ለህዳሴ ግድብ ግንባታ በሰኔ ወር ከ201 ሚሊዮን 595 ሺሕ ብር በላይ መሰብሰቡ ተነገረ

በሰኔ ወር የተሰበሰበው ገንዘብ ከሌሎች ወራቶች የላቀ መሆኑም ተገልጿል

አርብ ነሐሴ 6 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በሰኔ ወር የተሰበሰበው ገንዘብ ከ201 ሚሊዮን 595 ሺሕ በላይ በመሆን ከሌሎች ወራቶች የላቀ መሆኑ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

ለግድቡ ግንባታ በ2014 በጀት ዓመት አጠቃላይ የተሰበሰበው ገንዘብ ከ1ቢሊዮን 186 ሚሊዮን 297 ሺሕ ብር በላይ መሆኑን የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት የሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ ተናግረዋል።

ገቢው ከአገር ውስጥ እና ከዳያስፖራ ቦንድ ሽያጭ፣ ከህዳሴው ግድብ ዋንጫ፣ ከ8100 አጭር የሞባይል የጽሁፍ መልዕክት፣ ስጦታ እና ልዩ ልዩ ገቢዎች የተሰበሰበ መሆኑ ተጠቁሟል።

በበጀት ዓመቱ ከአገር ውስጥ የቦንድ ሽያጭ እና ስጦታ ከ733 ሚሊዮን 39 ሺሕ ብር በላይ፣ ከውጭ አገር ዳያስፖራ ቦንድ ሽያጭ እና ስጦታ ከ271 ሚሊዮን 794 ሺሕ ብር በላይ፣ ከ8100 አጭር የሞባይል የጽሁፍ መልዕክት ከ166ሚሊዮን 139 ሺሕ በላይ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢዎች የተሰበሰበ መሆኑ ተጠቁሟል።

የህዳሴው ግድብ ዋንጫ በተዘዋወረባቸው አካባቢዎችም መነቃቃትን በመፍጠሩ ከፍተኛ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉም ተነግሯል።

ዘንድሮ ለግድቡ ግንባታ የተደረገው የገቢ ማሰባሰብ ሥራ በአገሪቱ ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት በኹሉም የአገሪቱ ክፍሎች አለመከናወኑን የጠቀሱት ኃይሉ፣ ነገር ግን የተሰበሰበው ገንዘብ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የተወሰኑ ዓመታት ጋር ሲነጻጸር መልካም የሚባል እንደሆነ ተናግረዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ከ2003 ጀምሮ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ለግድቡ ግንባታ ከ16 ቢሊዮን 915 ሚሊዮን 312 ሺሕ ብር በላይ መሰብሰቡም ተገልጿል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply