‘ሕዝብ ምን ቢበድል ነው?’ -ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

‘ሕዝብ ምን ቢበድል ነው?’

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ

(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና

የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

በሀገራችንም ኾነ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በሕዝብ ስም በርካታ ነገሮች ሲከናወኑ፤ እናከናውናለን ሲባልና ሲደሰኮር መስማት እጅግ የተለመደ የትላንትና የዛሬ ያልተቋረጠና የማይቋረጥ ተርዕዮ ነው፡፡

በሕዝብ ስምና ለሕዝብ ሲባል ብዙና አያሌ የውጭና የውስጥ የርስ በርስ ጦርነቶች ተካሂደዋል፤ አያሌ ንጹሃን ለሕዝብ “ጠንቅ” ናቸው ተብለው እንዲራቡ፣ እንዲጠሙ፣ እንዲሰደዱ፣ እንዲታረዙና እንዲገደሉ ተደርገዋል፡፡ ብዙዎች ስለሕዝብና ሕዝባዊነት ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ ተርበዋል፣ ተጠምተዋል፣ ተሰደዋል፣ ታርዘዋል፣ ታስረዋል፣ ተሰቃይተው – ተገለዋል፡፡ ብዙዎች ስለሕዝብ ብዙ ኹለንተናዊ – የሕይወት፣ የአካል፣ የስሜት፣ የዕውቀት፣ የጊዜና የጉልበት መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ አስከፍለዋል፡፡

ብዙዎች ስለሕዝብና ሕዝባዊነት ብለው ብዙ ነገሮችን ታግለው – ጀምረው አቁመዋል፤ መስርተው – አፍርሰዋል፤ ገንብተው – ለቁም ነገር አብቅተዋል፤ ትንሽ ኾነው ጀምረው – እልፍ አላፍ ኾነዋል፤ በኹኔታዎች ተገደው ከጨዋታ ውጪ እንዲኾኑ ተገደዋል፤ እውነትን ቢይዙም በሀሰተኞች ተቀድመው የተዘነጉ ብዙዎች በታሪክ ማህደር ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡

በብዙ መልክና ቅርጽ የተነሡት አካላት በክለባት፣ በማህበራት፣ በድርጅቶች፣ በፓርቲዎች፣ በኮሚቴዎች፣ በአደራጆች – – – ወዘተ በሕዝብ ስም ስለሕዝብ በሚል የተመሰረቱ/ ተመሰረትን ያሉ፤ ስለሕዝብ መብትና ጥቅም በተለያየ አውድ መነሻና መዳረሻቸውን ስለሕዝብ ያደረጉና አደረግን ያሉ ናቸው፡፡ በዚህም ስለሕዝብ ሁሉም በተመሳሳይ ቋንቋ የሕዝብን ኃያልነት፣ የሕዝብን ታላቅነት፣ የሕዝብን ጨዋነት፣ የሕዝብን ታጋሽነት፣ የሕዝብን አዋቂነት የደሰኮሩና የሚደሰኩሩ ናቸው፡፡

በቃለ መጠይቆች፣ በመተዳደሪያ ደንብና ፕሮግራማቸው፣ በዓላማቸው/ ዓላማችን ብለው በሚገልጹት፣ በመግለጫዎቻቸው፣ በበራሪ ወረቀቶቻቸው፣ በማስታወቂያቸው – – – ኹሉ የሚያጎሉትና የሚያደምቁት – ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጡት ሕዝብን ኾኖ እናገኛለን፡፡

ኾኖም በውስጣቸው በአመራርና አመራር፣ በአመራርና አባል፣ በአባልና አባል፣ በአባልና ደጋፊ፣ በውጭ ኹለንተናዊ ግንኙነታቸው እና እንቅስቃሴያቸው ከመሰል፣ ከተቀራራቢና ከተፎካካሪ ኃይሎች ጋር ያላቸውን እሰጣ ገባ፣ ክርክር፣ አለመግባባት፣ ሙግት፣ ክስ፣ ስድድብ፣ ንትርክ፣ ጠላትነት፣ የርስ በርስ ፉክክር፣ የርስ በራስ መጠላለፍ – – – ወዘተ ስንመለከት – በዚህ ውስጥ በርካቶች ሲዳክሩ ስንመለከት ዕውን የቱ ሕዝብ ይኾን ይህን ያልተመለከተ/ የማይመለከት እድለኛ? ያስብላል፡፡

ለአብነት የሃይማኖት አባቶቻችን በትልቁ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ፍጹም አንድ ኾነው ከዚህ በታችና ለዚህ መሣሪያ (means) በኾነው አሰራርና አካሄድ ባለመስማማት – አብዝተው ከማንም በላይ ስለፍቅር፣ ስለአንድነት፣ ስለህብረት፣ ስለይቅርታ፣ ስለይቅር ባይነት የሚሰብኩ – እንኳንስ በአንድ ቤት ውስጥ ያለን ይቅርና “ጠላትህን እንደራስህ ውደድ!” በሚል የሚያስተምሩ፤ “ለራስህ እንዲደረግልህ የምትሻውን ለሌሎች አድርግ!” ይህ የሰው ልጅ የአብሮነት – በሰላምና በፍቅር የመኖሪያ ታላቅ ዕሳቤ ነው ብለው የሚያስተምሩና ማስተማር የሚገባቸው ነገር ግን እርስ በራሳቸው ተወጋግዘው – በጠላትነት ሲተያዩ –  ዕዳ ከፋዩ ምዕመኑ መኾኑ የአደባባይ ምሥጢር ነውና ዕውን የኢትዮጵያ ምዕመን በደሉ ምንድነው?

የተፎካካሪ ፓርቲዎች በሀገራችን እንደአሸን ፈርተው – ስንቶች ፈርሰው ሲገነቡ – ግለሰቦች እንዳሻቸው ሲያንቦራጭቋቸው – በብዙ ጉዳዮች ተመሳስለው በጥቃቅን ጉዳይ ሲለያዩ፡ በትንሹ ላይ ድንበር አበጅተው – በጠላትነት የሚተያዩና እርስ በራስ ሲዘላለፉ፣ ገና የአደባባይ የሕዝብ ሥልጣን ሳይዙ የጓዳ ሥልጣን ሽሚያ ውስጥ ገብተው ብዙዎች እርስ በራስ ሲበላሉ፣ ሲከራከሩ፣ ሲካሰሱ፣ ሲዘላለፉ፣ ሲመላለሱና ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት ሲንከራተቱ –  በስሙ የተነሡለት ሕዝብ ይህ ይገባዋልን? ምን ቢበድል ነው እንዲህ የተገባው?

ገዥው ፓርቲም የውስጡንና የሀገርን ችግር ለመፍታት – “ከ6 ሚሊዮን በላይ አባላት እና ከ40 ዓመታት በላይ የፖለቲካ ልምድ አለኝ” የሚል ድርጅት ለበርካታ ቀናት ቀን ከለሊት ሲሰበሰብ፣ የችግሮቹን ምንጭ አንዴ ወደ ውጭ – አንዴ ወደ ውስጥ በማድረግ ሲንገላታና በመንፈስ አንድ መኾን አቅቶት በስብሰባ ወራትን ሲያስቆጥር – በመሰብሰብ የሀገር፣ የሕዝብና የትውልድ ብድር ግን ወለድ ከመቁጠር ሳያርፍ፣ ወር እንደኾነ ሳይታወቅ እንደዘበት ሥራ ሳይሰራ እያለፈ ደሞዝ ግን እየተከፈለ፣ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ሲጓተቱ፣ ቱሪዝም ሲዳከም፣ ሀገር ገጽታዋ ሲበላሽ፣ ሀገር በመደበኛ ሥርዓቷ መረጋጋት ስላልቻለች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ስትገባ – ዕውን በዚህ ኹሉ ሂደት የሕዝብ በደል ምንድነው?

በብዙ ቃለ መጠይቆችና ጽሑፎች ሳይማር ያስተማረን የሚሉ ምሁራን በርካታ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ምሁራን ግን እርስ በራሳቸው መመቀኛኘት፣ መናናቅ፣ መጠላለፍና በመንፈስ ተግባብቶ በሕብረትና በአንድነት በጋራ ስለጋራ ጉዳይ አለመስራትን ባሕላችን ስለማድረጋችን የትላንትም ኾነ የዛሬ ግብራችን ዐቢይ ምስክር ነው፡፡ ሳይማር ያስተማረ ሕዝብ ምን ቢበድል ነው እንዲህ አይነት ፍሬ ያስገኘውና የተገባው?

በዚህ ኹሉ ኹለንተናዊ ውጣ ውረድ ውስጥ ግን የሚነገድበት፣ የሚነሣው፣ የሚወደሰውና የሚቀነቀነው ሕዝባዊነት እንደኾነው ኹሉ ተጠቃሚውና ቀጥተኛ የጥቅም ተዋናይ የኾነው አካል ቦታ ይለዋወጥ እንደኾን እንጂ ጉዳቱ ኹሉ የሚያርፈው ሕዝብ ላይ ነው፡፡

ወክለነዋልና እንወክለዋለን ያሉት ዝሆኖች ቢጣሉ ሣሩ ከመጎዳቱ በቀር እነሱ ኹለንተናዊ ትግላቸው ከዝሆንነት ወደ ሣርነት የማይለወጥና የማይወርድ በመኾኑ የበረዳቸው፣ የተቃጠሉ፣ የታረዙ ቢመስሉም ጫፋቸውን ሳይነካ ያልፋል፡፡ የዝሆኖቹ ልምድ፣ አይነት፣ መጠን፣ ዕድሜ፣ ውበት፣ ስልት፣ ፍላጎት – – – ወዘተ በኹለንተናዊ ልዩነቶች ውስጥ እንዳለ ኹሉ የሣሩም አይነት፣ መጠን፣ ንቃት፣ ስፋት፣ አድማስ፣ ዕድሜ፣ – – – ወዘተ ኹለንተናዊ ልዩነቶች እንዳሉት ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

የሃይማኖት አባቶቻችን እርስ በራስ ባለመስማማታቸው ምን ጎደለባቸው? ገዥዎቻችን በመንፈስ አንድ ባለመኾናቸው ምን አጡ? ተፎካካሪ መሪዎች ሕብረትና አንድነት የሌላቸው በመኾኑ ምን ጥቅም ጎደለባቸው? በትልቁ ባይችሉ በጥቃቅኑ መሪዎች በመባል ረክተው የለ? ምሁራን እርስ በራስ በመመቀኛኘትና በመናናቃቸው ምሁር ከመባል አልተሰረዙ – ምን ጎሎባቸው ቁጭት ይፍጠሩ? ሚድያዎቻችን በመልክና በባለቤትነት የኛ ቢመስሉም በአስተሳሰብና አመለካከት የሌሎች ኾነው በእምነት፣ በእውቀትና በግብር የሌሎች ተወካይ በመኾናቸው አድማጭና ተመልካች መች አጡና ወደ ልቦናቸው ይመለሱ?

ሌላውን ኹሉ ትተን የቅርብ ጊዜ የሀገራችንን ወቅታዊና ነባራዊ የሥልጣን ፖለቲካ ውጣ ውረድ እንኳ ብንመለከት ትርጉም ባለው መንገድ አስተውለን ስንመለከት ተሸናፊዎች የመሰሉን አሸናፊዎች፤ አሸናፊዎች የመሰሉን ተሸናፊዎች መኾናቸውን ሰንቶች አስተውለን ይኾን?

ይሁን ግድ የለም!!! ከሥልጣን ፖለቲካ ወደ ፖለቲካ ባልተሻገረበት፣ ገዥና ተገዢ በሥልጣን ፖለቲካ ኹለንተናዊ አስተሳሰብና አመለካከት ቅኝ በተገዛበት፤ ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ ዕሳቤ ባላደገበት፤ ከጓዳ ፖለቲካ ወደ አደባባይ ፖለቲካ ባልተቀየረበት፤ ከወሬ ወደ ተግባር – ከስሜት ወደ ምክንያታዊነት ባልተለወጠበት፤ ግልብ ባዶ አስመሳይነት ሞልቶ በፈሰሰበትና በብዙዎች ልቦና ላይ በነገሠበት፤ ትርጉም ያለው ሀሳብ ከተራ ፍሬ አልባ ፕሮፕጋንዳ ባልተለየበት – ሕዝብ መነገጃ መኾኑ በአደባባይ በድምቀት በሚታይበት ኹለንተናዊ ኹኔታ/ዎች ውስጥ እንዲህ አይነት ተርዕዮዎች መበራከትና መታየት አይደንቅም፡፡

ይህ ኹሉ ሲኾን ግን ኹለንተናዊ ዋጋ የከፈለው፣ እየከፈልን ያለነውና የምንከፍለው እንደሕዝብ ነው፡፡ ሕዝብ ምን ቢበድል ነው ሌሎች በስሙ ከመጠቀም በላይ ዋጋ ሲያስከፍሉት የኖሩትና የሚኖሩት? ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

 

 

 

 

 

Leave a Reply