ሕወሓት በመከላከያ ሰራዊቱ፣በአማራ ልዩ ኃይል፣ሚሊሻና ፋኖ እየደረሰበት ባለው መራር ሽንፈት ከወልቃይት፣ሁመራና ማይካድራ ከተሞች ከመልቀቁ በፊት በንፁሀን አማራዎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል…

ሕወሓት በመከላከያ ሰራዊቱ፣በአማራ ልዩ ኃይል፣ሚሊሻና ፋኖ እየደረሰበት ባለው መራር ሽንፈት ከወልቃይት፣ሁመራና ማይካድራ ከተሞች ከመልቀቁ በፊት በንፁሀን አማራዎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደፈፀመ ማረጋገጡን የባልደራስ መኢአድ ቅንጅት አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የባልደራስ መኢአድ ቅንጅት ሀገራዊ በሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ህዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ በሚገኘው በባልደራስ ዋና ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። ቅንጅቱ በሰጠው መግለጫ ሕወሓት የራሱን የታጠቁ የልዩ ኃይልን፣ የሚሊሻ አባላትን እንዲሁም ጀሌውን ኦነግ ሸኔን በመሰብሰብ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 4:30 ሰዓት ጀምሮ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጨለማን ተገን በማድረግ የወሰደው እጅግ ዘግናኝ የሆነ ጭፈጨፋን ታሪክ ይቅር የማይለው ትልቅ ሀገራዊ ክህደት መሆኑን ጠቅሶ መላው ኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲገነዘበው አሳስቧል። ሕወሓት በመከላከያ ሰራዊት ላይ ከፈፀመው እኩይ የሀገር ክህደት ወንጀል በተጨማሪ በአማራ ክልል ዳንሻ እና ጠገዴ ሶሮቃ በኩል ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣የአማራ ልዩ ኃይል፣ የአማራ ሚሊሻና ፋኖ እየወሰዱት ባለው የማጥቃት ዘመቻ መከላከያ ሰራዊቱ ድልን እየተቀዳጀ መሆኑን ቅንጅቱ አውስቷል። ሕወሓት በመከላከያ ሰራዊቱ እና በአማራ ልዩ ኃይል እየደረሰበት ባለው መራር ሽንፈት ከወልቃይት፣ሁመራና ማይካድራ ከተሞች ከመልቀቁ በፊት በንፁሀን አማራዎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደፈፀመባቸው ማረጋገጡን አስታውቋል። በመሆኑም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕወሓት እና በኦነግ ሸኔ አማካኝነት በኡትዮጵያ ላይ የከፈተውን ጦርነት ስለ ሀገሩ፣ስለወገኑ ሲል ከመንግስት ጎን አብሮ በመቆም የድርሻውን እንዲወጣ ሲል የባልደራስ መኢአድ ቅንጅት አሳስቧል። ሕወሓት እና ኦነግ ሸኔ።ባልታጠቀ ንፁሀን ህዝብ ላይ እየወሰዱት ያለው እጅግ አስከፊ የጅምላ ጭፍጨፋ የነጻነቱ ቀን እግራቸው ስር መድረሱን አለመረዳታቸውን ያሳያል ብሏል ቅንጅቱ በመግለጫው። በመሆኑም የባልደራስ መኢአድ ቅንጅት 6 አስቸኳይ ጥሪዎችን አድርጓል። ይኸውም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ ማንነትን መሰረት እያደረጉ የጅምላ ጭፍጨፋ እየፈፀሙ ያሉት የሕወሓትና የኦነግ ፅንፈኛ ቡድኖች በአሸባሪነት እንዲፈረጁ አጥብቀን እንጠይቃለን ብሏል ቅንጅቱ። የባልደራስ መኢአድ ቅንጅት ሲቀጥል ለ20 ዓመታት ያህል በቀበሮ ጉድጓድ ተቀምጠው ለሀገራቸው ሉአላዊነት መስዋዕት ሲከፍሉ ለነበሩትና በፅንፈኛው የሕወሓት ቡድን በአሰቃቂ መልኩ ጭፍጨፋ ለተፈለመባቸው የመታሰቢያ ሀውልት እንዲቆምላቸውም ጠይቋል። የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገራትም ሀገራችን ፅንፈኛውን የሕወሓት ቡድን በህግ ተገዥ ለማድረግ በሚል የገባችበትን ጦርነት ተገንዝበው ሕወሓትን በማውገዝ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንዲሰለፉም ተጠይቋል። የቅንጅቱ ከመንግስት ጋር ያለው የፖለቲካ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ ሕወሓት በመከላከያ ሰራዊት ላይ በፈፀመው የክህደት ወንጀልን በማውገዝና በመታገል በኩል ግን በሀገርንና በሕዝብን አንድነት ላይ የመጣ ጠላት በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከመከላከያ ጎን እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል። በተጨማሪም በከሀዲ ቡድኑ ጥቃት ከፍተኛ የሰው ህይወትና የንብረት ውድመት መከሰቱን የገለፀው የባልደራስ መኢአድ ቅንጅት ሀገር በቀል እና አለም አቀፍ የሲቪክ ማህበራትና የሀይማኖት ተቋማት ለተጎጅዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ቅንጅቱ ጠይቋል። አቻ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሀሳብ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆኖ አሁን ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን ጦርነት በአሸናፊነት ታጠናቅቅ ዘንድ ከህዝባችን ጎን በመቆም የድርሻችን እንወጣ ሲል የባልደራስ መኢአድ ቅንጅት ጥሪ አድርጓል። በባልደራስ ዋና ቢሮ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የቅንጅቱ ዋና ፀሀፊ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ መግለጫው ያነበቡ ሲሆን ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የመጡ ጋዜጠኞች በርካታ ጥያቄዎችን አንስተዋል። ህዝቡ ምን ማድረግ አለበት፣ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ምን ይጠበቃል፣የተፈፀመው ወንጀል በማንና እንዴት ይጣራና ሌሎችም ጥያቄዎች ተነስተው የባልደራስ መኢአድ ቅንጅት ም/ሊቀመንበር አቶ ማሙሸት አማረ፣የቅንጅቱ ዋና ጸሀፊ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉና የባልደራስ የህዝብ ግንኙነትና የጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ገለታው ዘለቀ ምላሽ ሰጥተውባቸዋል። ተጨማሪ መረጃዎችን ይዘን የምንመለስ ይሆናል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply