ሒደቱ የተገታውን የመሪ ዕቅድ ትግበራ ከወቅቱ ጋራ አስማምቶ በማስቀጠል፣ ቤተ ክርስቲያንን ለአስከፊ ጥቃት ያጋለጣት የአሠራር ጉድለት መስተካከል አለበት!

ሒደቱ የተገታውን የመሪ ዕቅድ ትግበራ ከወቅቱ ጋራ አስማምቶ በማስቀጠል፣ ቤተ ክርስቲያንን ለአስከፊ ጥቃት ያጋለጣት የአሠራር ጉድለት መስተካከል አለበት!

https://1.gravatar.com/avatar/7f09202441ad3b4b636e88820d6a7061?s=96&d=identicon&r=G
  • የአሠራር ጉድለቶችን አለማስተካከላችን፣ ከፀራውያን እንቅስቃሴ ባላነሰ ለጥቃት እንዳጋለጠን፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ በቃለ ምዕዳናቸው የጠቀሱት ትክክለኛ ነው፤
  • ኾኖም፣ ጉድለቱን ለማስተካከል የሚያስችለውን መሪ ዕቅድ፣ ምልአተ ጉባኤው አጽድቆት እንዲተገበር ከወሰነና ጽ/ቤቱም ተቋቁሞ የትግበራ ቅድመ ዝግጅቱ ከተጀመረ በኋላ በሻጥረኞች መገታቱን አርሞ ከማስቀጠል ይልቅ፣ እንደ ዐዲስ “ተዘጋጅቶ ይቅረብ” ማለታቸው ተተችቷል፤
  • ከቀትር በፊት የአጀንዳ አርቃቂዎችን የሠየመው ምልአተ ጉባኤው፣ ለአገር እና ለቤተ ክርስቲያን የሰላም እና የደኅንነት ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ ይወያያል፤

***

ዛሬ ኀሙስ፣ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠዋት፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን የጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በቋሚ ሲኖዶስ ተዘጋጅተው የቀረቡ የመነጋገርያ ነጥቦችን መነሻ በማድረግ፣ አጀንዳዎችን አርቅቆ የሚያቀርብ፣ ሰባት አባላት ያሉትን የብፁዓን አባቶች ኮሚቴ በመሠየም፣ ለምሳ ዕረፍት ተነሥቷል፡፡

በቋሚ ሲኖዶስ ቀደም ሲል ተዘጋጅተው የቀረቡለትን 32 ያህል የመነጋገርያ ነጥቦች የተመለከተው ምልአተ ጉባኤው፣ ወደ ቅዱስ ሲኖዶሱ መቅረብ የማያስፈልጋቸው፣ በቅዱስ ሲኖዶስ አካላት እና በአስፈጻሚው በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ማለቅ ያለባቸው የታጨቁ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁሟል፡፡ በመኾኑም፣ ከወቅታዊ ኹኔታ አንጻር፣ የአገርንና የቤተ ክርስቲያንን ሰላም እና ደኅንነት እየተፈታተኑ ያሉ ብርቱ ጉዳዮች ተለይተው እና ተመርጠው እንዲቀርቡለት ለአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴው መመሪያ ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት ኮሚቴው በአሁኑ ሰዓት፣ ዐበይት የመነጋገርያ አጀንዳዎችን የመለየት ሥራውን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በአገር ሰላም ጉዳይ ቀጥተኛ ሚና እንዲኖረው፣ በቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳን የተጠቀሰውን ጨምሮ፣ የቤተ ክርስቲያን ጥቃት እንዲቆም ኹነኛ መፍትሔ ማስቀመጥ፤ የመስቀል ደመራንና የአብሕርተ ምጥማቃት ይዞታዎቿ መከበር፣ በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የቅብዐት አራማጆች እስከ ሢመት የደረሱበት መደፋፈር፣ በአንገብጋቢነታቸው ከሚያዙትና በምልአተ ጉባኤው ውሳኔ ከሚሰጥባቸው የሰላም እና የደኅንነት ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል፣ በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ለከፋ አደጋ ያጋለጣት፣ በውስጣችን የሚታዩ ልዩ ልዩ የአሠራር ጉድለቶች እንደኾኑ፣ ቅዱስነታቸው በመክፈቻ ቃለ ምዕዳናቸው ማስረገጣቸው ትክክለኛ ቢኾንም፣ ለተጨማሪ ተደጋጋሚ ጊዜ፣ “የመሪ ዕቅድ ዘመናዊ አሠራር ተዘጋጅቶ ይቅረብልን፤” ማለታቸውን ግን ምልአተ ጉባኤው ተችቷል፡፡

“ቤተ ክርስቲያናችንን ለከፋ አደጋ የዳረጋት መሠረታዊ ምክንያት፣ የአክራሪዎች እና የተቃራኒዎች እንቅስቃሴ መኾኑን በውል ማወቅ አለብን፤” ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ “ይኹን እንጂ የእኛም አያያዝ፣ በክፍተት የተሞላ በመኾኑ፣ ከተቃራኒ አካላት ባልተናነሰ ኹኔታ እያስጠቃን ነው፤” ብለዋል፡፡ የአሠራር ጉድለት በማለት የገለጹትን ሲያብራሩም፣ የአስተዳደር ስልታችን፣ የፋይናንስ እና የንብረት አያያዛችን እንደኾኑና በእኒህ ረገድ በየጊዜው የሚታየው ክፍተት፣ ምእመናንን እያበሳጨ እንደኾነ መዘንጋት እንደሌለበት አስገንዝበዋል፡፡

ኾኖም፣ ችግሩን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅረፍ እና ጉድለቱን ለመሙላት፣ በራሳቸው በቅዱስነታቸው ትእዛዝ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በኾኑ ከፍተኛ ባለሞያዎች ተጠንቶና ለምልአተ ጉባኤው ቀርቦ የጸደቀ፣ እስከ 2.5 ሚሊዮን ብር የማስጀመሪያ በጀት የተመደበለት የቤተ ክርስቲያን መሪ ዕቅድ እያለ፣ ለተጨማሪ ተደጋጋሚ ጊዜ እንደ ዐዲስ፣ ተዘጋጅቶ ይቅረብልን፤ ማለታቸው፣ በምልአተ ጉባኤው ተተችቷል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት፣ በ2011 ዓ.ም. በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሥር የመሪ ዕቅድ ትግበራ ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እና ጽ/ቤቱ ተከፍቶ አመርቂ ጅምር የነበረው ቢኾንም፣ ሒደቱ ጥቅማቸውን በሚያቋርጥባቸው ሻጥረኞች ተስተጓጉሏል፡፡ ይህን በአፈጻጸም ሪፖርት ገምግሞ፣ ይዘቱን ከወቅቱ ፈተናዎች አንጻር አጣጥሞ ትግበራውን ለማስቀጠል የሚያስችሉ መመሪያዎችን ከማሰጠት ይልቅ፣ በየመደበኛ ስብሰባው፣ “ተጠንቶ ይቅረብልን” ማለት አግባብነት እንደሌለውና መታረም እንዳለበት ምልዓተ ጉባኤው ተችቷል፡፡ “ንግግሩን ያዘጋጀው አካል የራሱ ሐሳብ እንጂ የቤቱ ሐሳብ ሊኾን አይችልም፤ በአጀንዳም አልተያዘም፤ ቤቱ ቀደም ሲል ያጸደቀውን መሪ ዕቅድ አፈጻጸም ከሚገመግም በቀር ዐዲስ ይጠና ብሎ አይወያይበትም፤” ብለዋል አንድ የምልዓተ ጉባኤው አባል፡፡

ስድስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ከቀዳሚዎቻቸው የሚለዩት፣ በጥናት ላይ ለተመሠረተ የቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ለውጥ በሚሰጡት ትኩረት ነው፤ ትግበራውን ለመከታተል እና ለማስፈጸም የንግግራቸውን ያህል ትኩረት አይሰጡትም እንጂ!!

በቅዱስነታቸው ዘመነ ክህነት፣ ከጥቅምት 2006 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ጥቅምት 2012 ዓ.ም.  በተካሔዱት የምልዓተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባዎች፡-

  • የመዋቅር፣ አደረጃጀት እና አሠራር ለውጥ
  • የቤተ ክርስቲያን መሪ ዕቅድ
  • የቤተ ክርስቲያን ኹለተናዊ(መሠረታዊ) ችግሮች እና መፍትሔዎቻቸው…ወዘተ

የሚሉ ጥናቶች፣ በልሙድ ባለሞያዎች በትሩፋት ተዘጋጅተው፣ የካህናትንና የምእመናንን ከፍተኛ ድጋፍ አግኝተው፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ከጸደቁ በኋላ እንዲሠራባቸው ውሳኔዎች ቢተላለፉም፣ የትግበራ ጊዜያቸው እየባከነ፣ እነኾ ዛሬ ለፈተና ንብርብር ተጋልጠን እንገኛለን፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply