
ለ2013/14 የመኸር እርሻ ከ18 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) አርሶ አደር ዘላለም ጌቴ በምስራቅ ጎጃም ዞን ባሶሊበን ወረዳ ልምጭም ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አቶ ዘላለም ጤፍ፣ ስንዴ እና በቆሎ በብዛት ያመርታሉ፡፡ በ2012/13 ለመኸር እርሻ አገልግሎት የሚውለው የአፈር ማዳበሪያ ዘግይቶ በመግባቱ መጉላላት ገጥሟቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ዓመት ችግሩን ለመቀነስ የአፈር ማዳበሪያ እየገዙ እንደሆነም ነግረውናል፡፡ የተሻለ ምርት ለማግኘት ማሳቸውን ደጋግመው እያረሱም ነው፡፡
የእርሻ ማሳቸውን ሰብሉ እንደተነሳ ማረሳቸው አፈሩን ለፀሐይ በማጋለጥ ሰብላቸው ከተባይና ከሽታ እንደሚከላከለው ነው አቶ ዘላለም የተናገሩት፡፡
ሌላኛው ያነጋገረናቸው አርሶ አደር ደምል ተሻለ በባሶ ሊበን ወረዳ የዶገም ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ደምል በመኸር ስንዴ፣ ጤፍ፣ በቆሎ እና መሰል አዝዕርቶችን በብዛት ያመርታሉ፡፡ አርሶ አደር ደምል ለመኸር ምርት የሚጠቀሙበትን የአፈር ማዳበሪያ ቀድሞ የመግዛት ልምድ አላቸው፡፡ በዚህ ዓመትም እስካሁን አራት ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ገዝተው አዘጋጅተዋል፡፡
አቶ ደምል ዘር ከመዝራታቸው በፊት ማሳቸውን ደጋግሞ የማረስ ልምድ አላቸው፤ በዚህም የተሻለ ምርት ማግኘት እንደቻሉ ነግረውናል፡፡ ደጋግሞ በማረስ መሬቱ ለፀሐይ ስለሚጋለጥ አረምንና ተባይን እንደሚከላከል ነግረውናል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዓት ግብይት ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ጥሩሰው ለግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የግብርና ግብዓቶችን በሚፈለገው መጠን ለማቅረብ እየሠሩ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ለ2013/14 የመኸር ምርት ጥቅም ላይ የሚውል የክልሎችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ እንደ ሀገር
• 18 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሟል፡፡
• 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ሀገር ውስጥ ገብቷል፡፡
የከረመ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያን ጨምሮ ከገባው የአፈር ማዳበሪያ 64 በመቶ ያህሉ ከደረቅ ወደብ ወደ ማዕከላዊ መጋዝኖች መጓጓዙን ነግረውናል፡፡ አቶ መንግሥቱ እንዳሉት የአፈር ማዳበሪያ ግዢው ቀድሞ በመጀመሩ ካሁን በፊት ይገጥሙ የነበሩ ችግሮች እንዳይከሰቱና ክልሎች በጠየቁት መጠን ግዥ እንዲፈጸም አስችሎአል፡፡ ይሄም ከሌላው ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ነው ተብሎ መገምገሙን ነግረውናል፡፡
ዳይሬክተሩ የአፈር ማዳበሪያ ግዥው ተፈጽሞ ወደ ሀገር ከመግባቱ በፊት በሀገር ውስጥ መከናወን ያለባቸው ጉዳዮች በእቅድ ተይዘው መሠራታቸው ለአፈጻጸሙ መሻሻል አስተዋጽኦ እንዳላቸው በማብራሪያቸው አንስተዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳሉት የአፈር ማዳበሪያው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው በመርከብ በመሆኑ ድልድሉ በክልሎች ጥያቄ መሰረት መሠራቱን ነግረውናል፡፡
በአማራ ክልል ለ2013/14 መኸር እርሻ
• 7 ሚሊዮን 32 ሺህ 554 ኩንታል ማዳሪያ እንዲቀርብለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡
• የካቲት 16/2013 ዓ.ም 2 ሚሊዮን 963 ሺህ 498 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ደረቅ ወደብ ደርሷል፡፡
• ደረቅ ወደብ ከገባው የአፈር ማዳበሪያ 2 ሚሊዮን 530 ሺህ 559 ኩንታል ማዳበሪያ በክልሉ ባሉ 23 ዩኔኖች ደርሶ ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተሰራጭቷል፡፡
ቀሪውን የአፈር ማዳበሪያ በተያዘው ወር ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
በምርጥ ዘር አቅርቦት ረገድም እንደ ሀገር 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ለማቅረብ እቅድ መያዙን አቶ መንግሥቱ ተናግረዋል፡፡ የዘንድሮው ምርጥ ዘር የሚቀርበው ከሀገር ውስጥ በመሆኑ አርሶ አደሮች ሳይጉላሉ ዘር የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየሠሩ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ቅድመ ምርት ትንበያ በተሠራው መሰረት
• 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርጥ ዘር ይሰበሰባል ተብሎ ታቅዶ ነበር፡፡
• 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርጥ ዘር እስካሁን በግርድፉ ተሰብስቧል፡፡
ዳይሬክተሩ ዘሩን የማጣራት ሥራው በመንግሥትና በሀገር ውስጥ ዘር አቅራቢ ድርጅቶች እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊትር የአንበጣ፣ የተባይ እና በሽታ የሚከላከል የተለያየ ዓይነት ኬሚካል ግዥ ለመፈጸም በሂደት ላይ መሆኑንም ከፌዴራል ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post ለ2013/14 የመኸር እርሻ ከ18 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.
Source: Link to the Post