ለኢትዮጵያ ከተጠየቀው 3.24 ቢሊዮን የገንዘብ ድጋፍ 610 ሚሊዮን ቃል ተገባ

በኢትዮጵያ ላለው የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት በኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለም አቀፍ አጋሮች በተጠራው የገንዘብ ማሰባሰብ ሥነ ሥርዓት 610 ሚሊዮን ዶላር ተሰበሰበ።

ትናንት ሚያዚያ 8/2016 ዓ.ም. ጄኔቫ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ለ15.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ሕይወት አድን ድጋፍ ለማድረግ 3.24 ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር።

ይሁን እንጂ ከ21 ለጋሾች ማሰባሰብ የተቻለው 610 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።

የገንዘብ መዋጮውን ሥነ ሥርዓት ያዘጋጁት የኢትዮጵያ እና የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የተለያዩ አካላት ለቀረበው የገንዘብ ድጋፍ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡ እንጠብቃለን ብለው ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ጆይስ ምሱያ 20 መንግሥታት 630 ሚሊዮን ለመስጠት ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ዩናይትድ ኪንግደም 125 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃ ነበር።

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት በበኩሉ ለዜጎቹ የምግብ ድጋፍ ለማድረግ 250 ሚሊዮን ዶላር መድቢያለሁ ብሏል።

አሜሪካ ደግሞ 154 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ ብላለች።
የአውሮፓ ኅብረት ደግሞ የኅብረቱ አባላ አገራት 139 ሚሊዮን ዶላር ይለግሳሉ ብሏል።

እንደ ተመድ ከሆነ የሚሰበሰበው ገንዘብ በተፈጥረኖ እና በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን 15.5 ሚሊዮን ሕዝብ በ2024 መርዳታ ያስችላል።

ድርቅ፣ ጎርፍ እና ግጭት ሚሊዮኖችን ከቀያቸው ያፈናቀለ ሲሆን፣ በመጪዎቹ ከሐምሌ 2016 እስከ መስከረም 2017 መካከል የምግብ እጥረት የሚገጥማቸው ሰዎች ቁጥር 10.8 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል።

ለዓመታት በዘለቀ ጦርነት እንደ ትምህርት ቤት፣ ጤና ተቋማት፣ የውሃ መሠረተ ልማት የወደሙባቸው በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ደግሞ የምግብ እጥረቱ እየከፋ እንደሚሄድ የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል።

የመንግሥታቱ ድርጅት አስቸኳይ ድጋፍ ለሚፈልጉ ዜጎች ምላሽ ለመስጠት ለሚቀጥሉ አምስት ወራት 1 ቢሊዮን ዶላር የግድ ያስፈልገኛል ይላል።

ለመሰብሰብ የታቀደው 3.4 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረግ የሚችለው ለሚቀጥሉት 8 ወራት ብቻ ነው።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያን መንግሥትን ወክለው የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ፤ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚያጋጥማትን የምግብ እጥረት ለማስቀረት ትሠራለች ብለዋል።

አምባሳደር ታዬ በአየር ጸባይ ለውጥ ለሚከሰቱ ፈተናዎች ምላሽ ለመስጠት ዓለም አቀፍ ትብብር ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

ሚያዚያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

ኤትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጲያዊያን

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply