ለጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ቡድን ትንሽ ምክር – ነፃነት ዘለቀ

ነፃነት ዘለቀ ([email protected])

የለውጥ ጅምሮች ብዙውን ጊዜ ችግር አያጧቸውም፡፡ ከለውጡ እንጠቀማለን የሚሉ አካላት ደግሞ ጉጉታቸው ከፍተኛ ስለሚሆን የለውጡን እያንዳንዷን እንቅስቃሴ በንቃትና በጋለ ስሜት ይከታተላሉ፡፡ በዚህን ጊዜ የለውጡ ሞተሮችና ለውጡ የመጣላቸው ወገኖች እንደዬሁኔታው በቀላሉ ሊቀያየሙ ወይም ስምም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የለውጡ ዓላማ ግቡን ይመታ ዘንድ በለውጥ ጅምር ወቅት ከማንኛውም ወገን ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ የሚወዷቸውን ሰዎች ጨምሮ የተመዘገቡ ድሎችንም ማጣት ሊከሰት ይችላል፡፡

በኢትዮጵያችን የተጀመረው ለውጥ የአንድና የሁለት ግለሰቦች ግኝት እስኪመስል ድረስ ወደ አምልኮት የተጠጋ ሕዝባዊ ፍቅር ምጣዱ ላይ ለተደቀኑ ወገኖች ቢዥጎደጎድም በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህ እንደዐይናችን ብሌን በጥንቃቄ ልንይዘው የሚገባን የለውጥ እንቅስቃሴ በሥውር ፀረ-ለውጥ ኃይላት እየተጠለፈ ሕዝብን የሚያስከፉ ተግባራት በመታየት ላይ ናቸው፡፡ በበኩሌ አዲስ አበባ እምብርት ላይ ስለምውል የሕዝብን ስሜትና ፍላጎት የማንበብ ዕድል አለኝና ብዙ ነገር በመታዘብ ላይ እገኛለሁ፡፡ የሕዝብ አካል እንደመሆኔም የኔም ስሜትና ፍላጎት ከአብዛኛው ሕዝብ ጋር ይመሳሰላል፡፡

ይህ ለውጥ የተከሰተው በሁሉም ዜጎች ርብርብ መሆኑን በቅድሚያ መረዳት አለብን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እዳር ተንቀሳቅሶና ብዙ ልጆቹን ገብሮ ያመጣውን ይህን ለውጥ በሆነ ምክንያት አንዳንድ ኃይሎች መስመሩን ቢያስቱት መቼም ወደማንወጣው አዘቅት ወርደን እንደምንፈጠፈጥ ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል፡፡ እንኳንስ እጅግ በርካታ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ያሉብን እኛ እንቅርና የኛን ያህል የተወሳሰበ ችግር የሌለባቸው እነለቢያንና ኢራቅን የመሳሰሉ ሀገሮች እንኳን አንዴ ከገቡበት የመከራ አዙሪት መውጣት አቅቷቸው እዛው አረንቋ ውስጥ እየተንደባለሉ ለመኖር ተገደዋል፡፡ ስለዚህ “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ በሀገራችን እየታዩ ያሉ ለውጡን አደናቃፊ ችግሮችን ሥር ሳይሰዱ ማረም ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ አዲሶቹ አመራሮችም “ሕዝብ ምን ይላል?” የሚለውን የቀደምት ነገሥታት የአስተዳደር ዘይቤ በመከተል የሕዝብን ስሜት ማጤንና በየቀኑ ለሚበቅሉ ችግሮችም ሳይስፋፉ በቶሎ መፍትሔ መፈለግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አለበለዚያ የዛሬ ሆይ ሆይታና ብርቱ የሕዝብ ድጋፍ ውሎ ሳያድር እንደጤዛ ሊረግፍ እንደጉምም በንኖ ሊጠፋ ይችላል፡፡ አንድን ነገር ለመጥላት የሚወስደው የጊዜ ርዝማኔ ደግሞ ለመውደድና ለማፍቀር ከሚወስደው ጊዜ በእጅጉ እንደሚያጥር ልብ ማለት ተገቢ ነው – ፍቅር ኃይል ነው፤ አያያዙን ካላወቅነው ግን ይህም ኃይል ይዝልና አቀበትን ማስወጣት ቀርቶ ቁልቁለትን ማስወረድ የማያስችል ልፍስፍስ ይሆናል፡፡ ስለሆነም አሁን ባለው ሕዝባዊ ደጀንና ሁለንተናዊ ድጋፍ ፀረ-ለውጥ ኃይላትን ማቆምና ወደ ትክክለኛው ጎዳና እንዲገቡ ማድረግ ካልተቻለ ዳፋው በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ፈረንጆች Hit the iron when it is hot የሚሉት ወደው አይደለም፡፡ በሌላም በኩል “የየጁ ደብተራ ቅኔው ቢጎድልበት ቀረርቶ ጨመረበት” እንደሚባለው መሪዎች የሕዝብ ፍቅርና ውዴታ ሲያጥራቸው ወደ ዱላ እንደሚዞሩ የታወቀ ነው፡፡ ያ ግን መጨረሻው እንደማያምር በገዛ ሀገራችን የረጂም ዘመን ታሪክ በግልጽ የተረዳነው ነው፡፡ ዛሬ አንበርክከህ የምትገዛው ሕዝብ ቀን ጠብቆና በውስጡ ተጠናክሮ ነገና ከነገ ወዲያ ድባቅ ይመታሃል፤ መከራ ሲመጣብህም ብቻህን አጋልጦ ይሰጥሃል፡፡ ደርግን ማስታወስ ብቻ በቂ ነው፡፡ የሕዝብ ድጋፍ የተለዬው ደርግ የወደቀው በወያኔ ብቻ እንዳይመስለን፡፡

አሁን እየታዩ ካሉ የአካሄድ ስህተቶች ውስጥ የሚከተለውን ለአብነት እንመልከት፡፡

የአንድን ብሔር የበላይነት በሌላ ብሄር የበላይነት መተካት ሀገርንና ሕዝብን ወደ ነፃነት አያመራም፡፡ ሐጎስን በፈይሣ ወይም አምበርብርን በዘበርጋ መተካቱ ብቻውን ችግርን ያወሳስብ እንደሆነ እንጂ መፍትሔ አይሆንም፡፡ አሁን እያስተዋልን ያለነው የፈጠጠ እውነታ ይህንን የሚመስል ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ከጠበቅሁት በፍጹም የተለዬ ነገር ገጥሞኝ በጭንቀት ላይ እገኛለሁ፡፡

ሃይማኖትና ዘር ሳይገድበው የአዲስ አበባና አካባቢዋ ሕዝብ መስቀል አደባባይን ሞልቶ እንዲያ በደስታ ሲቃ በዕንባ እየተራጨ – ሕይወቱንም በመገበር ጭምር –  ዶ/ር ዐቢይንና እርሳቸው የሚመሩትን ለውጥ የደገፈው የፌዴራል የሥልጣን ቦታዎች ከሕወሓት ወደ ኦህዲድ እንዲዛወሩ ፈልጎ አይመስለኝም፡፡ የዚያ ሁሉ ደስታና ፈንጠዝያ መሠረታዊ ምክንያት ላለፉት 27 ዓመታት በሕዝብ ላይ ተጭኖ የነበረው ፈርዖናዊ አገዛዝ ጋብ ብሎ በፍቅርና በርቱዕ አንደበት ሀገርን ለማስተዳደር ጥሩ ተስፋና አበረታች ጅማሮ ከጫፍ አካባቢ በመታየቱ ነበር፡፡ ያን ተስፋ የሚያጨልም ማንኛውም ነገር በእንጭጩ ካልተቀጨ የሕዝብ ጠላቶች ሌላ ዕድል ያገኙና ወደነበርንበት የጨለማ ዓለም ሊመልሱን ይችላሉ፡፡ ህልም እልም ወገኖቼ! ያለንበት መስቀለኛ መንገድ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ ፈጣሪ ፊቱን ከኛ አይመልስብን እንጂ አህያን ተጠልለው የሚመጡብን ጅቦች አንዳች ጠባብ ዕድል ካገኙ ዘነጣጥለው ይጨርሱናል – ብሂሉ “አህያን ተገን አድርገው ጅብን ይመቱ” እንዲል፡፡ የክፋት አምባሳደሮች ደግሞ የማይሸጎጡበት ጎራ የለም፡፡ ጤፍ በሚቆላ አፋቸው እያታለሉ ህግንና ዐዋጅን እስከማሻርና ማጸደቅ የሚደርስ አጋጣሚን ያገኛሉ፡፡

ብዙ የኃላፊነት ቦታዎችን እየወሰዱ ያሉት እውነቱን ለመናገር የኦሮሞ ብሔር አባላት ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ የከተማችን ትኩስ ወሬ የሆነው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ሹመት ብዙ እያነጋገረ ነው፡፡ ካልጠፋ ሰው ይህ ክስተት መታየቱ በብዙ ጥያቄዎች ወጥሮናል፡፡ ወሬው ሁሉ “አዲስ አበባ ምን ያህል በተማረ ሰው ዕጦት ምች ብትመታ ነው የአንዲት መንደር ከንቲባ ሊሾምላት የቻለው?” የሚል ነው፡፡

እውነትንና እውነትን ብቻ እንነጋገር፡፡ ምንም ዓይነት አመክንዮ ወይም ምክንያት ይደርደር – ኢንጂኔር ታከለ ኡማ የተባሉ ግለሰብ ህግን በተላለፈ ሁኔታ ከሱሉልታና ከሰበታ ትናንሽ መንደሮች ተነስተው በቀጥታ የአዲስ አበባ ከንቲባ መሆናቸው ጤናማ የለውጥ እንቅስቃሴን አያመለክትም፡፡ ስለኚህ ሰውዬ አንዳንድ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ሞክሬያለሁ፡፡ እውነቱ ሌላ ቢሆንም ሰውዬው ከሙስና የፀዱ ናቸው ብለን እንመንላቸው – ግዴለም፡፡ ነገር ግን “አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት” በሚል ፍልስፍናቸው የሚታወቁ ግለሰብ በዚህን ወቅት መሾም አዲስ አበቤዎችን ምን ያህል ሊያስደስት ወይም ሊያስከፋ እንደሚችል ግምት ውስጥ መግባት ነበረበት፡፡ አዲስ አበባን በዘርና በጎሣ መቦደን ደግሞ የሚቻል አይመስለኝም – አዲስ አበባ የሁሉም እንጂ የማንም ልዩ አንጡራ ሀብት ልትሆን አትችልም፡፡ በመሠረቱ አንድን ቦታ “ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ አማራ….” እያሉ ለግዑዝ ነገር የጎሣና የነገድ ታርጋ መለጠፍ ፋሽኑ ሊያልፍበት ይገባል – አዲስ አበባን “የነእገሌ/የነእገሊት” ብሎ መፈረጅ በተለይ በዚህን የሥልጣኔ ዘመን ከአንድ ፊደል ቆጠረ ከሚባል ወገን የማይጠበቅ ፍጹም ነውር ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሥፍራ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የእኩል ሀብት ነው፡፡ ይህን የሕዝብ መብት እየነፈግን እስከመቼም መቀጠል አንችልም፡፡ ወልቃይትንና ራያን ተመርኩዞ የመጣብንና እስካሁንም ድረስ አሣራችንን እያበላን ያለው አንድን ቦታ “የኛ ነው፣ የነሱ ነው” የማለት ችግር ካልተወገደ ሀገር ሰላም አትሆንም፡፡ ማንኛውም ዜጋ በፈለገው የሀገራችን ክፍል ተዘዋውሮ መሥራት፣ መኖርና ሀብት ንብረት ማፍራት ካልቻለ ወያኔ ያስታቀፈን የቤት ሥራ እንደተጫወተብን እንኖራለን – ከወያኔ የተሻለ አስተሳሰብ ካልመጣ ውድቀታችን የከፋ ይሆናል፡፡ ከሕወሓት ትብታብ እንውጣ ብለን ካሰብንና ከቆረጥን ደግሞ ወያኔዎች የጣሉብንን የዘረኝነት ደንቃራ ጠራርገን መጣል አለብን፡፡ ከዚህ ነጥብ አንጻር ኢንጂኔር ታከለ ይህን “አዲስ አበባ የኦሮሞ ነች” የሚል ለኔ ቅዠት መሰል አስተሳሰብ ጥለውት ከሆነና ተቀይረው ከሆነ መልካም ነው፡፡ ከነዚሁ አስተሳሰባቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ ግን ዛሬ ባይሆን ነገ ሊከሰት የሚችል ችግር አብሯቸው እንዳለ ማመን አይከብድምና ሹመቱ አደጋ አለው፡፡

አንድ አጋጣሚ ሲፈጠር ያንን አጋጣሚ ከተፈለገው ዓላማ ውጪ ሊጠቀምበት የሚፈልግ አካል መኖሩ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በነዶ/ር ዐቢይ ቡድን ውስጥ መሽጎ የለውጡን ባቡር በሌላ አቅጣጫ በመዘወር ድብቅ ተልእኮውን መወጣት የሚፈልግ ኃይል ሊኖር እንደሚችል በተለይ ዶ/ር ዐቢይ ሊገነዘቡና ተገቢውን የእርምት እርምጃ ሊወስዱ ይገባል፤ “የገበያ ግርግር ለቀጣፊ ያመቻል” ይባላል፡፡ ይቺ ኦሮሞ ኦሮሞ የምትባል ነገር ደግሞ ግዘፍ እየነሣች የሕዝብንም ሰላም እየነሳች ነውና ይታሰብባት፤ “የጋላቢ መቀየር የፈረስና በቅሎን ድካም አያስቀረውም”፡፡ ሰሞኑን በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች እየተዘዋወርኩ የሕዝብን ስሜት ስቃኝ በዚህ ሌሎችን እያገለለ ኦሮሞን ወደ ትላልቅ የሥልጣን እርከኖች የማውጣት ጉዳይ ብዙዎች ቅስማቸው ተሰብሯል – ከድጥ ወደ ማጥ የመሄድ ያህል የተሰማቸውም አሉ፤ ለለውጡ ኃይሎች ላደረጉት ልባዊ ድጋፍ የተቆጩም ገጥመውኛል – ቀድሞ ማመስገን ለኋላ ወቀሣ እንደማያመች ደግሞ የታወቀ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ማንኛውም ዓይነት አክራሪነትና ጽንፈኝነት ጎጂ ነው፡፡ አንድን ዘውግ ብቻ ያማከለ የሀብትም ሆነ የሥልጣን ክፍፍል ዞሮ ዞሮ የሚያስከትለው ጉዳት  በቀላሉ ሊታይ አይገባምና ይህን መሰሉን አካሄድ ቆም ብለን ብናስብበት የተሻለ ነው፡፡ ባለፈው ስለተጎዳንበት ወደዚያ መመለስ አይገባንም፡፡ ወያኔዎች ራሳቸውስ እንዴት ይታዘቡን? በፈጸሙት ዘረኛ የአፓርታይድ አገዛዝ እንዳይጸጸቱ ዕድሉን እየነፈግናቸው እኮ ነው! “እኛስ ከዚህ በላይ ምን አደረግን?” ማለታቸው ይቀራል? እውነት ነው፡፡

በነገራችን ላይ በሥልጣን ላይ አማራን አስገቡ እያልኩ አይደለም፡፡ በጭራሽ፡፡ አማራ ሥልጣን መያዙ ይቅርበትና ቀን የሰጠው ማንም ወገን በወጉ ይግዛው፤ አማራ ጥያቄው – እንደሚመስለኝ – “አራት ኪሎን ልቆጣጠር” ሣይሆን “በጋራ ሀገራችን አንዱ አሳዳጅ ሌላው ተሳዳጅ መሆኑ ቀርቶ እንደሰው ልቆጠርና በአግባቡ ልገዛ፤ በቅጡ ልዳኝ! የዘር መድሎና ዘር ላይ ያነጣጠረ ፍጅት ይቅር!” ነው፡፡ “የአማራው ችግር የሚመለከታችሁ ወገኖች እባካችሁን አማራው ጽድቁ ይቅርበትና በቅጡ ኮንኑት” የሚለው የኔም የእግረ መንገድ መልእክት ነው፡፡ በሌላም ወገን የተማረና ችሎታ ያለው ከሌሎች ዘውጎችና ነገዶችም እየተወዳደረ የኃላፊነት ቦታ ይያዝ፡፡ ኢትዮጵያ ያሏት ብሔሮች ሦስት ብቻ አይደሉም፤ አንዳንድ የዋሃን እነዚህ ሦስቱ ብቻ ይመስላቸዋል የኢትዮጵያ ዜጎች፡፡ የተማረ አፋርና ሶማሌ፣ የተማረ ጀምጀምና ጋሞ፣ የተማረ ጉራጌና ደራሳ፣ የተማረ ወይጦና ኮንሶ፣ የተማረ አኙዋክና ሃዲያ፣ የሰለጠነ ኣሪና ሙርሲ፣ የሠለጠነ ከምባታና ሲዳማ…. ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነውና በነገዱ የአኀዝ ማነስ መብዛት ወይም በሌላ ምክንያት ከሥልጣን አይገፋ፡፡ ጎሣው ሣይሆን ትምህርቱና ችሎታው እየታዬ – በሚቀመጡ መሥፈርትም እየተወዳደረ – በገዛ ሀገሩ ይሥራ፡፡ አሁንና እስካሁን በተያዘው የእከክልኝ ልከክልህ መንገድ ግን ገደል እንጂ ሥልጣኔ አይገኝም፡፡ በጎሣና በሃይማኖት ወይም በአብሮ አደግነትና በዝምድና ቅርርብ ሰውን ለሹመትም ሆነ ለሥራ ዕድገት ማጨት በጣም ያረጀ ያፈጀ የአስተዳደር ሥልት ነው፡፡ በአእምሮ አድጎ መገኘትን የመሰለ መልካም ነገር የለም፡፡ በተጨማሪም በሃይማኖትና በዘውግ ወይም በቋንቋ መደራጀት ወይም ፓርቲ ማቋቋም በሕግ የተከለከለ ይሁን፡፡ ሰውነትና ዜግነት ብቻ በቂ ናቸው፡፡ ድመትና ዐይጥ፣ ውሻና ዝንጀሮ፣ አንበሣና ሚዳቋ … በእንስሳት መኖሪያዎች (Zoos) ውስጥ የአጥፊና ጠፊ ተፈጥሯዊ ባሕርያቸውን ረስተው በፍቅር ሲጫወቱና ሲላፉ እያየን የአንድ አዳም ዘር የሆን ሰዎች በትርኪ ምርኪ ሰበብ አስባቦች ልንጨራረስ እንደማይገባን እንረዳና በአንዲት ሀገራችን በሰላም እንኑር፡፡… እንደዚህ ያለ አስታራቂ ሃሳብ መናገር ደግሞ ኃጢኣትም ሆነ ወንጀል ሊሆን አይገባም፡፡(የዚህ አንቀጽ የመጨረሻ ዐረፍተ ነገር ይችን ጽሑፍ ላላስተናገዱልኝ የስም ነፃ ፕረሶች መታሰቢያ ትሁንልኝ፡፡)

አሁንም ቢሆን ብዙም አልዘገየም፡፡ እንደኔ አስተሳሰብና እምነት የሕዝብን ስሜት በመከተል ይህን የኦህዲድና ምናልባትም የኦነግ የይሉኝታን ድንበር የዘለለ ተፅዕኖ በአፋጣኝ ማስተካከል ይቻላል፤ ይገባልም፡፡ ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ አሰላለፎችን ሁሉ እስከመቀያየር ይደርሱና መልካም ጅምሮች በቀላሉ መስመር ሊስቱ ይችላሉ፡፡ አንዴ መስመር ከሳቱ ደግሞ ማጣፊያው ወደሚያጥረን አጣብቂኝ ውስጥ እንገባና የፈነጠቀልን የነፃነት ጮራ በአጭሩ ሊቀጭ ይችላል፡፡ በውጤቱም ሕዝብ ተስፋ በመቁረጥ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሄዶ የተዳፈኑ የሚመስሉ ችግሮች ፈንድተው የፈራነው ሁሉ መድረሱ አይቀር ይሆናል፡፡ የለውጡ ኃይል ጀግና ይሁንና ኢንጂኔር ታከለ ኡማን በአፋጣኝ ከም/ከንቲባነት ቦታው ያንሳ! የተዛቡ የሹመት አካሄዶችንም በቶሎ ያርም፤ የሕዝብን ስሜት ከየሚዲያው በመቃረም ችግሮችን በአፋጣኝ ለማስተካከልና ለሕዝብ የገባውን ቃል እውን ለማድረግ ይሞክር፡፡ ለወደፊቱም ሹመት ሲሰጥ በኮታና በዘር ሣይሆን በሙያ ብቃትና በትምህርት ይሁን፡፡ ለምሣሌ የቴሌ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበረው አንዷለም አድማሴ የሄርቃ ኃላፊ ሆኖ ተመድቧል፡፡ ሰውዬው አንድ ቦታ ማግኘት ስላለበት ነው ወይንስ ሥራውን ይችለዋል? ስለአትክልት የተማረን ሰው ብረት ላይ መመደብ፣ ስለእንጨት የተማረን ሰው ጤና ቢሮ ላይ መመደብ፣ ስለህዋ የተማረን ሰው ውጭ ጉዳይ መመደብ…. አግባብ አይደለምና ምደባዎች እየተስተዋሉ ይከናወኑ፡፡ ሰውን ለማስደሰት ወይ ለማስከፋት የሚደረጉ ነገሮች ካሉም ተገቢ አይደሉምና ይቅሩ፡፡ ሰው አለሙያው በመመደቡ እንዳያዝን፣ ሥራም እንዳይበደል ጥረት ይደረግ፡፡

 የጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ልፋትና ድካም ባልተገባ ጣልቃ ገብነት ሊኮላሽና ሕዝባዊ ድሉ በሸማቂዎች ሊነጠቅ አይገባም፡፡ የምንደፋው ዳቦ ሁሉ እያረረ ዕድሜ ልካችንን እዬዬ ስንል መኖርም ይብቃን፡፡ እርግጥ ነው ሕወሓት ዱሮ እንዲህ ይል ነበር – “ እኛ ኢትዮጵያን መግዛት ቢያቅተን ለኦሮሞ አስተላልፈን እንሄዳለን፡፡” አሁን ያለው ሁኔታ ግን – በተለይ ለውጡ ከተጀመረ አንስቶ ሦስት ወራትን እስኪያልፍ ድረስ – ይህን “ትንቢት” የተከተለ አይመስልም ነበር፡፡ አሁን አሁን ገባ ብለን ስንመረምር ታዲያን አንዳንድ ምልክቶች ጥሩ አይደሉም – የወያኔን ቀዳሚ “ትንቢት”ም ንቀን እንዳንተወው የሚያደርጉ ሁኔታዎችን እየታዘብን ነው –  እነዚህ ተግባራት ደግሞ የዶ/ር ዐቢይን ይሁንታ ማግኘት አለማግኘታቸውን ማወቅ ያስቸግራል፡፡ በበኩሌ እርሳቸው በዚህን መሰል ተራ የአስተሳሰብ ደረጃ ይገኛሉ ብዬ ማመን አልፈልግም፡፡ ትንቢቱን በሚመለከት ግን ለምሣሌ ኤርምያስ ለገሠ ሰሞኑን በጻፋት አንዲት አጭር ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው የኦነግ አባላት በሸራተን አዲስ በቀን አምስት ሸህ ብር ገደማ ወጭ እየተደረገላቸው በሕወሓት አባላት የሚቀማጠሉበትን አካሄድ ስንመለከት ብዙ ነገር እንድንጠራጠር ቢያደርገን አይፈረድብንም – ይህንንም ጉዳይ አዲሱ መንግሥት አያውቀውም ማለት ይከብዳል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለጥርጣሬ በጣም ክፍት ነውና ፈጣሪ ካልታደገን የሚደገስልን ድግስ ሁሉ በአወንታዊነት አጥጋቢ ነው ማለት አንችልም፡፡ ይሁዳ ክርስቶስን በ30 አላድ እንደሸጠው ሁሉ የኞች ናቸው የምንላቸው ወገኖቻችንም ረብጣ ገንዘብ ካገኙ እኛን ለመቸብቸብ ዐይናቸውን የሚያሹ አይመስለኝም፡፡ የሀገር ስሜትና የወገን ፍቅር ተሟጦ ከሰውነት ወጥቶ ባለበትና ሆዳምነት በነገሠበት በዚህን ወቅት ብዙ ነገር መጠርጠር ተገቢ ነው፡፡ በተረቱስ “ጠርጥር ገንፎም አለው ስንጥር!” ይባል የለም? ለማንኛውም በአዲሱ ጸሎት ልለይ፡- እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ፤ ከዳግም ሀዘንና እንግልትም ይታደገን፡፡ አሜን፡፡

Leave a Reply