
ሕገ ወጡ ቡድን የነጌሌ አርሲ ወረዳ ቤተ ክህነትን በመውረር ላይ ሲሆን በአሰላ ከተማ መንበረ ጵጵስናው በሚገኝበት ደብረ ምጽላል ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቅዳሴ እንዳይከናወን መደረጉ ተገልጧል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ/ም … አዲስ አበባ ሸዋ የፍርድ ቤትን ዕግድ ችላ በማለት ሕገ ወጥ ተግባሩን ማከናወኑን ቀጥሏል የተባለው ቡድን የካቲት 28/2015 በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት የነጌሌ ወረዳ ቤተ ክህነትን መውረሩ ተገልጧል። ሕገ ወጡ ቡድን በእሥር ላይ የሚገኙትን የወረዳ ቤተ ክህነቱን ሥራ አስኪያጅና ጸሐፊ ይዞ ወደ ጽሕፈት ቤቱ በመውሰድ እና በኦሮሚያ የጸጥታ አካላት በመታገዝ ንብረት እንዲያስረክቡት በማድረግ ላይ ስለመሆኑ ተመላክቷል። ለሀገረ ስብከቱ ተሹሜያለሁ ያለው ግለሰብ ከሌሎች ሦስት ተሿሚዎች ጋር በመሆን በ5 ፓትሮል መኪና የኦሮሚያ የጸጥታ ኃይሎች ታጅቦ ቤተ ክርስቲያኗን ለመውረር እየሞከረ በመሆኑ ውጥረት ነግሷል ተብሏል። የግለሰቡን ወደ ሀገረ ስብከቱ መግባት ተከትሎ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ውጭ አንቀበልም በማለት ከአገልግሎት ቦታቸው ሳይገኙ ስለመቅረታቸው የተሚማ ዘገባ አመልክቷል። በተያያዘ በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት መቀመጫ አሰላ ከተማ መንበረ ጵጵስናው በሚገኝበት ደብረ ምጽላል ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ሥርዓተ ቅዳሴ ታጉሏል። በሕገ ወጥ ተሿሚውም በኩልም ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሥራ እንድትገቡ የሚል የማስጠንቀቂያ መልእክት የተጻፈላቸው ስለመሆኑ ተገልጧል።
Source: Link to the Post