You are currently viewing ላለፉት ሶስት ሳምንታት በተከታታይነት የቀጠለው በአማራ ባለሀብቶች ላይ ያነጣጠረው ሕገወጡ ዘመቻ ሲፈተሽ የአማራና የአፋር ባለሀብቶች የባንክ አካውንት መታገዱን መዘገባችን ይታወሳል። ይህ አሁ…

ላለፉት ሶስት ሳምንታት በተከታታይነት የቀጠለው በአማራ ባለሀብቶች ላይ ያነጣጠረው ሕገወጡ ዘመቻ ሲፈተሽ የአማራና የአፋር ባለሀብቶች የባንክ አካውንት መታገዱን መዘገባችን ይታወሳል። ይህ አሁ…

ላለፉት ሶስት ሳምንታት በተከታታይነት የቀጠለው በአማራ ባለሀብቶች ላይ ያነጣጠረው ሕገወጡ ዘመቻ ሲፈተሽ የአማራና የአፋር ባለሀብቶች የባንክ አካውንት መታገዱን መዘገባችን ይታወሳል። ይህ አሁንም ተጧጡፎ ቀጥሏል። ባንክ አውንታቸው የታገደው አብዛኛዎቹ የአማራ ባለሀብቶች ሲሆኑ ከሽብር ፈጠራና መንግስትን በኃይል ለማስወገድ የሚንቀሳቀሱትን በመደገፍ ውንጀላ ቀርቦባቸዋል። ይህ ውንጀላ በሚቀርብበት ወቅት መንግስት ከሱዳንና ከግብፅ ወታደራዊ ድጋፍ አግኝቶ፣ ሌሎች አገራት በፕሮፖጋንዳና በጫና አግዘውት የኢትዮጵያን መንግስት አስወግዳለሁ ብሎ ሲሰራ ከቆየው ህወሓት ጋር እየተቃቀፈ ነው። መንግስት ባለሀብቶችን በሽብር ፈጠራና መንግስትን በኃይል በማስወገድ ሰበብ ክስ የሚያቀርብባቸው የሰሜን ዕዝን የመታ፣ የመንግስት ተቋማትን ያወደመ፣ ከተሞችን በሮኬት የደበደበው ህ…ወሓት ጋር ጫጉላ ይዞ ነው። መንግስት የአፋርና የአማራን ባለሀብቶች በወንጀል ጠርጥሬያለሁ የሚለው ጦርነቱን በገንዘብ የደገፉትን የአማራና የአፋር ባለሀብቶች ሽብር ፈጣሪ እያለ፣ ሽብር የፈጠረውን ህወሓትን ቤተ መንግስት እየጋበዘ ነው። መንግስት የአማራና የአፋር ባለሀብቶች ላይ ወንጀል እያቀረበ ያለው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ኃላፊዎችን፣ የቤንሻንጉልና ኦሮሚያ ባሀስልጣናትን የገደለው ኦነግ ሸኔ ጋር እየተነጋገረ ነው። የብልፅግና መንግስት ባለሀብቶችን በሽብር ልክሰሳቸው እያለ ያለው የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ሲያቃጥል ከከረመው ኦነግ ሸኔ ጋር እየተወያየ ነው። የፌደራል መንግስቱ ከክልል መንግስታት ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 50 የተቀመጡ መሰረታዊ መርሆዎችን በግልፅ በጣሰ ሁኔታ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስተዳደራዊ ክልል የስልጣን ወሰን ውስጥ ሆነው መታየት ባለባቸው ጉዳዮች ውስጥ በማን አለብኝነት ስልጣን በሌላቸው የፌደራሉ አካላት በመጠቀም ጣልቃ በመግባት ተከታይነት ያለው ሕገወጥ ተግባር እየፈጸመ ያለ መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ ለዚሕም አንድ ማሳያ እንመልከት፡፡ የፌደራሉ መንግስት ወደ አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመከላከያ ሀይሉን ያሰማራው ፋኖን ትጥቅ ለማስፈታት መሆኑን በተደጋጋሚ ገልፅዋል፡፡ እዚሕ ላይ መነሳት ያለበት ዋናው ጉዳይ ፋኖን ትጥቅ ማስፈታት የግድ አስፈላጊ ነው ከተባለ ትጥቁን ለማስፈታት በሕግ ስልጣን ያለው ማነው የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ፋኖ በታሪኩ የአማራ ሕዝብ የነጻነት እና የክብር መገለጫ የሆነ ሀይል ነው፡፡ ምንም እንኳን ጦር መሳርያ በተለየ የሕግ ስርአት የሚተዳደር ንብረት ቢሆንም ፋኖ መሳርያ ታጠቀ የተባለው በግለሰብ ደረጃ የራሳቸውን ሀብት አውጥተው ገንዘባቸውን ከፍለው በገዙት እና ከሕወሀት ጋር በነበረው ጦርነት በማረኩት የጦር መሳርያ ነው፡፡ የክልሉ መንግስት የሕወሀት ታጣቂዎች በክልሉ ላይ አውጀውት የነበረውን ጦርነት ለመመከት ፋኖ እንዲሰማራ ሲያደርግ በግል ገንዘባቸው ጦር መሳርያ ከነተተኳሹ ገዝተው እና/ወይም በጦርነቱ የማረኩትን ጦር መሳርያ የግላቸው ሀብት አድርገው እንዲወስዱ እና የሕወሀት ኃይልን እንዲመክቱ በግልፅ በአዋጅ ሲገልጽ የፌደራሉ መንግስት ምንም ያሰማው ተቃውሞም አልነበረም፡፡ በመሆኑም የፋኖ ሀይል በግል ገንዘባቸው በመግዛት እና/ወይም ከሕወሀት ጋር በነበረው ጦርነት ማርከው የታጠቁት የጦር መሳርያ በክልሉም ሆነ በፌደራሉ መንግስት ፈቃድ እና እውቅና የግል ሀብታቸው ተደርጓል፡፡ ስለሆነም የታጠቁት መሳርያ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 40 መሰረት የንብረት ባለቤትነት ጥበቃ የሚደረግለት በሕግ እውቅና ያለው የግል ሀብታቸው ነው ማለት ነው፡፡ ይህን ሀብታቸውን በሀይል መቀማት አይቻልም፡፡ የፋኖ ሀይል በማናቸውም ምክንያት ትጥቁን መፍታት ካለበት ስለትጥቁ መፍታት ወይም አለመፍታት ለመወሰን ብቸኛ ስልጣን ያለው መጀመርያም ትጥቁን እንዲታጠቁ ፈቃዱን በአዋጅ የሰጣቸው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ብቻ ነው፡፡ ትጥቁን እንዲታጠቁ በፈቀደበት ሕግ ስርአት መሰረት ትጥቁን የማስፈታትም ስልጣን የክልሉ መንግስት ብቸኛ ስልጣን ነው፡፡ የክልሉ መንግስት ፋኖን ትጥቅ ማስፈታት የግድ አስፈላጊ መሆኑን ካመነበት ትጥቅ መፍታቱ የግል ሀብታቸው የሆነውን የጦር መሳርያ ለመንግስት የማስረከብ ውጤት ያለው በመሆኑ በቅድምያ ትጥቁ መፈታት ያለበት ስለመሆኑ፤ ሲፈታም በምን ሁኔታ እና ስርአት እንደሚፈታ እንዲሁም ትጥቃቸውን በመፍታት መሳርያቸውን ለመንግስት የሚያስረክቡት ግለሰቦች ካሳ እንዴት እና በምን መጠን እንደሚከፈላቸው የሚደነግግ ሕግ በቅድምያ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሕግ ከመውጣቱ በፊት ትጥቅን ማስፈታት አይቻልም፡፡ ከተሞከረም ድርጊቱ የዜጎችን ሕገመንግስታዊ መብጥ የሚጥስ ህገወጥ ተግባር ይሆናል፡፡ በመሆኑም ፋኖን ትጥቅ በማስፈታት ሒደት ውስጥ የፌደራል መንግስቱ ምንም አይነት ስልጣን የለውም፡፡ ስለሆነም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስልጣንን በማለፍ በማናቸውም መልኩ ፋኖን ትጥቅ ስለማስፈታት በፌደራል መንግስቱ የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ በሕንግስቱ አንቀጽ 50 የተቀመጡትን የመንግስት አወቃቀር ስርአት መርሕን የጣሱ ተግባራት ናቸው፡፡ ከዚህ የሚከፋው ደግሞ ትጥቅ ማስፈታት በሚለው ሕገወጥ ተግባር ውስጥ የመከላከያ ሀይሉ መሳተፍ ነው፡፡ የፌደራል የመከላከያ ሀይል በአንድ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ሀይሉን ሊያሰማራ የሚችለው በጣም ውስን በሆኑ ጉዳዮች ብቻ ነው፡፡ የመከላከያ ሰራዊት በሕመንግስቱ አንቀጽ 87 መሰረት የሀገሪቱን ሉአላዊነት ከማስጠበቅ በተጨማሪ በውስጥ ጉዳዮች ላይ ሊሳተፍ የሚችለው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ በሚሰጡት ተግባራት ብቻ ነው፡፡ የመከላከያ ሰራዊቱ ከዚሕ ውጭ በክልሎች ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ሊገባ አይችልም፡፡ የመከላከያ ሀይል በተቋም ደረጃ አሁን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስተዳደራዊ ክልል ውስጥ ገብቶ ፋኖን ትጥቅ ማስፈታት በሚል እያከናወነ ያለው ተግባር ሙሉ በሙሉ ሕገመንግስታዊ ስርአቱን ያልተከተለ እና በሕግ ባልተሰጠው ስልጣን እየተከናወነ ያለ ሕገወጥ ተግባር ነው፡፡ ይህንንም ኤታማጆር ሹሙ በፊት ለፊት ቆመው እያስፈጸሙ ያሉበት መንገድ ተቋሙን ሕግን ባልተከተለ ሁኔታ ለመምራት ያላቸውን አቋም የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ይህን የኤታማጆር ሹሙን ውሳኔ ለማስፈጸም በክልሉ ውስጥ ወታደሮቻቸውን በማሰማራት ትጥቅ ማስፈታት በተባለው ሕገወጥ ተግባር ውስጥ የተሰማሩት ከፍተኛ የመከላከያ ሀይል አመራሮች ተግባርም ተቋሙ ፍጹም ሕገወጥ በሆነ አምባገነናዊ ስርአት እንዲሰማራ ያላቸውን ፈቃደኛነት እና ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው፡፡ የፌደራል መንግስቱ እና የመከላከያ ሀይሉ ሕገመንግስታዊ መርሕን ጥሰው በክልሉ ላይ እንዲሕ አይነት ሕገወጥ ተግባር ሲፈጽሙ የክልሉ መንግስት አመራሮችም ለሕገወጥ ተግባሩ ተባባሪ ሆነው የመገኘታቸው ሁኔታ ሀገሪቱ ፍፁም ወደ ሆነ አምባገነናዊ አሀዳዊ የመንግስት ስርአት ለመግባቷ በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡ ይህን ያነሳነው አሁን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስተዳደራዊ ክልል ተወላጅ በሆኑ ምሁራን፤ ጋዜጠኞች እና የተመረጡ ባለሀብቶች ላይ የተጀመረው ሕገወጥ የእስር እና የማዋከብ ተግባር የፌደራል መንግስቱ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ላይ በመፈጸም ላይ ያለው ሕገመንግስታዊ መርሕን የጣሰ ሕገወጥ ተግባር ቅጥያ በመሆኑ ነው፡፡ የፌደራል መንግስቱ በነዚሕ በተመረጡ ምሁራን፤ ጋዜጠኞች እና ባለሀበቶች ላይ የጀመረው ሕገወጥ ዘመቻ ያሉበትን ግልጽ የሆኑ የሕግ ጥሰቶች በዝርዝር ማየት ይቻላል፡፡ ለዛሬው በፌደራል መንግስቱ እየተከናወነ ባለው የተወሰኑ ባለሀብቶች ላይ ያነጣጠረ ሕገወጥ ዘመቻ ተሳታፊ የሆኑት አካላት የፋይናንስ ደሕንንት አገልግሎት፤ የኦሮሚያ ፖሊስ፤ የኦሮሚያ ፍርድ ቤት፤ የፌደራል ፖሊስ እና የፌደራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ፤ የገቢዎች ሚኒስትር እና የጉምሩክ ኮሚሽንን ያካተተውን ተግባር እንደሚከተለው እናያለን፡፡ እዚሕ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ዋናው ነጥብ የፌደራል መንግስቱ ለሕገወጥ ተግባሩ ሁሉንም የፍትሕ አካላት እና በዜጎች ላይ የወንጀል ክስ ለማቅረብ የሚያስችል ስልጣን ያላቸውን የተመረጡ አስፈጻሚ አካላት በአንድ ላይ አቀናጅቶ ማሰማራቱ ምን ያሕል አደገኛ ተግባር መሆኑን እና እንዲሕ አይነቱ ተግባርም ሀገሪቱ ወደ አምባገነናዊ የመንግስት ስርአት ስለመግባቷ ጉልህ ማሳያ ምልክት መሆኑን ነው፡፡ በነዚሕ ተቋማት እየተፈጸመ ያለውን የሕግ ጥሰት አንድ በአንድ እንመልከት፡፡ 1. የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት የፋይናንስ ደሕንነት አገልግሎት በነዚሕ በተመረጡ የክልሉ ተወላጅ በሆኑ ባለሀብቶች ላይ በተቀናጀ ሁኔታ እየፈጸመ ያለውን ሕገወጥ ተግባር በባለቤትነት እያከናወነ ይገኛል፡፡ በአቶ አብዱልሀሚድ መሀመድ እየተፈረመ ከፋይናንስ ደሕንነት አገልግሎት ለባንኮች የሚወጡ የእገዳ ደብዳቤዎችን ስንመለከት በተቋሙ የሚፈፅሙት የሕግ ጥሰት ገደብ ያለው አይደለም፡፡ በደብዳቤዎቻቸው የግለሰቦችን እና የንግድ ድርጅቶችን የባንክ ሒሳብ ማገዳቸውን እና ተቋማቸው ሳያውቅ እግዳቸው እንዳይነሳ በግልጽ ትእዛዝ ይሰጣሉ፡፡ ለዚህ ትእዛዛቸው መሰረት