ለ12 ዓመታት በእስር የተንገላቱት እና በኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር (ኢሕአግ) ተሰልፈው በአባልነት ብሎም በአመራርነት ተጋድሎ ያደረጉት አርበኛ ወርቁ በለጠ አርፈዋል። አማራ ሚዲያ ማዕ…

ለ12 ዓመታት በእስር የተንገላቱት እና በኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር (ኢሕአግ) ተሰልፈው በአባልነት ብሎም በአመራርነት ተጋድሎ ያደረጉት አርበኛ ወርቁ በለጠ አርፈዋል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 25 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች የአስተዳደር መምሪያ ሃላፊ እና ም/ሊቀመንበር ሆነው የታገሉት እና ለ12 ዓመታት በህፍ እስር የተሰቃዩት አርበኛ ወርቁ በለጠ ማረፋቸውን ከአርበኞች ግንባር የተሰኘው በአርበኞች ማንነትና ተጋድሎ ላይ መረጃ የሚያጋራው የማህበራዊ ትስስር ገጽ በሚከተለው መልኩ ገልጾታል:_ የአርበኛ ወርቁ በለጠ አጭር የህይወት ታሪክ! አርበኛ ወርቁ በለጠ ከአባታቸው በለጠ ደሳለኝ ከእናታቸው ወ/ሮ አያልነሽ የኋላሸት ሰንደቄ በጎንደር አምባጊዮርጊስ በ1951 ዓ/ም ተወለዱ። እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በትውልድ አካባቢያቸው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ሃገራቸውን በውትድርናና በፖሊስ ኮሚሽን ስር ሆነው በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች አገልግለዋል። አርበኛ ወርቁ በለጠ ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ። አርበኛ ወርቁ በአዲስ አበባ ፖሊስ ሃላፊ ሆነው ያገለግሉበት ተቋም የተበላሸ አሰራርና የኢህአዴግን አገዛዝ በመቃወም በ1994 ዓ/ም የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባርን ተቀላቀሉ። በኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር የትግል ጊዜያቸው በተለያየ ቦታ አገልግለዋል። በትግሉ የአስተዳደር መምሪያ ሃላፊ እና ም/ሊቀመንበር ሆነው የታገሉበት ተጠቃሽ ናቸው። በመሪነት፣ በታጋይነትና አታጋይነት በቆዩባቸው ጊዜያት ተግባቢ ቀና እና መካሪ በአርዓያነት የሚጠቀሱ አርበኛ ነበሩ። የኢህአዴግን አገዛዝ በታገሉበት ከ1994 እስከ 1998 ዓ/ም በዘለቀው ትግላቸው በሰራዊቱ ደጀን ከባቢዎች ካበረከቱት አስተዋጽዖ ባሻገር በ1998 ዓ/ም በምዕራብ ጎንደር አርማጭሆና መተማ አካባቢዎች በተካሄዱ አውደ ውጊያዎች የተሳተፉ ሲሆን በውጊያው ክፉኛ ቆስለው በኢህአዴግ መር ስርዓት በቃሊቲና ቂሊንጦ እስር ቤቶች ሲማቅቁ ኖረዋል። ለ12 ዓመታት በእስር ከቆዩ በኋላ በ2010 ዓ/ም በምህረት ከእስር ተፈተው ቤተሰቦቻቸውንና ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ለማግኘት በቅተዋል። አርበኛ ወርቁ በለጠ ባደረባቸው ህመም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና በፖሊስ ስራዎች ጠቅላይ ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው በህዳር 24/2015 ዓ/ም ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ገደማ በተወለዱ በ64 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply