ለአቶ ጃዋር መሐመድ ሕገወጥ መሣሪያ በመግጠም ወንጀል ለተከሰሰው አሜሪካዊ የተፈቀደው ዋስትና ታገደ

ከቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣንና ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ዕውቅና ውጪ በሕገወጥ መንገድ የገባ የሳተላይት መሣሪያ በአቶ ጃዋር መሐመድ ቤት በመግጠም አዋጅ ቁጥር 761 ድንጋጌን በመተላለፍ፣ የቴሌኮም ማጭበርበበር ወንጀል ፈጽሟል በማለት ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተበት አሜሪካዊ በዋስ እንዲለቀቅ የተፈቀደለት ቢሆንም ዋስትናው በይግባኝ ታግዷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ባቀረበበት ክስ አሜሪካዊው አቶ ሚሻ አደም የኢትዮ ቴሌኮምን መሠረተ ልማት በመተው፣ የሳተላይት መሣሪያዎችን ከአሜሪካ በማስመጣት በአቶ ጃዋር ቤት መገጣጠሙን አስረድቷል፡፡ መሣሪያዎቹ በግለሰብ እጅ የሚያዙ እንዳልሆኑና በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የገቡ መሆኑንም አስረድቷል፡፡ ተከሳሹ በአቶ ጃዋር ቤት የዘረጋቸው መሣሪያዎች ሮኬት ፕሪዝም ጂንቱ ሲስተም፣ ዩቢኪው ኤጅ ራውተርና ከሳተላይት የሚመጣውን ሲግናል ለመሰብሰብና የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ቪት ዲሽ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

ክሱን እያየው የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ ወንጀል ተረኛ ችሎት ጳጉሜን  4 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ፣ የተከሳሹ ጠበቆች ያቀረቡትን የደንበኛቸውን የዋስትና መብት የማስጠበቅ አቤቱታ እንደተመለከተው አስታውቆ፣ ተከሳሹ በ20 ሺሕ ብር ዋስ ሆኖ በውጭ ክርክሩን እንዲቀጥል ብይን ሰጥቶ ነበር፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የዋስትና መቃወሚያ አቤቱታ የተከሳሹ ዜግነት አሜሪካዊ ስለሆነ በአገር ውስጥ አድራሻ የሌለው መሆኑን፣ በዋስ ቢወጣ የምሕንድስና ሙያውን ተጠቅሞ በምስክሮች ላይ ጫና ሊፈጥር ይችላል የሚል ነበር፡፡ አሁንም በምስክሮች ላይ ማስፈራራት እየደረሰባቸው መሆኑንም አክሏል፡፡

የዓቃቤ ሕግን መቃወሚያ የተቃወሙት የአቶ ሚሻ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ተከሳሹ (ደንበኛቸው) የተጠቀሰበት የወንጀል ሕግ አንቀጽ ከአሥር እስከ 20 ዓመታት የሚያስቀጣ ቢሆንም ዋስትና አይከለክልም፡፡ የዋስትና መብት ሊከለከል የሚችለው አንድ ተከሳሽ የተጠቀሰበት የሕግ አንቀጽ ከ15 ዓመታት በላይ የሚያስቀጣው  ሲሆን ነው ብለዋል፡፡ አቶ ሚሻ የተከሰሰበት የወንጀል ድርጊትና የተጠቀሰበት የሕግ አንቀጽ አዋጅ ቁጥር 761 አንቀጽ (9)ን በመተላለፍ የቴሌኮም ኦፕሬተርነትን የሚመለከት  ድንጋጌ ተላልፎ የወንጀል ድርጊት ፈጽሟል በሚል ከአሥር እስከ 20 ዓመታት ያስቀጣል የሚል ቢሆንም፣ ዋስትና እንደማይከለክለው በመጥቀስ ተከራክረው ነበር፡፡

ዓቃቤ ሕግ በተጨማሪ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው ተከሳሹ ኢትዮ ቴሌኮም ከዘረጋው መሠረተ ልማት ውጭ የቴሌኮም መሣሪያዎችን ከአሜሪካ በማስመጣት፣ በአቶ ጃዋር መኖሪያ ቤት መዘርጋቱንና ድርጊቱ ሕገወጥ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ አስረድቷል፡፡

አቶ ሚሻ በኢትዮጵያ ሁለት ዓመታት መቆየቱን፣ ፓስፖርቱም በፖሊስ እጅ መሆኑንና አድራሻው ከእነ ክፍለ ከተማው ተጠቅሶ እያለ ዓቃቤ ሕግ ዋስትና ለማስከልከል እንደ መከራከሪያ መጠቀሙን ጠበቆቹ ተቃውመዋል፡፡ አቶ ሚሻ ከአገር የወጣው የዘጠኝ ዓመት ሕፃን እያለ ከመሆኑ አንፃር ምስክሮችን አግኝቶ ያባብላል ለማለት እንደማይቻልም ጠበቆች ተከራክረዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የደንበኛቸውን ሙያ በመጥቀስ ምስክር ሊያባብል ይችላል ማለቱ ተገቢ ካለመሆኑም በላይ፣ ሙያና ብቃት ወይም ዕውቀት የክብር መለኪያ እንጂ የተከሳሽን መብት መገደቢያ ሊሆን እንደማይገባም በክርክራቸው አስረድተዋል፡፡ ደንበኛቸውን አስሮ ለማሰቃየት የተነሳ መቃሚያ መሆኑን በመጠቆም፣ የዓቃቤ ሕግ አቤቱታ ውድቅ ተደርጎ አቶ ሚሻ በዋስ እንዲለቀቅ ተከራክረው ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በሰጠው ብይን የዓቃቤ ሕግ መከራከሪያ ሐሳብን እንዳልተቀበለው በመግለጽ፣ ተከሳሹ የ20 ሺሕ ብር ዋስትና በማስያዝ ከእስር እንዲፈታና በውጭ ሆኖ ክርክሩን እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

የፍርድ ቤቱ ብይን ቅር ያሰኘው ዓቃቤ ሕግ ብይኑን በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ተከሳሹ የውጭ ዜጋ መሆኑንና አድራሻው የማይታወቅ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የተጠቀሰበት የሕግ አንቀጽ እስከ 20 ዓመታት ሊያስቀጣው የሚችል በመሆኑ ዋስትና ሊፈቀድለት እንደማይገባ ገልጾ አቅርቧል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ለተከሳሹ የተፈቀደውን ዋስትና በማገድ ጠበቆቹ ጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ.ም. አስተያየት እንዲሰጡበት በማዘዝ፣ ብይን ለመስጠት ለመስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

https://www.ethiopianreporter.com/article/19813

Leave a Reply