“ላለፉት 30 ዓመታት ሕገ መንግሥቱ እውቅና የነፈገው ሕዝብ” የጠለምት አማራ ህዝብ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ… ጥር 15 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በኢፌ…

“ላለፉት 30 ዓመታት ሕገ መንግሥቱ እውቅና የነፈገው ሕዝብ” የጠለምት አማራ ህዝብ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ… ጥር 15 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ እንደተቀመጠው ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ በቋንቋው የመናገር፣ የመጻፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግ፣ ባሕሉን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት እንዳለው አስቀምጧል። በንዑስ አንቀጽ 3 ላይ ደግሞ ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት እንዳለው ተገልጿል። ይህ መብት ብሔሩ፣ ብሔረሰቡ፣ ሕዝቡ በሰፈረበት መልክዓ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋማት የማቋቋም እንዲሁም በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን እንደሚያጠቃልል ተቀምጧል፡፡ እነዚህ መብቶች በሕገ መንግሥቱ ላይ ይቀመጡ እንጅ ህወሓት በጠለምት ህዝብ ላይ ሕገ መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት በኃይል በመቆጣጠር ግፍና በደል ሲያደርስ እንደነበር የወረዳው ነዋሪዎች ነግረውናል። ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል ሰለሞን አታላይ እንደነገሩን የጠለምት ሕዝብ ከ1983 ዓ.ም በፊት በበጌምድር ክፍለ ሀገር ሥር ሲተዳደር ነበር። ይሁን እንጅ ህወሓት በትረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ ከነበረው የተስፋፊነት ፍላጎት የተነሳ የጠለምትን ለም ቦታ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ከመጽደቁ በፊት በኃይል እና በጉልበት ወደ ትግራይ ክልል እንዲካለል ማድረጉን ነግረውናል። በጉልበት ወደ ትግራይ ክልል ከተካለለ በኋላም የአካባቢው ነዋሪዎች ባህላቸውን እንዳያሳድጉ፣ በአካባቢው የመንግሥት ተቋማት ተቀጥረው እንዳይሠሩ፣ በአማርኛ ቋንቋ እንዳይናገሩና ሌሎችንም በደሎች ፈጽሟል። አካባቢው በኀይል ወደ ትግራይ ከተካለለበት ጊዜ ጀምሮ የጠለምት የአማራ ሕዝብ በጉልበት የተነጠቀውን ማንነት ለማስመለስ ትግል ሲያደርግ መቆየቱን ነግረውናል። በዚህም የአማራ ተወላጆች ታስረዋል፤ መከራና ስቃይ ደርሶባቸዋል፤ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ሌሎች ደግሞ የገቡበትን አድራሻ ማወቅ አለመቻሉን ነው ያስረዱን። የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ በከፈሉት መሥዋዕትነትም ሲደርስባቸው ከነበረው የህወሃት ጭቆና በመላቀቃቸው መደሰታቸውን ገልጸውልናል። ከዚህ በኋላ ማንነትን ለመደፍጠጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደማይኖረውም አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡ ወጣት ሀረገወይን ደሳለኝ ህወሓት በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ መወገድ “በትዕግስት የተገኘ ድል” ነው ብላዋለች። ወጣቷ እንደነገረችን በአካባቢው ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀን እና ማንነትን መጠየቅ መሥዋዕትነትን አስከፍሏል። ወደ ዋልድባ ገዳም በነጻነት ተንቀሳቅሶ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ማካሄድ የማይቻልበት ጊዜ እንደነበር ነግራናለች። ህወሃት በማይካድራ ብቻ ሳይሆን ባለፉት 30 ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ የጠለምት ነዋሪዎችን ማንነትን መሠረት ባደረገ መልኩ በስውርና በይፋ መግደሉንም ገልፃልናለች። የህወሃት ቡድን የፈጸመው ግፍና በደል ጭቁኑን የትግራይ ህዝብ እንደማይወክል የገለጸችው አስተያየት ሰጭዋ በቀጣይም የሁለቱ ህዝቦች አብሮነት እንደበፊቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግራለች። አቶ ሀብታሙ ይርጋ በበኩላቸው ህወሓት ወደ አካባቢው ከገባ ጀምሮ በጠለምት ህዝብ ላይ እሥራት፣ ግርፋት፣ ማፈናቀል እና ማሳደድ ዋነኛ ተግባሩ እንደነበር ነው የነገሩን። ህዝቡ በኢኮኖሚ ጎልቶ እንዳይወጣ ደባ ይሰራበት እንደነበርም አቶ ሀብታሙ አስረድተዋል። ከዚህ በፊት የተፈጸሙት በደሎች እንዳይደገሙ በቋንቋቸው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ባህላቸውን የመግለጽ፣ የማዳበር እንዲሁም ታሪካቸውን የመንከባከብ መብታቸው ሊከበር እንደሚገባም አቶ ሀብታሙ ጠይቀዋል። አብመድ እንደዘገበው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply