቤተ ክርስቲያኗ ከጸሎት ባለፈ ለተራቡ፣ለተጠሙና ለተራዙ ወገኖቻችን መድረስ፣ ለፈረሱ የትምህርት፣ የጤና እና የኃይማኖት ተቋማት እንዲሁም የግለሰብና የመንግስት ቤቶችን መልሶ መጠገን ተገቢ በመሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል። ብፅዕነታቸው አያይዘውም ሰው ለሰው መዳህኒት መሆኑን ወደ ጎን በመተው አጥፊ ከሚሆን ይልቅ የሚጠቅመው ክፉውን ጊዜ ተደጋግፎና ተከባብሮ በማሳለፍ እና ክፍውን በጋራ ሀይ በማለት ለጋራ ከሰላምና ልማት በጋራ መቆም እንደሚገባ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የባህርዳር ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው በብፅዕ አቡነ አብርሃም የሚመራው የባህርዳር ሀገረ ስብከት ከዚህ በፊት የህልውና ዘመቻው ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ህዝቡን በጸሎት ከመጠበቅ ባሻገር እየተደረገ ያለው የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ከሚጠበቀው በላይ መሆኑን አስታውሰዋል። በዛሬው ዕለትም መንፈሳዊና የቁሳዊ እንዲሁም ስነ ልቦናዊ ጉዳት ለደረሰባቸውና በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙ የጦርነት ቀጠና ሆነው ለቆዮ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ 4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማድረጋቸው በባህርዳር ከተማ ህዝብና መንግስት ስም የከበረ ምስጋና ያላቸው መሆኑን ገልፀዋል። በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ በሚያከናውናቸው የህዝብ ልማትና ሰላም ግንባታ ተግባራት ላይ ሀገረ ስብከቱ ከጎናቸው እንደማይለይና የተጀመረውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን የፀና እምነት ገልፀዋል ሲል የዘገበው የባህርዳር ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ነው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply