ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ አቀባበል ተደረገ

ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ አቀባበል ተደረገ

https://1.gravatar.com/avatar/7f09202441ad3b4b636e88820d6a7061?s=96&d=identicon&r=G

“የቻልነውን ኹሉ በጋራ እንሠራለን፤ ሀገረ ስብከቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እናደርጋለን፤ በቻልነው መጠንም ችግሮችን እንፈታለን፤ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እስከ አጥቢያ የአገልጋዮችና የምእመናን ተግባራዊ ተሳትፎ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፤”

/ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ/

“የሀገረ ስብከቱ ኹለንተናዊ ብልሽት እየተባባሰ በመምጣቱ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የልዩ ሀገረ ስብከት ድንጋጌን ቅድሚያ ሰጥቶ አሻሽሏል፤ ችግሮቹም መፍትሔ ያገኛሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤”

/ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ/

***

ለተቋማዊ ለውጡ ተግባራዊነት ከብፁዕነታቸው ጎን እንደሚሰለፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አስታወቀ፤ አደናቃፊ መዝባሪዎችን እንደማይታገሥ አስጠነቀቀ!

“የብፁዕነታቸው ምደባ የሀገረ ስብከቱ የለውጥ ተስፋ አረጋጋጭ ነው፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ለሀገረ ስብከቱ ተቋማዊ ለውጥ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በማስተግበር፣ የአፈጻጸም ድክመቶችን ከመሠረቱ በማረም ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ እናግዛቸዋለን፤…

እኵይ ምዝበራቸውን ለማስቀጠል፣ ከአጥቢያ እስከ ሀገረ ስብከት ተሰግስገው ለውጡን ለማደናቀፍ ዕንቅፋት የሚፈጥሩ የጨለማ ኃይሎችን አንታገሥም! በይፋ እያጋለጥን ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው በጽናት እንታገላቸዋለን፤”

/የአዲስ አበባ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት/

***

“ቅዱስነታቸው በውሳኔው አልተስማሙም፤ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን በሙሉ ስለማሻሻል እንጂ፣ አጀንዳውን ከፍላችኹ በአንድ ሀገረ ስብከት ላይ ብቻ ለምን ታተኩራላችኹ፤ በሚል በምደባ ደብዳቤው አልፈረሙም፤ የጉባኤውን ውሳኔ እንዲያከብሩ ለአራት ቀናት ብናሳስባቸውም፣ በአንጋፋ አባቶች ብናስለምናቸውም አልተዉም፤ የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ስለማይቀለበስ፣ በብፁዕ ዋና ጸሐፊው ተፈርሞ እንዲወጣ አድርገናል፤…

ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውና ዝርዝር ማስፈጸሚያ ይወጣላቸዋል የተባሉትን ሌሎች የሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጾች ለይተው ከማሻሻያ ሐሳብ ጋራ ለቀጣዩ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ የሚያቀርቡ ሦስት ብፁዓን አባቶች እና የሕግ ባለሞያዎች ያሉበት ኮሚቴ ሠይመናል፡፡”

/የምልአተ ጉባኤው አባላት/

########

በቅዱስ ሲኖዶስ በተሻሻለው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሕገ ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌ መሠረት፣ በምልአተ ጉባኤው አብላጫ ድምፅ ተመርጠው፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ለተመደቡት ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 50 ንኡስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ፣ አዲስ አበባ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ኾኖ ቆይቷል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው መደበኛ ስብሰባው፥ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ እንደሌሎቹ አህጉረ ስብከት፣ ራሱን ችሎ በሊቀ ጳጳስ እንዲመራ በመወሰን ድንጋጌውን አሻሽሎታል፡፡

የድንጋጌውን ማሻሻያ ተከትሎ፣ ሀገረ ስብከቱን የሚመራ ሊቀ ጳጳስ ለመመደብ፣ ሦስት ብፁዓን አባቶች ተጠቁመው በተደረገው ምርጫ፣ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ፣ የምልአተ ጉባኤውን አብላጫ ድምፅ አግኝተው ተመርጠዋል፡፡ በመኾኑም፣ ከጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የጉራጌ ሀገረ ስብከትን እንደያዙ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው እንዲሠሩ በቅዱስ ሲኖዶስ በመመደባቸው፣ ትላንት ቅዳሜ፣ ጥቅምት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ከሌሎች ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ በመኾን ከብፁዕነታቸው ጋራ በተገኙበት የአቀባበል መርሐ ግብር፣ የብፁዕነታቸው የምደባ ደብዳቤ፥ በምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ እና ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ተነቧል፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ሀገረ ስብከቱን በተሻለ ለመምራት እና ለማስተዳደር የሚያስችል ከልዩ ኹኔታው ጋራ የተገናዘበ መዋቅር እና አደረጃጀት አለመኖሩ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በየዓመቱ ከሚነሡ አጀንዳዎች አንዱ እንደኾነ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የሲዳማ ጌዲኦ እና ቡርጂ ዞኖች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በአቀባበል መርሐ ግብሩ ላይ ተናግረዋል፡፡ ለአጀንዳው በቂ እና አግባብነት ያለው ምላሽ ሳይሰጠው በመዘግየቱ ግን፣ የሀገረ ስብከቱ ኹለንተናዊ ብልሽት እየተባባሰ መምጣቱን ብፁዕነታቸው አስረድተዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ አሁን እያካሔደ ባለው የምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባው፣ በጉዳዩ ተወያይቶ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን በማሻሻል ሀገረ ስብከቱ ራሱን ችሎ እንዲተዳደር በመወሰኑ፣ ምርጫ ተከናውኖ በአብላጫ ድምፅ የተመረጡትን ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አድርጎ መመደቡን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም፣ “የሀገረ ስብከቱ ችግሮች ምላሽ እና መፍትሔ ያገኛሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤” ብለዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱን ለሌላው አርኣያ ሊኾን በሚችል መልኩ በመልካም አስተዳደር መመራት እንዳለበትም በአጽንዖት አክለው አሳስበዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ሸዋ-ወሊሶ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በበኩላቸው፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን ነባራዊ ኹኔታ በማጥናት የተሰጠ መፍትሔ እንደኾነና ለሌሎች አህጉረ ስብከትም ደረጃ በደረጃ ችግሮችን ለመቅረፍ በመንፈሳዊ ጥብዓት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አክለውም፣ ኹላችንንም የጠራችንና የሰበበሰችን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን፣ በአኹኑ ጊዜ እየደረሰባት ያለውን ዘርፈ ብዙ መከራ ለመቅረፍ፣ በውስጥ ያለው የአስተዳደር ችግር በመቅረፍ  ለዘለዓለማዊ  ቅዱስ ወንጌል ዓላማ እና ሕይወት ተግቶ መሥራት የሚገባን ሰዓት ነው፤ ብለዋል፡፡

“ኵሎ ዘፈቀደ ገብረ እግዚአብሔር = እግዚአብሔር የፈቀደውን ያደርጋል፤” በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ፣ ቀደም ሲል በዚህ ቦታ ተመድበው ለዘጠኝ ወራት ያህል ሀገረ ስብከቱን መምራታቸውን አወስተዋል፡፡ የአኹኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ  ድንገተኛ እንደኾነባቸውና አልኾንም፤ አይገባኝም ብለው እንደነበር በኋላ ግን አባቶች፣ “እኛ እና መንፈስ ቅዱስ ወሰንን” ብለው ያገለገሉባት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በመኾኗ፣ የአባቶቼን አደራ ለመቀበል  ችያለኹ፤ ሕግ የመሥራት እና የማሻሻል ሥልጣን የተሰጠው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በድጋሚ መርጦ ለዚኽ ትልቅ ቦታ ሲመድበኝ፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደኾነ ተረድቼ ለማገልገል መጥቻለኹ፤ ብለዋል፡፡

አያይዘውም፣ እግዚአብሔር በሰጠን መልካም ዕድል እና ጊዜ ተጠቅመን፣ የቻልነውን ኹሉ በጋራ እንሠራለን፤ ሀገረ ስብከቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እናደርጋለን፤ በቻልነው መጠንም ችግሮችን እንፈታለን፤ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እስከ አጥቢያ ያሉ አገልጋዮች እና ምእመናን ተግባራዊ ተሳትፎ እጅጉን አስፈላጊ ነው፤ የእናንተ አብሮነት እና ጸሎት እንዲሁም ምክር አይለየኝ፤ በማለት አባታዊ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ፣ በቀደመው የልዩ ሀገረ ስብከት ድንጋጌ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ረዳት ጳጳስ ኾነው በቆዩበት ወቅት፣ ተወጥነው የነበሩ፥ የሰው ሀብት አስተዳደር፣ የንብረት እና ሀብት አስተዳደር፣ የመዝገብ ቤት ፋይል አስተዳደር እና የግምጃ ቤት(ስቶክ) አስተዳደር ሥርዓት መተግበሪያ ሶፍትዌሮችን ሥራ ላይ በማዋል ያሳዩትን ጅምር በበጎ በመጥቀስ፣ ሀገረ ስብከቱ የሚያስፈልገውን ተቋማዊ ለውጥ እና የአሠራር መሻሻል እውን ለማድረግ የሚያስችል ምሁራዊ ዐቅም እና ተራማጅ አስተሳሰብ እንዳላቸው ብዙዎች ተስፋን ሰንቀዋል፡፡

በርግጥም ይኸው የሀገረ ስብከቱ መሻሻል ተስፋ፣ በምልአተ ጉባኤው አባላትም ዘንድ የታየ ነው፡፡ የልዩ ድንጋጌው እንዲሻሻልና ሊቀ ጳጳሱ እንዲመደብ የተወሰነው፣ “ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን በሙሉ እንዲሻሻል ማድረግን በተመለከተ” በሚል ተይዞ ከነበረው አጠቃላይ አጀንዳ ማሕቀፍ ውስጥ ለብቻ ለይቶ ቅድሚያ በመስጠት ነው፡፡ ለድንጋጌው መሻሻል ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ ለቀናት የተሟገቱ ብፁዓን አባቶች፣ “የሀገረ ስብከቱ ችግር ጊዜ የማይሰጥ” ስለነበረ ነው ይላሉ፡፡

በገደብ አልባ እና ዘግናኝ የጉቦ ክፍያ በሚከናወነው የሠራተኛ ቅጥርና ዝውውር፣ “ወረራው መባባሱን፣ ሰዉም በጥቅም ሊጋደል መድረሱን” ይጠቅሳሉ፡፡ ቅዱስነታቸው፣ ድንጋጌው እንዳይሻሻል የተከላከሉትን ያህል፣ ሀገረ ስብከቱን በተግባር ቢቆጣጠሩትና ቢያሻሽሉት ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን፣ “የልዩ ድንጋጌ ለዱርዬዎቹ ጣልቃ ገብነት እና ጫና ነው የተመቻቸው፤ ቅዱስነትዎ የዚኽ ተጠቃሚ አይደሉም፤ እናውቃለን፤ እነእገሌ ግን መጫወቻ አድርገውታል፤” ብለዋል፡፡ በመኾኑም፣ “አዲስ አበባ እንደ ሌሎቹ አህጉረ ስብከት ራሱን ይቻል፤ ለልማቱም ለጥፋቱም ተጠያቂ ሊኾን የሚችል አንድ አባት ያለጣልቃ ገብነት መርጠን እናስቀምጥለት፤ ብቁ አመራር ይኑረው፤” በማለት መከራከራቸውን ተናግረዋል፡፡

የምልአተ ጉባኤውን መደበኛ ስብሰባ በርእሰ መንበርነት የሚመሩት ቅዱስነታቸው በበኩላቸው፣ “አጀንዳው በጸደቀበት መንገድ ማለትም፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን በሙሉ ስለማሻሻል መወያየቱን ትታችኹ፣ አጀንዳውን ከፍላችኹ በአንድ ሀገረ ስብከት ጉዳይ ላይ ብቻ ታተኩራላችኹ፤” በማለት አካሔዱን ተቃውመዋል፡፡ “ይህ ጥፋት አለ የምትሉትን አስረዱኝ፤ አሳምኑኝ፤ ካልኾነ ሕግ የምትጥሱ እናንተ ናችሁ፤ በግሩፕ ነው የምትሠሩት፤ ይኼ ቤተ ክርስቲያንን ያፈርሳል፤” ሲሉ የተከራከሯቸውን ብፁዓን አባቶች ተችተዋል፡፡

ብፁዓን አባቶችም፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን የማሻሻል ሐሳብ መሠረታዊ መነሻ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አሳሳቢ ብልሽት በየምልአተ ጉባኤው በተደጋጋሚ መነሣቱ መኾኑን ጠቅሰው፣ በተናጠል ከሚታይ ይልቅ አጠቃላይ ሕጉን በማሻሻል ማሕቀፍ ውስጥ ተካትቶ፣ በውይይቱ ሒደት ግን እንደ መግፍኤ ጎልቶ እንዲነሣ፣ አጀንዳን ባረቀቀው ኮሚቴ መግባባት ላይ በመደረሱ እንደኾነ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የልዩ ሀገረ ስብከት ድንጋጌ ያስከተለው ችግርና መፍትሔው፣ ለኹሉም ግልጽ በመኾኑና እንዲሻሻልም በቀደሙት መደበኛ ስብሰባዎች ተወስኖበት ያደረ ስለነበር፣ ምልአተ ጉባኤው ባመነበት ራሱን አስችሎ ማሻሻሉ፣ ውሳኔውን ማስፈጸም እንጂ ሕገ ወጥነት ተደርጎ በቅዱነታቸው መታየቱን ተከላክለዋል፡፡

የምልአተ ጉባኤው አባላት በዚህ መንፈስ ተራ በተራ ሐሳብ እየሰጡ ለኹለት ቀናት(ከጥቅምት 16 እስከ 18 ቀን) የተካረረ ውይይት ከተካሔደ በኋላ፣ የአዲስ አበባ የልዩ ሀገረ ስብከት ድንጋጌ እንዲሻሻል እና ራሱን ችሎ ሊቀ ጳጳስ እንዲመደብለት የጋራ አቋም ላይ መደረሱን ያስረዳሉ፡፡ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው እና ዝርዝር ማስፈጸሚያ ይወጣላቸዋል የተባሉ ሌሎች የሕገ ቤተ ክርስቲያኑን አናቅጽ ለይተው ከማሻሻያው ጋራ ለቀጣዩ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ የሚያቀርቡ፣ ሦስት ብፁዓን አባቶች(ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ እና ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ) እንዲሁም በውጭ የሚካተቱ የሕግ ባለሞያዎች ያሉበት ኮሚቴ ሠይሟል፡፡

ኾኖም፣ የልዩ ድንጋጌን ማሻሻል ፍጥጫ፣ በዚህ አልተቋጨም፡፡ ድንጋጌው ተሻሽሎ ሊቀ ጳጳሱ በምልአተ ጉባኤው ቢመረጥም፣ በሕጉ አንቀጽ 32 ንኡስ አንቀጽ 8 እና 9 መሠረት፣ የምደባውን(የሹመቱን) ደብዳቤ ፈርመው የሚሰጡት ቅዱስነታቸው ናቸው፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጡ ሕጎችን፣ የተላለፉ መመሪያዎችንና የተሰጡ ውሳኔዎችን ለሚመለከታቸው አካላት ለማስተላለፍ ባለባቸው ሓላፊነት፣ ሊቀ ጳጳሱ የሀገረ ስብከቱን አካውንት እንዲያንቀሳቅሱ፣ ለሚመለከታቸው ባንኮች ደብዳቤ መጻፍ ይኖርባቸዋል፡፡ የውሳኔ ቃለ ጉባኤው ለቅዱስነታቸው ሲቀርብላቸው ግን፣ “በውሳኔው ስለማልስማማ አልፈርምም፤” አሉ፡፡ የልዩነት ሐሳባቸው እንዲሰፍር፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሕግ ለመሥራትና ለማሻሻል ባለው ሉዓላዊ ሥልጣን በስምምነት የወሰነውን አክብረው እንዲፈርሙ ተጠየቁ፤ “ሥልጣኑ የእናንተ ነው፤ ወስኑ፤ እኔ ግን አልፈርምም!” ብለው ወይ ፍንክች አሉ፡፡ ይብሱኑ፣ “ጥዬ እሔዳለኹ፤ በኋላ እንዳይቆጫችኹ፤” ብለው አስጠነቀቁ፡፡

ይህን ጊዜ ምልአተ ጉባኤው፣ የሕግ ማሳሰቢያውን ትቶ ይማፀናቸው ገባ፡፡ የሹመት ቅድምና የዕድሜ እርግና ያላቸውን ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መርጦ ቃለ ጉባኤውን አስይዞ ከፊታቸው አቆመ፤ መላው የጉባኤው አባላትም ተነሥተው ቆሙ፡፡ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ(የስዊድንና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ) እና ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ከቅዱስነታቸው ፊት ቆመው፥ ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ መድኃኔዓለም እያሉ ውሳኔውን ተቀብለው በቃለ ጉባኤው እንዲፈርሙ፣ በሚያሳምን አቀራረብ አስተዛዝነው ለመኗቸው፡፡

“ይኼን ጊዜ መሸነፍ ይገባ ነበር፤” ያሉ አንድ ብፁዕ አባት፣ አሻፈረኝ ያሉት ቅዱስነታቸው ግን፣ “አላመንኩበትም፤ አልፈርምም!” በማለት መጽናታቸው፣ በተለይ በሃይማኖት ዐይን ሲታይ ጉባኤውን በእጅጉ ማሳዘኑን ተናግረዋል፡፡ በስብሰባ ሥነ ሥርዓት፣ የተቃውሞ አልያም የተዓቅቦ አቋም ማራመድ ቢኖርም፣ አስተዳደራዊ ጉዳይ እንደመኾኑ፣ ከተገኙት አባላት ከግማሽ በላይ በኾነ ድምፅ የተደገፈውንና ብዙኃኑ የተስማማበትን ሐሳብ አክብሮ ዕንቅፋት ከመፍጠር መቆጠብ ግዴታ እንደኾነ አስገንዝበዋል፡፡ ይህም ባይኾን፣ ታላላቅ አባቶች ከመላው ጉባኤተኛ ጋራ ቆመው ሲለምኗቸው አለመቀበላቸው እንዳስደመማቸው አልሸሸጉም፡፡  

ይህን ተከትሎ የተለያዩ የማስታረቂያ ሐሳቦች ከጉባኤው ተሰንዝረዋል፡፡ “ወቅቱ አይደለም፤ አጀንዳውን እናቆየው፤” ያሉ አሉ፡፡ የልዩ ድንጋጌው እንዳለ ኾኖ፣ ረዳት ሊቀ ጳጳሱን ምልአተ ጉባኤው ይመድብ፤ የለም ቅዱስነታቸው ይመድቡ፤ ብለው የተከራከሩ አሉ፡፡ በአንጻሩ፣ “ቤተ ክርስቲያን እንዳትከፈል፣ ወዳልኾነ አቅጣጫ እንዳንሔድ ወቅቱን መዋጀት ያስፈልጋል፤ እባካችኁ አናግሯቸው፤” ያሉ አባቶች፣ የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ተፈጻሚ መኾን እንዳለበት ቢያምኑም፣ ቅዱስነታቸውን ከስብሰባው ውጪም ቢኾን ሽማግሌዎችን ልኮ ማግባባት እንደሚያስፈልግ በመወትወታቸው፣ ብፁዓን አባቶች በጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ ሔደው ለማሳመን ሞክረዋል፡፡ ቅዱስነታቸው ግን እንደተለመደው፣ “ሐሳቤን አለወጥኹም፤ እንዲያውም እኔ መነኵሴ ነኝ፤ ምንም የምፈልገው ነገር የለም፤” ብለው መልሰዋቸዋል፡፡

ምልአተ ጉባኤው ሥራውን እየተወ ለአራት ተከታታይ ቀናት እየቆመ እንደለመናቸው የጠቀሱ ብፁዓን አባቶች፣ ቅዱስነታቸው በአቋማቸው የጸኑት፣ በዙሪያቸው ባሉ ሤረኞች እና ተጠቃሚዎች ክፉ ምክር በመኾኑ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ የሕገ ቤተ ክርስቲያኑን አንቀጽ 20 በመመርመር፣ ውሳኔውን አስከብሮ እንዲያስፈጽምና ወደ ሌሎች አጀንዳዎች እንዲሻገር አሳሰቡ፡፡ ሕጉ በአንቀጽ 20 ድንጋጌው፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ ጉባኤውን በርእሰ መንበርነት ስለማይመሩባቸው ምክንያቶች(የእርግና እና የጤና ችግሮች) አስፍሯል፡፡ ኾኖም ችግሩ፣ የቅዱስነታቸው የዐሳብ ልዩነት እንጂ በድንጋጌው የተጠቀሰው ባለመኾኑ፣ አንቀጽ 20ን ተፈጻሚ የማድረግ ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ታልፏል፡፡

“መንበራቸውን አልተጋፋንም፤ ሌላ ሰብሳቢ አልመረጥንም፤ ጥቅማጥቅማቸውን አልነካንም፤ እንደራሴ ወይም ዐቃቤ መንበር ይመረጥ አላልንም፤ እርስዎ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ነዎት እንጂ የአንድ ሀገረ ስብከት አይደሉም፤ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ያክብሩ ነው ያልናቸው፤ ወደ ሌላ ርምጃ ተኪዶ ነበር፤ ነገር ግን ቅዱስ ሲኖዶሱ አልተቀበለውም፤” ብለዋል፣ ለአራት ተከታታይ ቀናት ቅዱስነታቸውን በብዙ መንገድ ለማግባባት መድከማቸውን የተናገሩ ብፁዓን አባቶች፡፡

በመጨረሻም ምልአተ ጉባኤው፣ “የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አይቀለበስም፤ እየተባባሰ በመጣው ችግር የሀገረ ስብከቱ ችግር ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶሱ እየተተቸ መቀጠል የለበትም፤ ሕጉን የሠራው፣ ሕጉንም የማሻሻል ሥልጣን ያለው ቅዱስ ሲኖዶሱ ነው፤” በማለት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሕገ ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌ ማሻሻያ እና የሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ምደባ፣ ለአንድ ጊዜ ብቻ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ፊርማ ወጪ እንዲደረግ ተስማምቶ ወስኗል፤ የሚመለከታቸው አካላት እና የሥራ ሓላፊዎች እንዲያውቁት እንዲደረግም ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና ከቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ባሻገር፣ የሰላም ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የውሳኔው ግልባጭ ከደረሳቸው መካከል ይገኙበታል፡፡

ይኸው የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሰማቱን ተከትሎ፣ አንዳንድ የአድባራት አስተዳዳሪዎች በአንዳንድ የክፍላተ ከተማ ሥራ አስኪያጆች ቀስቃሽነት ለተቃውሞ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ የመሰለፍ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም፣ በፖሊስ መታገዳቸው ታውቋል፡፡ ለሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ፣ ትላንት በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ አቀባበል በተደረገበት ወቅት፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እና አንዳንድ የሀገረ ስብከቱ ዋና ክፍል ሓላፊዎች አለመገኘታቸው እያነጋገረ ይገኛል፡፡ ያም ኾነ ይህ፣ ምክሩ እና ጭንቀቱ በርግጥም ለቤተ ክርስቲያን በማሰብ ከኾነ፣ በድንጋጌው ማሻሻያ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተሰነቀው የተቋማዊ ለውጥ ተስፋ፣ እስከ አሁን ከተጓተተው በላይ እንዳይዘገይ፣ ኹሉም አካላት በቅን መንፈስ መተጋገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በዚኽ ረገድ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ በውሳኔው ማግሥት ያወጣው የድጋፍ መግለጫ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ራሱን ችሎ እንዲቋቋም እና በሊቀ ጳጳስ እንዲመራ መወሰኑ፣ ለሚጠበቀው የመዋቅር፣ የአደረጃጀት እና የአሠራር ለውጥ፣ አንድ እመርታ መኾኑን፣ አንድነቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ የብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ መመደብ ደግሞ፣ የላቀ ተስፋ አረጋጋጭ ኾኖ አግኝተነዋል፤ በማለት ድጋፉን ገልጿል፡፡ ብፁዕነታቸው፣ ቀደም ሲል በሀገረ ስብከቱ የቅዱስነታቸው ረዳት ሳሉ በነበራቸው ውስን ጊዜ፣ መሠረታዊ የአሠራር ለውጥን ለመተግበር ጥረት አድርገው እንደነበረ ኾኖም፣ የግልጽነት እና ተጠያቂነት መስፈን ሕገ ወጥ ጥቅማቸውን በሚያቋርጥባቸው የተደራጁ ሌቦች ጥልፍልፎሽ ተገትቶ፣ ብፁዕነታቸውም ከቦታው በድንገት መነሣታቸውን አስታውሷል፡፡

ይኹን እንጂ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የሀገረ ስብከቱን አጠቃላይ ችግር ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ የመፍትሔ ሐሳቦችን የሰነቁ፣ በሚመጥን የትምህርት ዝግጅታቸው፣ ዘመናዊ እና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ለመዘርጋት እና ለመምራት ዐቅም፣ ተነሣሽነት እና ቅንዓት ያላቸውን ሊቀ ጳጳስ፣ ዳግመኛ በሙሉ ሓላፊነት በዐዲስ አደረጃጀት መመደቡ፣ ከአጥቢያ ጀምሮ የተንሰራፋውን ብልሹ አሠራር፣ የሀብት ብክነት እና ዘረፋ፣ ጠርዝ የነካ ጎጠኝነት እና ወገንተኝነት፣ አድሏዊ አሠራር፣ የሥራ ዋስትና ማጣት፣ ምዝበራ እና አርኣያነት የጎደለው ክብረ ክህነትን ያስነቀፈ ኢክርስቲያናዊ ምግባር፣ በቁርጠኝነት ለማስወገድ እና የቤተ ክርስቲያንን ክብር ለማንበር በማለም መኾኑን እንደማይጠራጠር እምነቱን ገልጿል፡፡

ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅም፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ለሀገረ ስብከቱ ተቋማዊ ለውጥ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በማስተግበር፣ የአፈጻጸም ድክመቶችን ከመሠረቱ በማረም ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጡ፣ የልዩ ልዩ ሞያዎች ባለቤቶች የኾኑ አባላቱን በማስተባበር ሞያዊ እገዛን በትሩፋት ለማበርከት ዝግጁ መኾኑን አስታውቋል፡፡ የተቋማዊ ለውጡን ተግባራዊ አፈጻጸም እንደቀድሞው በማጨናገፍ፣ እኵይ ምዝበራቸውን ለማስቀጠል፣ ከአጥቢያ እስከ ሀገረ ስብከት ተሰግስገው በኔትወርክ የሚዶልቱ እና ዕንቅፋት የሚፈጥሩ የጨለማ ኃይሎችን እንደማይታገሣቸው፣ በይፋ በማጋለጥም ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው በጽናት እንደሚታገላቸው አስጠንቅቋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply