ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይል የተሰጡ ሥልጣኖች

ማንኛውንም የፀጥታ ኃይል ትጥቅ ማስፈታትን ጨምሮ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይሉ የተሰጡ ሥልጣኖች ይፋ ሆኑ፡፡

በትግራይ ክልል ለ6 ወር የሚፀናው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕዝብ እንደራሴዎች መፅደቁን ተከትሎ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ የሰጡት የፌደራል ዋና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም የሚመራው እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆነው ግብረ ኃይል ማንኛውንም የፀጥታ ኃይል በማስተባበር በአንድ ዕዝ ስር እንዲመራ ማድረግ ይችላል ብለዋል፡፡

የንፁሃን ዜጎች መብት ሳይጣስ አዋጁ በተጣለባቸው አካባቢዎች ላይ ተልዕኮውን ማስፈፀም የሚያስችለውን እርምጃ መውሰድ እንዲችል ሥልጣን የተሰጠው ግብረ ኃይሉ፤ ፖሊስን ጨምሮ ማንኛውንም የፀጥታ ኃይል ትጥቅ ማስፈታት ይችላል ሲሉም አብራርተዋል፡፡

የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መገደብን ጨምሮ የሰዓት እላፊ ገደብ የማውጣት፣ የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴዎችን የማስቆም፣ የመገናኛ ዘዴዎች እንዲቋረጡ የማድረግ ኃላፊነትም ተሰጥቶታል፡፡

መግለጫዎችን የመከልከል እና ሕገ ወጥ በሆነ ተግባር ተሳትፈዋል ያላቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች መያዝና ማቆየትም ይችላል ተብሏል፡፡

እንደ ዋና አቃቤ ሕጉ ማብራሪያ ቤትና አካባቢዎችን ጨምሮ መጓጓዣዎችንም በማንኛውም ጊዜ መበርበርና መፈተሽ ይችላል፡፡

አሐዱ ቴሌቪዥን

Source: Link to the Post

Leave a Reply