ሕብረት ባንክና ዘምዘም ባንክ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

 ሕብረት ባንክና ዘምዘም ባንክ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

 ሕብረት ባንክ፤ የቴክኖሎጂ የእውቀት ሽግግርና ልምድን ማካፈል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙርያ ከዘምዘም ባንክ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ባለፈው ረቡዕ ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም በሕብረት ባንክ ዋና መሥርያ ቤት ተፈራርሟል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረትም፣ ሁለቱ ባንኮች በቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግርና ሥልጠና አብረው የሚሰሩ ሲሆን፤ ሕብረት ባንክም በዘርፉ ያለውን የካበተ እውቀትና ልምድ በማካፈል፣ ለዘምዘም ባንክ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡  
የስምምነት ሰነዱ በባንኮች መካከል ሲፈረም በአይነቱ የመጀመሪያው መሆኑን የገለፁት የሕብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ከበደ፤ ስምምነቱም በትብብርና በውድድር ውስጥ አብሮ መስራትን የሚያበረታታ፣ የውጭ ምንዛሪ ወጪን የሚያስቀርና የውስጥ ሠራተኞችን አቅም የሚገነባ ነው ብለዋል፡፡
የዘምዘም ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ መሊካ በድሪ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ በባንኪንግ ኢንዱስትሪው ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ገልፀው፣ የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለማስቀረትና የዕውቀት ሽግግርን ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ሁለቱ ባንኮች የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ የተለያዩ ሥራዎች ላይ በቅንጅት ለመሥራትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል፡፡
 ሕብረት ባንክ “ኦራክል ፍሌክስኪዩብ ኮር ባንኪንግ ሲስተም”ን በራሱ ከመተግበሩ ባሻገርም፣ በቅርቡ የሞባይል ባንኪንግ አፕሊኬሽኑንም በራሱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ማዘመኑ የሚታወቅ ነው፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply