“ለፍጻሜው ምክንያት እንሁን”—ቤተ-ክርስቲያኗቤተክርሲቲያኗ በእድሳት ላይ ለሚገኝው የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠየቀች። እድሳ…

“ለፍጻሜው ምክንያት እንሁን”—ቤተ-ክርስቲያኗ

ቤተክርሲቲያኗ በእድሳት ላይ ለሚገኝው የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠየቀች። እድሳቱ አሁን ላይ 75 በመቶ ደርሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት የካቴድራሉን ህንጻ ለሚያከናውነው ኮንትራክተር ክፍያ ለመፈጸም በቂ ገንዘብ እንደሌላትም ጨምራ ገልጻለች፡፡

በመሆኑም ይህን ታሪካዊ ህንጻ እድሳቱን ለመጨረስ ኢትዮጵያዊያን ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ነው ቤተክርስቲያኗ ጥያቄ ያቀረበችው፡፡

በዕድሜ እርዝማኔ ምክንያት በቤተክርስቲያኗ ህንጻ ላይ ውስጣዊ እና ውጪዊ አካሉ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ለችግር የሚያጋልጠው ሆኖ በመገኘቱ እድሳት እንዲደረግለት መወሰኑ ይታወቃል፡፡

ቤተክርስቲያኑን ለማደስ 18 ወራት ያህል ጥናት እንደተደረገም ተገልጿል።

በጥናቱ ውጤት መሰረት እድሳቱ አሁን ላይ እየተካሄደ ይገኛል።

ካቴድራሉ ህንጻውን ከሚያድሰው ቫርኔሮ ከተባለ ድርጅት ጋር ውል ገብቶ እድሳቱ በመገባደድ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።

ካቴድራሉ ህንጻውን ለማደስ 172 ሚሊዮን ብር የስራ ውል ስምምነት መፈጸሙንም ገልጿል።

ሆኖም ካቴድራሉ ክፍያ የሚፈጽመው ከምእመናን ከሚሰበስበው ገንዘብ ብቻ በመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች ለኮንትራክተሩ ክፍያ ለመፈጸም መቸገሯን ቤተክርስቲያኗ አስታውቃለች፡፡

የህንጻው እድሳት ለማጠናቀቅ 85 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግም ነው የተነገረው።

የካቴድራሉ የገቢ ምንጭ በዋናነት ከምእመናን የሚሰበስብ ሲሆን የካቴድራሉ የእለት የወርና የአመት የተለያዩ ወጪዎቹን የሚሸፍነውም በዚህ መልክ ነው ተብሏል።

እድሳቱ ሲጀመር በባንክ የነበረው 500ሺህ ብር ብቻ እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን፣ እስካሁን ምእመናን በሚለግሱት ገንዘብ ሲሰራ እንደነበረ ነው የተገለጸው።

እድሳቱ አሁን ላይ 75 በመቶ የደረሰ ሲሆን እስካሁን 90ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉም ተነግሯል።

በመሆኑም የህንጻ-ቤተክርስቲያኑን እድሳት ለመጨረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ካቴድራሉ ጠይቋል።

የህንጻው እድሳት ከሶስት ወር በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን በሁሉም ባንኮች በአጭር ቁጥር 7829 ማስገባት እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል

ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply