“ልጇ ክብር በማግኘቱ ቤተ ክርስቲያን ደስ ብሏታል”፡ ብፁዕ አቡነ አብርሃም መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም (አሻራ ሚዲያ) ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የክብር ዶክትሬታቸውን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲ…

“ልጇ ክብር በማግኘቱ ቤተ ክርስቲያን ደስ ብሏታል”፡ ብፁዕ አቡነ አብርሃም መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም (አሻራ ሚዲያ) ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የክብር ዶክትሬታቸውን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም ተቀበሉ። ብፁዕነታቸው ለሐዋርያዊ አገልግሎት ከሀገር ውጭ ስለ ነበሩ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም የሰጣቸውን የክብር ዶክትሬት በአካል ተገኝተው መቀበል አልቻሉም ነበር፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመርሐ ግብሩ ላይ “ልጇ ክብር በማግኘቱ ቤተ ክርስቲያን ደስ ብሏታል” ብለዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ከዲቁና እስከ ሊቀ ጵጵስና ድረስ በትክክል የበጎች እረኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ሲሉም ብፁዕነታቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ (የክብር ዶክተር) በበኩላቸው “ሁሉ ከእርሱ፣ ሁሉ በእርሱ፣ ሁሉም ለእርሱ በመሆኑ የመከራው ቀን አልፏል፤ የተሰጠኝ የክብር ዶክትሬት ወገኑን ለማትረፍ መልካም ነገርን ሁሉ ላደረገ ሕዝብ ነው” ብለዋል። ብፁዕነታቸው በወቅቱ ለ5 ወራት እህል፣ ውኃ፣ ልብስ፣ መብራት በሌለበት ወቅት ችግር ላይ ወድቆ የነበረን ሕዝብ በእግዚአብሔር ድጋፍ ወደ ሰላም እንዲመለስ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው “ብዙዎች ከአካባቢያቸው በሚሸሹበት ወቅት በጦርነት ውስጥ ወደ ሚገኘው ሕዝባቸው በመሄድ የመከራ ቀን እንዲያልፍ ታሪክ የማይረሳው ሥራን ሠርተዋል” ብለዋል። በዚህም የከበረ ሥራን አከናውነው የከበሩትን በማክበራችን እኛም ብዙ አትርፈናል በማለት ገልጸዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ባህር ዳር ሲገቡ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ፣ የባህርዳር እና የሰሜን ወሎ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም የከተማዋ ወጣቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ባህር ዳር ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በመገኘት አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ © ተሚማ ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24

Source: Link to the Post

Leave a Reply