#ለጤናዎ #ጥቂት ስለ የአንጀት መታጠፍ የተለመደዉ የአንጀት ስራ መስተጓጎል የአንጀት መታጠፍ ይባላል፡፡ምግብ በጨጓራ ከተፈጨ በኋላ ወደ ትንሹ እና ወደ ትልቁ አንጀት ደርሶ ኬሚካሎቹ ተመጠዉ…

#ለጤናዎ
#ጥቂት ስለ የአንጀት መታጠፍ

የተለመደዉ የአንጀት ስራ መስተጓጎል የአንጀት መታጠፍ ይባላል፡፡

ምግብ በጨጓራ ከተፈጨ በኋላ ወደ ትንሹ እና ወደ ትልቁ አንጀት ደርሶ ኬሚካሎቹ ተመጠዉ ተረፈ ምርቱ መወገድ አለበት፡፡

ይህ የአንጀት ስራ መስተጓጎል ካጋጠመዉ ታዲያ አንጀት ታጥፏል እንላለን፡፡

#የአንጀት መታጠፍ ብዙ ጊዜ የመከሰት ዕድል አለዉ፡፡

ከትርፍ አንጀት ቀጥሎ ድንገተኛ የቀዶ ህክምና የሚያስፈልገዉ የህመም ዓይነት ነዉ፡፡

 በዚህ ጉዳይ ላይ ታዲያ ጣቢያችን ኢትዮ ኤፍኤም 107.8 አጠቃላይ የቀዶ ህክምና እና የትልቁ አንጀት ቀዶ ህክምና ሀኪም ከሆኑት ከ ዶ/ር ቢንያም ዮሀንስ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
 በቆይታችንም ዶ/ር ቢንያም ያነሷቸዉን ነጥቦች በዝርዝር አቅርበንላችኋል፡፡

#አንጀት በምን ምክንያት ሊታጠፍ ይችላል?

ምክንያቶቹ የትኛዉ የአንጀት ክፍል እንደታጠፈ የሚለዩ ናቸዉ፡፡

ብዙ ጊዜ ትንሹ አንጀት የሚታጠፈዉ በ‹‹ቦዓ›› ምክንያት ነዉ፡፡ በሰዉነታችን ዉስጥ ያሉ ክፍተቶች ዉስጥ ትንሹ አንጀት ወደ ዉጪ ይወጣ እና ሊዘጋ ይችላል፡፡

ሌላ ደግሞ ከቀዶ ህክምና በኋላ የሚኖር ጠባሳ ነዉ፡፡ በተለይ ደግሞ ከወሊድ በኋላ ፣ ከማህጸን ዕጢ ቀዶ ህክምና፣ ትልቁ አንጀት ላይ የሚደረጉ ቀዶ ህክምናዎች አብዛኛዎቹ የመጨረሻ ዉጤታቸዉ ሆድ ዕቃ ዉስጥ የሚፈጠር ጠባሳ ነዉ፡፡ ይህ ደግሞ ትንሹ አንጀትን የመዝጋት ዕድላቸዉን ከፍ ያደርገዋል፡፡

ሌላኛዉ እና ብዙም ያልተለመደዉ ምክንያት ትንሹ አንጀት እራሱ ላይ መሽከርከር ወይም መጠቅለል ነዉ፡፡

በዓለም ዓቀፍ ደረጃም ሆነ በአገራችንም እየጨመረ የመጣዉ የትልቁ አንጀት ካንሰር ደግሞ ሌላዉ ምክንያት ነዉ፡፡

#ምልክቶቹ ምንድናቸዉ?

የተለመዱ አራት ዓይነት ምልክቶች አሉት፡፡

የመጀመሪያዉ የሆድ መነፋት ነዉ፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ ሆድ የመነፋት እና ዉጥርጥር የማለት ስሜት ይኖራል፡፡

ሁለተኛዉ ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ ሲሆን ብዙ ጊዜ የበላነዉን ምግብ ሊያስመልሰን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ሀሞት ሊያስመልሰንም ይችላል፡፡

ሶስተኛዉ ምልክት ሰገራ እና አየር ማስወጣት እምቢ ማለት ወይም ማስቸገር ነዉ፡፡

አራተኛዉ ምልክት ደግሞ የሆድ ቁርጠት ነዉ፡፡ የሆድ ቁርጠቱ አይነት ታዲያ እንደሚነሳበት የአንጀት ክፍል ይለያያል፡፡

ከትንሹ አንጀት የሚነሳ ከሆነ ቶሎ ቶሎ የሆድ ቁርጠት ይኖራል፡፡ ከትልቁ የአንጀት ክፍል ሲነሳ ደግሞ አልፎ አልፎ አረፍ እያለ ቁርጠት የሚኖር ይሆናል፡፡

#አጋላጭ ሁኔታዎች ምንድናቸዉ?

ከዚህ በፊት የነበረ ቀዶ ህክምና

የተለያዩ አደጋዎች

የጨረር ህክምና መዉሰድ

ወንድ መሆን

ጉልበት የሚጠይቁ ስራዎችን ማብዛት የተለመዱ አጋላጭ ሁኔታዎች ናቸዉ፡፡

#ከአጋላጭ ሁኔታዎች እንዴት ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን?

ከዚህ በፊት የሆድ ዕቃ ቀዶ ህክምና ያደረጉ ሰዎች ከሆኑ ቁርጠት፣ ማስመለስ በሚኖር ሰዓት በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል፡፡

#ህክምናዉ ምን ይመስላል?

ታካሚዉ ወደ ባለሙያ ሲቀርብ ማስመለስ፣ ቁርጠት ፣ ሆድ መነፋት ስለሚኖረዉ ይህንን ለማስታገስ የተለያዩ መድሃኒቶችን ይወስዳል፡፡

ሆዱን ለማስተንፈስ በአፍንጫ በኩል የሚገባ ቱቦ ከተደረገ በኋላ በደም ስር በኩል የጸረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች የሚሰጡ ይሆናል፡፡

ከዛ በኋላ ለቀዶ ህክምና ዝግጁ ሲሆን የታመመዉ የሰዉነት ክፍል በህክምና የሚወገድ ይሆናል፡፡

#ልብ ማለት ያሉብን ጉዳዮች

ትልቁ አንጀት ላይ የሚከሰቱ የአንጀት መቆላለፎች በጊዜዉ ህክምና ካላገኙ እና አንጀት መበስበስ የሚያመጡ ከሆነ ለተወሰነ ጊዜ የሚቆይ በሆድ ዕቃ በኩል የሰገራ ማስተንፈሻ የሚሰራ ይሆናል፡፡
እስከዳር ግርማ

ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply