ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የመብት ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ከወረታ ወደ አዲስ አበባ የመጡ የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች በፀጥታ አካላት እንዲመለሱ መደረጉን አስታወቁ። አማራ ሚዲያ ማዕከ…

ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የመብት ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ከወረታ ወደ አዲስ አበባ የመጡ የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች በፀጥታ አካላት እንዲመለሱ መደረጉን አስታወቁ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መስከረም 10 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በአርበኞች ግንቦት 7 ድርጅት ስር ሆነው በኤርትራ በርሀ የቆዩና በግዳጅ፣በድርድር እና በተለያየ መልኩ ወደ ሀገር ቤት የተመለሱ ታጋዮች በ3 ወር ውስጥ እንድትቋቋሙ ይደረጋል በሚል በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ወረታ ካምፕ እንዲገቡ መደረጉና መንግስት በገባው ቃል መሰረት ሳይቋቋሙ ከ2 ዓመት በላይ እንደሆናቸው ይታወቃል። መንግስት የገባውን ቃል አላከበረም በሚል በባህር ዳር ከአዴኃን፣ከኢሕአግ እና ከደምሂት ታጋዮች ጋር በመሆን መስከረም 9 ቀን 2013 ዓ.ም ለማድረግ የሞከሩት የተቃውሞ ሰልፍ በክልሉ መንግስት የፀጥታ አካላት ክልከላ የገጠመው መሆኑን መዘገቡ ይታወሳል። ይህን ተከትሎም በወረታ ካምፕ የሚገኙ ቁጥራቸው 80 የሚሆኑ የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች የመብት ጥያቄያቸውን ከውክልና ባለፈ በቀጥታ ለፌደራል መንግስት እና ለሚመለከታቸው አካላት ለማቅረብ በሚል ዛሬ መስከረም 10 ቀን 2013 ዓም ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ገልፀዋል። ታጋዮቹ ከአሁን ቀደም መንግስት ለማቋቋም የገባውን ቃል እንዲያከብርና ለተዘነጉ እና በችግር ላይ ላሉ ታጋዮች እንዲደርስ በሚል የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ አቅደው እንደነበር ገልፀዋል። ይሁን እንጅ ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት ገደማ አዲስ አበባ ለመግባት እንጦጦ አካባቢ ሲደርሱ በፌደራል፣በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላት አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ መከልከላቸውን አርበኛ ያሬድ ገብርዬ አስታውቋል። ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ብሎም እንዲመለሱ መደረጉ እንዳሳዘነው የገለፀው አርበኛ ያሬድ ታጋዮቹ ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱላቸውና ትኩረት እንዲሰጣቸው በሰላማዊ መንገድ ለመንግስት ድምጻቸውን ከማሰማት ውጭ ሌላ አላማ እንደሌላቸው ነው ያስታወቀው። በፓትሮል በተጫኑ ቀይ ቦኔት ለባሽ እና በሌሎች የፀጥታ አካላት ተገደውና ታጅበው በጨለማ እንዲመለሱ እየተደረገ እና በጉዞ ላይ መሆናቸውን ለአማራ ሚዲያ ማዕከል የገለፀው ሌላኛው ታጋይ የመንግስት አድራጎት ታጋዮችን እጅግ በጣም እንዳስቆጣቸውና እንዳሳፈራቸውም ጭምር ገልጧል። መንግስት የገባውን ቃል አክብሮ እንዲቋቋሙ እስካላደረገ፣በየበርሀው ለወደቁ የታጋዮች ቤተሰብ ተገቢ ድጋፍ እስካልተደረገለና የመብት ጥያቄዎችን ከመመለስ ይልቅ በሀይል ማፈንን እስከመረጠ ድረስ ትግሉ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply