
ሕዝበ ክርስቲያኑ ጾመ ነነዌን ጥቁር ልብስ ብቻ በመልበስ በጾምና በጸሎት ምሕላ በመያዝ እንዲያሳልፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥሪ አደረገች። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ሕዝበ ክርስቲያኑ ጾመ ነነዌን ጥቁር ልብስ ብቻ በመልበስ በጾምና በጸሎት ምሕላ በመያዝ እንዲያሳልፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥሪ አድርጋለች። “ሕገወጥ የተባለው የጳጳሶች ቡድን” በመንግሥት ኃይሎች በመታገዝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምታስተዳድራቸውን መንበረ ጵጵስናዎችንና ቢሮዎችን በኃይል በመውረርና በመስበር ከፍተኛ ጥፋት እያደረገ ስለመሆኑ ተገልጧል። ”ጾመ ነነዌን ምክንያት በማድረግ በመላው ዓለም የሚገኙ ሕዝበ ክርስቲያን ጥቁር ልብስ ብቻ በመልበስ በጾምና በጸሎት ምሕላ በመያዝ በቤተ ክርስቲያን ዓውደ ምሕረት በመገኘት ወደ እግዚአብሔር ጾም፤ ጸሎትና ምሕላ እንድታቀርቡ“ ሲል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ጥሪ አድርጓል፡፡ ቋሚ ሲኖዶስ የጾምና የምሕላ አዋጅ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። “መንግሥትም ሕግ ከማስከበር ይልቅ ለሕገ ወጥ ቡድኖች ድጋፍ በመስጠት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግና መብት ሊያስከብር ስላልቻለ ሁሉን ማድረግ ወደሚቻለው አምላካችን በመማፀን ጸሎትና ምሕላ ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ተረድቷል።” ያለው ቅዱስ ሲኖዶሱ፤ ጾመ ነነዌን በመላው ዓለም የሚገኙ ሕዝበ ክርስቲያን ጥቁር ልብስ ብቻ በመልበስ በጾምና በጸሎት ምሕላ በመያዝ በቤተ ክርስቲያን ዓውደ ምሕረት በመገኘትና ወደ እግዚአብሔር ጾም፤ ጸሎትና ምሕላ እንድታቀርቡ ሲል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ “ጥቁር ልብስ የምንለብሰው በመከራ መጽናትን ለመግለጽ ነው፤ ከእውቀት በላይ የሆነውን አምላካችንን በመማፀን ፈተናዉ ከዚህም ማንም ሊያናውጽን እንደማይችል የምናረጋግጥበት ነዉ” ብሏል ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው። ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው “ዳኞች እውነት እንፈርዳለን ሲሉ ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ ፤ እኛም መከራው የሚያሰቅቀን ሳይሆን ይበልጥ ልንጸናና ልንበረታ የሚገባ መሆኑን ለዓለም ሕዝብ የምናሳይበት በመሆኑ ከጥር 29 እስከ የካቲት 1 ቀን 2015 ለሦስት ቀናት በጾምና በጸሎት በአንድ ልብ በመሆን ወደ ፈጣሪያችንን እንድትጮሁ” ሲል ጥሪ አድርጓል።
Source: Link to the Post