የሚያደርጉት በወንጀል የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ስለመከላከል እና መቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 19/3ን ነው፡፡ በዚህ በጠቀሱት ሕግ መሰረት የፋይናንስ ደሕንነት አገልግሎት ያለው ስልጣን የፋይናንስ ወይም የፋይናንስ ነክ የሆኑ ተቋማት በወንጀል የተገኘ ፍሬ ስለመሆኑ ወይም ሽብርተኝነትን ከመርዳት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ በበቂ ምክንያት የጠረጠሩትን ግብይት ለተቋሙ ሪፖርት ሲያደርጉ ይህን ጥርጣሬ ያለበትን ግብይት ስለመሆኑ ሪፖርት የቀረበበትን ግብይት ከሶስት ቀን ላልበለጠ ጊዜ ማገድ ብቻ ነው፡፡ ከዚሕ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ከፋይናንስ ወይም ከፋይናንስ ነክ ተቋማት አጠራጣሪ ግብይትን አስመልክቶ ሪፖርት ሳይቀርብለት በራሱ አነሳሽነት የአንድንም ግለሰብ ግብይት ለማገድ ስልጣን የሌለው መሆኑን ነው፡፡ ከዚሕ አንጻር ሲታይ አቶ አብዱልሀሚድ መሀመድ በደብዳቤያቸው ላይ በግልጽ አረጋግጠው እንደሚገልጹት በተለይ በፌደራል መንግስቱ ትኩረት በተደረገባቸው የአማራ ተወላጅ ባለሀብቶችን በተመለከተ ከአንድም የፋይናንስ ወይም የፋይናንስ ነክ ተቋም አጠራጣሪ ግብይትን በተመለከተ ምንም አይነት ሪፖርት ሳይቀርባላቸው በተቋማቸው አነሳሽነት የእግዱን ትእዛዝ መስጠታቸው ግልጽ የሆነ ሕገወጥ ተግባር ነው፡፡ የፋይናንስ ደሕንነት አገልግሎት በተቋም ደረጃ በተከታታይ እየፈጸሙት ባለው ተግባር ሕግን የሚጥሱበት መጠን ከዚሕም የከፋ ነው፡፡ የፋይናንስ ደሕንነት አገልግሎት በሕግ የተሰጠው ስልጣን ከፋይናንስ ወይም ከፋይናንስ ነክ ተቋማት በቀረበለት ሪፖርት ላይ በመመስረት አጠራጣሪ የሆነውን ሪፖርት የቀረበበትን ግብይት ብቻ ለሶስት ቀን ማገድ ቢሆንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አብዱልሐሚድ ግን በሕግ ባልተሰጣቸው ስልጣን ጠቅላላ የግለሰቦችን የባንክ ሒሳብ ላልተወሰነ ጊዜ ማገዳቸውን በደብዳቤያቸው ላይ በግልጽ አስቀምጠው ትእዛዙን ለሁሉም ባንኮች አስተላልፈዋል፡፡ ይህን አይነት በግልጽ ሕግን የጣሰ ተግባር በሀገራችን የሕግ ስርአት በአዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 መሰረት በሙስና ወንጀል የሚያስጠይቅ ተግባር ነው፡፡ ደብዳቤውን ፈርመው ያወጡት የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተርን በሙስና ወንጀል በፍርድ ቤት ለማስቀጣት ለባንኮቹ የፃፏቸውን ደብዳቤዎች ማቅረብ ብቻውን በቂ ነው፡፡ እዚሕ ላይ ትኩረት ሰጥተን ማየት ያለብን የፋይናንስ ደሕንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ግልጽ የሆነ ሕግን የጣሰ በሙስና ወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል በተመረጡ የአማራ ተወላጅ ባለሀብቶች ላይ ያነጣጠረ የእስር እና የማዋከብ ሕገወጥ ተግባር ያለምንም መሳቀቅ ለመፈጸም መነሻቸው ድርጊታቸው በፌደራል መንግስቱ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ላይ የመከላከያ ሰራዊትን በመጠቀም በተጀመረው የመዋቅራዊ ጥቃት ዘመቻ ማእቀፍ ውስጥ ሆኖ የሚከናወን መሆኑን በሚገባ የሚያውቁ በመሆኑ እና ሕገወጥ ተግባራቸውንም ያለምንም መሳቀቅ እንዲያስፈጽሙ ከፌደራል መንግስቱ አመራሮች በተሳጣቸው ድጋፍ እና ሽፋን በመተማመን በፈጠሩት ድፍረት መሆኑን ነው፡፡ 2. ኦሮሚያ ፖሊስ እና ፍርድ ቤት በፌደራል መንግስቱ ልዩ ትኩረት ተደርጎባቸው ምርመራ እየተደረገባቸው ባሉ ባለሀብቶች ላይ የቀረበው አንዱ ውንጀላ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የጨው ምርት በመጋዘን አከማችተው ተገኝተዋል የሚል ነው፡፡እዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ዋናው ነጥብ ይሕ ውንጀላ ከመጀመሩ በፊትም ሆነ አሁን ባለው ሁኔታ በሀገር ደረጃ የተፈጠረ የጨው እጥረትም ሆነ የዋጋ ንረት አለመኖሩ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በሀገራችን የሕግ ስርአት ምንም አይነት በወንጀል የሚያስጠይቅ ጉዳይ የለም ማለት ነው፡፡ ስለሆነም በፖሊስ ምርመራ ማድረግም ሆነ ባለሀብቶቹን ማዋከብ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ይህንን ያፈጠጠ የሕግ ጉዳይ በማለፍ አንዱ መጋዘን በክልሌ ይገኛል በሚል ምክንያት የመጋዘኑን ሰራተኞች እና አከራይ በማሰር የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሸገር ከተማ ፖሊስ ምርመራ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ለክሱ ምክንያት የሆነው መጋዘን በአዲስ አበባ ክልል ውስጥ የሚገኝ የነበረ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መካከል በተደረገ ድንበር የማካለል ስምምነት ወደ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንዲካተት በመደረጉ በአሁኑ ወቅት በሸገር ከተማ አስተዳደር ስር ይገኛል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በሙሉ የፌደራል መንግስት ተመዝጋቢ የሆኑ የንግድ ድርጅቶች ናቸው፡፡ እንዲሁም የጨው ምርቱ ከተመረተበት ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ተጓጉዞ በፌደራል መንግስት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ የምግብ፤ የመድሀኒት እና ጤና ክብካቤ አስተዳደር፤ እና ቁጥጥር ባለስልጣን፤ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ መስርያ ቤቶች በተሰጠ ፈቃድ የተከማቸ ነው፡፡ ከዚሕ በቀላሉ መረዳት እንደሚቻለው ጉዳዩ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን፤ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን እንዲሁም የፌደራል መንግስትን የሚመለከት ነው፡፡ በዚሕ ምክንያት ተከማችቶ ተገኘ ከተባለው የጨው ምርት ጋር በተያያዘ የሚነሳ ማናቸውም አይነት የምርመራ ምክንያት ካለ ምርመራውን ለማከናወን በአዋጅ ቁጥር 720/2004 መሰረት በሕግ ስልጣን ያለው የፌደራል ፖሊስ ብቻ ነው፡፡ የሸገር ከተማም ሆነ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፖሊስ በዚሕ ጉዳይ ላይ ምርመራ ለማጣራት ምንም ስልጣን የላቸውም፡፡ ይህን ግልጽ የሆነ ሕግ በመጣስ በሸገር ከተማ ፖሊስ የተጀመረው ምርመራ ሕገወጥ ነው፡፡ ይህ የሸገር ከተማ ፖሊስ በሌለው ስልጣን የጀመረውን ምርመራ መነሻ በማድረግ ተጠርጣሪዎቹ በጊዜ ቀጠሮ አቤቱታ የቀረቡለት የሸገር ከተማ ፍርድ ቤትም ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለኝም ብሎ መዝገቡን ሊዘጋ ሲገባው በድፍረት ተጠርጣሪዎችን በእስር እንዲቆዩ በመፍቀድ ጉዳዩን ማየቱ በዳኞች የዲስፕሊን ደንብ መሰረት በዲስፕሊን ተጠያቂነትን የሚያስከትል ሕገወጥ ተግባር ነው፡፡ የሸገር ከተማ ፖሊስ እና ፍርድ ቤት በግልጽ በህግ ምክንያት በሌላቸው ስልጣን ተጠረርጣሪዎችን በእስር አድርገው ጉዳዩን ማየታቸው በፌደራል መንግስት ለተጀመረው ሕገወጥ ዘመቻ ድጋፍ ለማድረግ የተከናወነ ነው ከሚባል በስተቀር ሌላ ትርጉም ሊኖረው አይችልም፡፡ 3. የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የፌደራል መንግስት በተለይ ትኩረት አድርጎ ዘመቻ በጀመረባቸው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ተወላጅ የሆኑ ባለሀብቶች ላይ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የጨው ምርት አከማችታችሁ ተገኝታችኋል በሚል ምክንያት የተጀመረውን ምርመራ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሕግን ባልተከተለ ሁኔታ ቅርንጫፉን በማስፋት ተጠርጣሪዎቹ በሙስና፤ ግብር እና ታክስ በመሰወር፤ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ በመጠቀም እና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር በመፈፀም ወንጀል ምርመራ እየተደረገባቸው ነው የሚል የተቀነባበረ የክስ ምክንያት በማቅረብ የተጠርጣሪዎችን የባንክ ሒሳብ እንዲሁም የማይንቀሳቀስ እና የሚንቀሳቀስ ንብረቶችን በሙሉ እንዲታገድለት አቤቱታ በማቅረብ እስከ አሁን የ65 ግለሰቦች እና የንግድ ድርጅቶች የባንክ ሒሳብ እና በስማቸው ተመዝግቦ የሚገኝ ማናቸውም የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት በሙሉ ያለምንም ገደብ በፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዲታገድ አድርጓል፡፡ እነዚሕ ንብረታቸው የታገዱ ልዩ ትኩረት የተደረገባቸው የአማራ ሕዝብ ተወላጅ የሆኑ ባለሀብቶችም ከሀገር እንዳይወጡ በፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የእገዳ ትእዛዝ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ የፌደራል ፖሊስ የተጠርጣሪዎቹን ንብረት እንዲታገድለት ለፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቤቱታ ሲያቀርብ ሶስት መሰረታዊ የሕግ ጥሰቶችን ፈጽሟል፡፡ አንደኛ ፖሊስ አቤቱታውን የሙስና ጉዳዮች ላይ በሚደረግ ምርመራ ጋር በተያያዘ የሚሰጡ ማናቸውንም ትእዛዞች ለማየት ስልጣን ላለው የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡ ሁለተኛ የእግድ ትእዛዝ እንዲሰጥለት አቤቱታ ሲያቀርብ እንዲታገድለት የሚጠይቀውን የሀብት መጠን ገልጾ እንዲያቀርብ በሕግ ግዴታ ያለበት ቢሆንም ሆን ብሎ ይህን ግዴታውን ወደ ጎን በመተው በደፈናው ሁሉም ንብረት እንዲታገድለት አቤቱታ አቅርቧል፡፡ የንግድ ድርጅቶች የባንክ ሒሳብ እንዲታገድ ሲደረግ የንግድ ድርጅቱ ሙሉ በመጀሉ የፋይናንስ እንቅስቃሴው ስለሚታገድ ድርጅቱ የሰራተኞችን ደመወዝ፤ ግብር፤ ታክስ፤ መክፈል የማይችል እንዲሁም ከውጭ ለሚያስገባቸውም ሆነ ለሚልካቸው እቃዎች የውል ግዴታውን መወጣት የማይችል፤ የባንክ እዳውን መክፈል የማይችል በመሆኑ በዚህ መልክ እግድ እንዳይሰጥ ሕግ ይከለክላል፡፡ ይህ ሕግ መርሕ እየታወቀ ፖሊስ ይህን ተደራራቢ ጉዳት በአንድ ጊዜ በማድረስ የንግድ ድርጅቶቹን ለመግደል የታሰበ በሚያስመስል መልኩ ሕግን ያልተከተለ አቤቱታ አቅርቧል፡፡ የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቱም መጀመርያ አቤቱታው ሲቀርብለት መመርመር ያለበት ጉዳዩን ለማየት ስልጣን ያለው መሆን ያለመሆኑን ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ በፖሊስ አቤቱታ ላይ በግልጽ የተጀመረው ምርመራ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ስለመሆኑ ተገልጾለት እያለ እና በሕግ ይህን መሰል ጉዳዮች ለማየት ስልጣን ያለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሆኑ እየታወቀ በፌደራል መንግስቱ በእነዚሕ የአማራ ተወላጆች ላይ ለተጀመረው ሕገወጥ ዘመቻ ያለውን ድጋፍ ለማሳየት ብቻ በሌለው ስልጣን ጉዳዩን ተቀብሎ እና አይቶ የተጠርጣሪዎቹ የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በሙሉ እንዲታገዱ ሕገወጥ የሆነ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ በፍርድ ቤቱ በተሰጠው የእግድ ትእዛዝ የተፈጸመው በጣም የከፋው ጥፋት በሌለው ስልጣን የእግድ ትእዛዙን በመስጠቱ ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ከዚህ የከፋው ጥፋት ፍርድ ቤቱ ቁጥራቸው 65 በሆኑ ግለሰቦች እና የንግድ ድርጅቶች ላይ እግድ ሲሰጥ የእግድ ትእዛዝ የተሰጠባቸው ሰዎች በሕይወት የሌሉ ሰዎች፤ የሟቾቹ ወራሾች፤ እድሜያቸው 18 አመት ያልሞላ ልጆች፤ የዋና ተጠርጣሪዎች ጥዳር አጋሮች፤ የንግድ ድርጅቶች ባለአክስዮን አባላት እና የመሳሰሉት መሆናቸውን አላጣራም፡፡ ይህን ማጣራት አስፈላጊ የሚሆነው በወንጀል ጉዳይ ተጠያቂነት የሚኖረው እያንዳንዱ ግለሰብ በሚኖረው ተሳትፎ መጠን እንጂ የተጠርጣሪ የንግድ ድርጅት ባለአክስዮን አባል በመሆን፤ የተጠርጣሪ ሰው የትዳር አጋር፤ ልጅ፤ ወራሽ በመሆን ስላልሆነ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ከስማቸው በቀላሉ መረዳት በሚያስችል ሁኔተ የቤተሰብ አባላትን ያካተተ በድምሩ 65 ሰው በሙስና ወንጀል ተጠርጣሪ ተብሎ ሲቀርብለት የአቤቱታውን አቀራረብ አግባብነት መመርመር ይጠበቅበት ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ለሰጠው የእግድ ትእዛዝ መሰረት ያደረገው የተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የስነስርአት እና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 9 መሰረት ንብረት የሚታገደው በወንጀሉ ተገኘ ከተባለው የማይገባ ጥቅም ወይም ደረሰ ተብሎ ከሚገመተው ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ንብረት ብቻ ስለመሆኑ በግልጽ ተደንግጎ ሳለ ይህን ግልጽ የሆነ የሕግ ድንጋጌ ደፋር በሆነ መንገድ በመጣስ ከሕጉ አላማ እና መንፈስ ውጭ በመውጣት የተጠርጣሪዎችን ሀብት እና ንብረት በሙሉ ያለምንም ገደብ እንዲታገድ ትእዛዝ መስጠቱ ነው፡፡ ዳኛው ጉዳዩን ለማየት እና ትእዛዝ ለመስጠት ስልጣን የሌላቸው ስለመሆኑ እና የእግድ ትእዛዝ የሚሰጠው መጠኑ ተለይቶ በተገለጸ ንብረት ላይ ብቻ ስለመሆኑ በግልጽ የተቀመጠ የሕግ ድንጋጌዎችን በመጣስ ይህን ሕገወጥ የሆነ ተደራራቢ የሕግ ጥሰቶች የተፈጸመበትን ጠያቂ ቢኖር በዲስፕሊን እና ከዚያም ሲያልፍ በሙስና ወንጀል ሊያስጠይቅ የሚችል ትእዛዝ ያለምንም ፍርሀት ተጠያቂነት በማናቸውም መንገድ እንደማይመጣባቸው እርግጠኛ በመሆን በድፍረት የሰጡት ምንም በመተማመን ነው የሚለውን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ለዚሕ ሕገወጥ የሆነ የእግድ ትእዛዝ መሰጠት ድፍረት ምክንያቱ ትእዛዙ በፌደራል መንግስቱ ከፍተኛ አመራሮች ሕመንግስታዊ ስርአትን በመጣስ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፤ በክልሉ ተወላጅ ምሁራን፤ ጋዜጠኞች እና በክልሉ ተወላጅ ባለሀብቶች ላይ መዋቅራዊ ጥቃት በመፈጸም ክልሉን ለማዳከም እና ለማንበርከክ የተጀመረው ሕገወጥ ዘመቻ አካል መሆኑን በመረዳት ተጠያቂነት እንደማይመጣባቸው በመተማመን የሰሩት ስለመሆኑ መረዳት ከባድ አይደለም፡፡ የገቢዎች ሚኒስትር እና የጉምሩክ ኮሚሽንም ኦዲት እናደርጋለን በሚል ሰበብ በነዚህ በተመረጡ የአማራ ተወላጅ ባለሀብቶች ላይ የተጀመረው የእስር እና የማዋከብ ዘመቻ አካል ሆነዋል፡፡ ይህም የፌደራል መንግስቱ በመንግስቱ መዋቅር ውስጥ ያሉ ሁሉንም አካላት በማሳተፍ የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ምሁራንን፤ ጋዜጠኞችን እና ባለሀብቶችን በማሰር እና በማዋከብ የክልሉ አስተዳደርን ተንበርካኪ ለማድረግ በቁርጥ መነሳቱን ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ የፌደራል መንግስቱ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ላይ ሕገመንግስታዊ መርሆዎችን በመጣስ በሕግ ስልጣን የሌላቸውን የመከላከያ፤ የደሕንነት እና የፍትሕ ተቋማትን እንዲሁም የገቢዎች ሚኒስትር እና የጉምሩክ ኮሚሽንን በመጠቀም የክልሉን መንግስታዊ አመራሮች በማንበርከክ እና የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ምሁራን፤ ጋዜጠኞች እና ባለሀብቶችን በማሳደድ የጀመረው ሕገወጥ ተግባር አላማው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ተወላጆችን በማዳከም ከፖለቲካው ተጽእኖ ፈጣሪነት በማስወገድ እና በማራቅ ፖለቲካውን በተረኛ ቡድን ስር ለመጠቅለል እንዲሁም የክልሉን ተወላጅ ባለሀብቶች በማሳደድ ከንግድ ስራቸው እንዲወጡ በማድረግ የንግድ ስራቸው በተረኛ የፖለቲካ ስርአቱ ታዛዥ ባለሀብቶች እንዲያዙ እና እንዲተኩ በማድረግ በአማራ ሕዝብ ላይ መዋቅራዊ ጥቃት መፈጸም መሆኑም መላው የአማራ ሕዝብ በሚገባ ተረድቶታል፡፡ ይህን በአማራ ሕዝብ ላይ መዋቅራዊ ጥቃት የሚፈጸምበት ሕገወጥ የሆነ ዘመቻ እንዲቆም እና የአማራ ሕዝብ መብቱ እና ክብሩ ተጠብቆ የሚኖርበት ስርአት እንዲመሰረት ለማድረግ በመላው የኢትዮጵያ ግዘት ውስጥ እንዲሁም በውጭው አለም የሚገኙ አገር ወዳድ ህዝብ በደል እየተፈጸመበት ካለው አማራ ሕዝብ ጎን በመቆም ትግሉን ሊቀላለቀል ይገባል፡፡ ይህ የመንግስት መዋቅርን በመጠቀም ሕገወጥ የሆነ ተግባር በመፈጸም ሀገርን የማፍረስ ዘመቻ የጀመረው ቡድን በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ትግል ከሕገወጥ ተግባሩ እንዲታቀብ ካልተደረገ ዛሬ በአማራ ሕዝብ ላይ የተጀመረው ዘመቻ ነገ በሌላው ሕዝብ ላይ የማይፈጸም ስለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ ስለሆነም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት አመራር መዋቅር ላይ በአንድ በኩል እና በአማራ ሕዝብ ተወላጆች በሆኑ ምሁራን፤ ጋዜጠኞች እና ባለሀብቶች ላይ በሌላ በኩል በፌደራል መንግስቱ የተጀመረው የእስር እና የማዋከብ ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲቆም ሊደረግ ይገባል፡፡ ©ዘሀበሻ

Source: Link to the Post

Leave a Reply