ሐሙስ 12/12/14 ከእለቱ ዋና ዋና ዜናዎች መካከል፡- የፌደራሉ መንግስት ህወሃት የቅድመ ሁኔታ ዝርዝሮችን በማቅረብ የሰላም አማራጭ ሙከራዎች እንዳይሳኩ እንቅፋት ሆኗል ሲል ወቀሰ፡፡የ…

ሐሙስ 12/12/14 ከእለቱ ዋና ዋና ዜናዎች መካከል፡-

 የፌደራሉ መንግስት ህወሃት የቅድመ ሁኔታ ዝርዝሮችን በማቅረብ የሰላም አማራጭ ሙከራዎች እንዳይሳኩ እንቅፋት ሆኗል ሲል ወቀሰ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታርያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም፣
መንግስት ከጦርነቱ መጀመር አስቀድሞም የሰላም አማራጭን ቅድሚያ የሚሰጠው እንደነበር አስታውሰው “ህወሃት አሁንም ወደ ጦርነት ለመግባት ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችንና ሙከራዎችን እያደረገ ነው” ብለዋል።

ለዜጎች ሁሉንም አይነት አገልግሎቶች የማቅረብና ሰላምና ጸጥታ የማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር የመንግስት ነው”ያሉት ሃላፊዋ፣ አሸባሪው ህወሃት ግን የሰላም አማራጭ ሙከራዎች እንዳይሳኩና መሰረታዊ አገልግሎቶችም እንዳይጀምሩ እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 ክልልነት በጠየቁ የደቡብ አካባቢዎች ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ::

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ስር ያሉ 6 ዞኖችና የአምስት ልዩ ወረዳ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች ክልል እንሁን ጥያቄ ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደዉ አስቸኳይ ጉባኤ፣ በአንድ ክልል እንጠቃለል ጥያቄ ተቀብሎ ከመረመረ በኋላ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ውሳኔ ተላልፏል።

በዚህም የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የጌዴኦ፣ የኮንሶ ዞኖች፣ እንዲሁም የደራሼ፣ የአማሮ፣ የቡርጂ፣ የአሌ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በጋራ ”የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል”ን የመመስረት ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠትም የህዝብ ይሁንታ መገኘት ስላለበት ህዝበ ዉሳኔ ይካሄዳል ተብሏል፡፡

 ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ እና የቻይናው ዋይቶኦ (YTO) ኩባንያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ኩባንያዎቹ በጋራ ኮምባይነር፣ ትራክተር እና የትራክተር ተቀፅላዎችን አንድ ላይ ለማምረትና ለመገጣጠም ያለመ የትብብር ስምምነት ነው የተፈራረሙት።
ስምምነቱ ከአፍሪካ ግዙፍ የተባለ የትራክተር ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት ያለመ ነውም ተብሏል።
በትብብር ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በሶላር እና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ትራክተሮችን ለማምረት በቀጣይ እንደሚሰሩም ተመላክቷል።

 ለትግራይ ተረጅዎች ተገቢውን ትኩረት የነፈገው በቀለም ልዩነት ሊሆን ይችላል ሲሉ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኻኖም ተናገሩ፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኻኖም በሰጡት መግለጫ ላይ
ባለፉት ጥቂት ወራት ከበለጸጉት አገራት አንድም መሪ ትግራይ ስላለችበት ሁኔታ ሲናገር ሰምቼ አልውቅም ብለዋል፡፡
የትግራይ ሰብዓዊ ቀውስ ግን ከዩክሬኑ ቀውስ የባሰ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
ይህም በቀለም ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምክንያት እንደሌለዉ ነዉ የተናገሩት፡፡

 በአውሮፓ የተከሰተው ድርቅ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎትን አስተጓጎለ፡፡

በዚህም ምክንያት እንደ ጀርመን ያሉ አንዳንድ ሀገራት ለኃይል ምርቶቻቸው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች እና መሳሪያዎችን ከባህር ትራንስፖርት ይልቅ ለባቡር ትራንስፖርት ቅድሚያ ሰጥተዋል፡፡

በፈረንሳይ የሚገኙት ሐይቆችም መጠናቸው በመቆነሱ የጀልባዎች እንቅስቃሴ ቆሟል፡፡
በሐይቆች አካባቢ የሚገኙ ዳርቻዎች ደርቀው መታየታቸውንም ሲጀቲኤን ዘግቧል፡፡

 ከፍተኛ ድርቅ የገጠማት ቻይና ድርቅን ለመቋቋም ሰው ሰራሽ ዝናብ ለማዝነብ ሙከራ ጀመረች፡፡

የያንግትዜ ወንዝ በዚሁ ድርቅ ምክንያት ከፍተኛ መቀነስ እንዳጋጠመዉ ሲ ጂ ቲኤን አስነብቧል፡፡

አንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በመደበኛነት ከሚያገኙት የዝናብ መጠን ከግማሽ ያነሰ ማግኘታቸውም ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎታል ነዉ የተባለዉ።
ሃገሪቱ ይህን ችግር ለመቋቋም ሰዉ ሰራሽ ዝናብ ለማዝነብ ጥረት እያደረገች ነዉ፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ኢትዮጵያዊያን

Source: Link to the Post

Leave a Reply