ሐማስ 13 እስራኤላውያን ታጋቾች እና ሦስት ታይላንዳውያን እና አንድ ሩሲያዊ ለዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አስረከበ። ግብጽ ዛሬ እሁድ የሚለቀቁ 13 እስራኤላውያን እና 39 ፍልስጤማውያን…

ሐማስ 13 እስራኤላውያን ታጋቾች እና ሦስት ታይላንዳውያን እና አንድ ሩሲያዊ ለዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አስረከበ።

ግብጽ ዛሬ እሁድ የሚለቀቁ 13 እስራኤላውያን እና 39 ፍልስጤማውያን ሥም ዝርዝር መቀበሏን አስታውቃ ነበር።

የግብጽ መንግሥት የኢንፎርሜሽን አገልግሎት ኃላፊ ዲያ ራሽዋን ዛሬ እሁድ ባወጡት መግለጫ ሐማስ እና እስራኤል ለአራት ቀናት ተኩስ ለማቆም የደረሱበት ሥምምነት “ያለ ዕንከን” ተግባራዊ እየሆነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በግብጽ እና ቃጣር አሸማጋይነት በተደረሰው ሥምምነት መሠረት ዛሬ እሁድ ነዳጅን ጨምሮ 120 ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ማቋረጣቸውን መግለጫው ይጠቁማል። ሐማስ አንድ ሩሲያዊ ታጋች እንደለቀቀ ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በሥምምነቱ መሠረት ዛሬ ይለቀቃሉ ተብለው የሚጠበቁ ታጋቾችን ሥም ዝርዝር የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መቀበሉን ቀደም ብሎ አረጋግጦ ነበር።

ትላንት ቅዳሜ ሐማስ 13 እስራኤላውያን ታጋቾች እና አራት የታይላንድ ዜጎች ለቋል። ሐማስ ከለቀቃቸው ታጋቾች መካከል አራት የጀርመን ጥምር ዜግነት ያላቸው ሰዎች እንደሚገኙበት የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒኒስትር አናሌና ቤርቦክ በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ጽፈዋል።

እስራኤል በበኩሏ ከሐማስ በተደረሰው ሥምምነት መሰረት 39 ፍልስጤማውያንን ከእስር ቤት ለቃለች። ከእስራኤል ሁለት እስር ቤቶች የተለቀቁት ስድስት ሴቶች እና 33 ወጣቶች ናቸው።

ባለፈው ዓርብ ሐማስ 24 እስራኤላውያን እና የውጭ ዜጎችን ለቆ ነበር። እስካሁን ድረስ 26 እስራኤላውያን እና 15 የውጭ ዜጎችን ሐማስ ለቋል። እስራኤል በልዋጩ በእስር ቤቶቿ የነበሩ 78 ፍልስጤማውያንን ፈታለች።

ታጋቾች የተለቀቁበት እና ፍልስጤማውያን ከእስር የተፈቱበት የእስራኤል እና የሐማስ የአራት ቀናት የተኩስ አቁም ሥምምነት በመጪው ማክሰኞ ማለዳ ያበቃል።

የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጂድ አል-ናስሪ ግን ለተጨማሪ ቀናት ይራዘማል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ለአሜሪካው ሲኤንኤን የቴቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

ህዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ለታማኝና ወቅታዊ መረጃዎች ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ።

Telegram https://t.me/ethiofm107dot8
YouTube
https://www.youtube.com/…/UCn4D20GPsAtNqN5bIC1BhFA/video

Source: Link to the Post

Leave a Reply