መለስ ዜናዊ መሓሪ ዮሐንስን የመሰሉ እሳት የላሱ ልጆችን ተክቶ አልፏል! ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

በጣም ታሪካዊ ታሪክ በሀገራችን እየታዬ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ የቱን ይዘህ የቱን እንደምትጥልም አታውቅም፡፡ የዐይን ማረፊያ፣ የጆሮ መጽናኛ የሚሆን ደግ ነገር ለማግኘት ቀኑን ቀርቶ ዓመቱን በሙሉ ብትኳትን አሁን ባለው ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ አንድም ነገር አታገኝም፡፡

የመሓሪ ዮሐንስ ጉዳይ ደግሞ ትንሽ ለየት ይላል፡፡ በትራግይ ቲቪ የትግርኛ ፕሮግራም እንደተከታተልኩት በርሱ እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ይቅርና መንግሥትም የለም፡፡ በዚያ ሰሞን የተላለፉ የግፉኣን ሰቆቃም የነዶ/ር ዐቢይ ቅንብር የውሸት ድራማ ነው – ተጋሩን ለመነጠልና በሌሎች ለማስመታት፡፡ ትግራይ ቲቪ በኢትዮጵያ ምድር የሚገኝ ሚዲያ ሣይሆን አልባንያ ወይም ቻይና ውስጥ የሚገኝ እንደአቃቂ ፈረስ ግራና ቀኙን የተለጎመ የወያኔ ጋሪ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ድምፂ ወያኔ የሚባል አጋዥ የወያኔ ቱሪናፋ መጥቷል፡፡የሁለቱም ዓላማ አንድ ነው – ወያኔን ወደ ቀድሞ ሙሉ ክብሩና ግርማው መመለስ፡፡ ከዚያም በኋላ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ላይ ለ27 ዓመታት እንዳደረጉት ጥሬ እንትናቸውን በአራቱም ማዕዘን መልቀቅ፤ ጥሬ ብስናታቸውን ማበስናትና ሆዳቸው ውስጥ ለዘመናት የታቆረውን ዘረመላዊ የጎጠኝነት የተበከለና የበሰበሰ ወተት ማቀርሸት፡፡ ከዚያም ሀገሪቱን ማግማትና የፈጣሪን አፍንጫ ሳይቀር በቁናሳቸው መቁረጥ፡፡ ይሄኛውንስ አያ’ርግብን፡፡ ህልም እልም፡፡ እነዚህኞቹን ደግሞ ጥቂት እንያቸው፡፡…

ዛሬ ጧት ደግሞ በወልቃይት ድረገፅ ያው እሳት የላሰ የመለስ ልጅ በትግርኛ ተናገረው ተብሎ ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ እንዳነበብኩት ከማስገረም አልፎ ሰዎቹ ምን ዓይነት የዕብደትና የጉሽ ጠላ ስካር ከፍተኛው ደረጃ ላይ እንደደረሱ በመገመት ክፉኛ ያሳዝናል፡፡ እነዚህን ሰዎች ከዚህም ሳይብስባቸው ወደ ጠበል የሚወስዳቸው ጤናማ ሰው ጠፋና እነሱም ሀገራችንም ተያይዘን ችግር ውስጥ ገባን፡፡ ይሄ ሆድ ለካን ስንቱን ያሳያል!

እውነትም መለስ አልሞተም፡፡ ብዙ ታዳጊ ወጣትና ጎልማሣ መለሶች አሉ፡፡ ትግራይ ቲቪን ክፈት፤የድምፂ ወያኔን ቲቪና ሬዲዮን ክፈት፤ “ህገ መንግሥቲ ተጣሂሹ፤ ህገ መንግሥቲ ይኮበር” ሲሉ በብዛት ታገኛቸዋለህ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በበላዔ-ሰቦች ልጆቹ እንዲያ ሲረገጥና ተነግሮ የማያልቅ ዘግናኝና ሰቅጣጭ ግፍና በደል ሲደርስበት፣ የኢትዮጵያ ወጣት እንዲያ ሲኮላሽና በየእስር ቤቱ በወያኔዎች እየተደፈረ በሲዖል ትሎች ሲንገበገብ፣ ወያኔ ትግሬ ከየጉራንጉሩ እየተጠራራ የኢትዮጵያን ሀብትና ሥልጣን በግላጭ ሲቀራመት፣ ቤንሻጉልና ሶማሌ – ጉሙዝና አፋር ክልሎች በወያኔ የእጅ አዙር ሰላዮችና የሦስተኛ ክፍል ምሩቃን  ጄኔራል ተብዬዎች ተይዘው ሀብታቸው ሲቦጠቦጥና በይምሰል ፌዴራሊዝም ሀገር ስትፈርስ ትንፍሽ ያላሉ ተጋሩ ዛሬ የነካቸው ነገር በውል ሳይታወቅ “ህገ መንግሥት ይከበር” የሚለው የሞኝ ፈሊጥ ነጋ ጠባ ከአፋቸው የማይለይ የዘወትር ጸሎታቸው ሆኗል፡፡ መቼም ሀፍረትና ይሉኝታ ከትግራይ ምድር ጠቅልላ ከወጣች ብዙ ዓመታትን አስቆጥራለች – ሊያውም ጥንትም በዚያ ሥፍራ ኖራ ከሆነ (ገበሬውና ባላገሩ አሁንም ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ደግ ሕዝብ እንደሆነ እገምታለሁ – ችግሩ ፊደል ቀመስ የሆነው ኤሊት ተብዬው ይመስለኛል)፡፡ አንድ ትልቅ ክፍለ ሀገር በብዙ መለሶች እየታመሰች በምትታይበት የፉከራና የሽለላ ቱማታ ዘመን “ወያኔዎች ብቻቸውን ናቸው” እያሉ በመጽናናት ከፊት ለፊት የተደቀነን መራራ ትግል ለማንኳሰስ መሞከር አደጋ ሊኖረው እንደሚችል ብልኆች መጠራጠር አለባቸው፡፡ ወንድሜ የበላን ያብላላዋልና እንኳንስ ለዘመናት የተረጨ የዘረኝነት መርዝ ታክሎበትና ትንሽም በላ ብዙ በስሜት የታወረ ወገናዊነት በምክንያት የተደረደረን እውነት ክፉኛ ሊገዳደር መቻሉ ግልጽ ነውና ስንቅና ትጥቅን ጠበቅ ማድረግ ይሻላል፡፡ “ ‹አይመጣም›ን ትተሸ ‹ይመጣል›ን ባሰብሽ” ነው ነገሩ፡፡

ጤናማ ተጋሩ ቢቆጠሩ አሥር የሚሞሉ አይመስለኝም፡፡ ካልሰለቻችሁኝ የምችለውን ያህል መቁጠር ልጀምር – የአርአያ ልጆች ገብረ መድኅንና (ዶ/ር) ኃይሉ  አርአያ፣ የገብረ ሥላሤ ልጆች አስገደና አምዶም ገ/ሥላሤ፣ ጌታቸው ረዳ(ኢትዮሰማይ ድገፅ አዘጋጅ)፣  ወዲ ሻምበል፣ የኢትዮሚዲያው አብርሃ በላይ (በተለይ በሰሞኑ ትንታኔው)፣… ሊያቅተኝ ነው መሰል፡፡ “ቸርነቴን ላብዛው”ና  ሣምራውያን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ተጋሩ – በገጠርም በከተማም – በግርድፍ ሥሌት አሥር ሽህ ይሁኑ እንበል ግዴለም፡፡ የማይሞቀው የማይበርደውን ግዴለሽ፣ “ከነገሩ ጦም ዕደሩ” ባይ እንደኔ ፈሪውን፣ በሀገራችን ምን እየተካሄደ እንዳለ እንኳን የማያውቀውን ገበሬና ባላገር  … ለጊዜው ከቁጥር ሳናስገባ እንተወው፡፡ በተረፈ ሆድ ይፍጀው፡፡ …..

“ከሰው መርጦ ለሹመት፣ ከእንጨት መርጦ ለታቦት” አዲዮስ! ዱሮ ቀረ፡፡በኔ የልጅነት ዘመን ሰው ሲሾም ተጠንቶ ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ቅድሚያው ጥናት የሰውዬው/የሰውዬዪቱ ዘር ሆነና ተቸገርን፡፡(ሴትም ሰው ናት!)

ይቺ “ምክትል ከንቲባ” እና “ምክትል አገረ ገዢ (በዘመኑ ቋንቋ ፕሬዝደንት)” የምትባል  አዲስ ፈሊጥ ከየት የመጣች ትሆን ግን? ዋናው ከንቲባና ፕሬዝደንት ጨረቃ ላይ ወይንስ ሰላማዊ ውቅያኖስ ወለል ላይ እንደምትገኝ በምትታመነው ቤርሙዳ ከተማ ውስጥ ይገኙ ይሆን? ደግሞስ ይቺ የፉጌ አባባል የማትፎርሸው እስከመቼ ድረስ ነው? የትግራዩስ ግዴለም – መለስ ቢሞትም በመንፈስ አብሯቸው ስላለ እስከወዲያኛው በምክትልነት ቢጠሩ ግልጽ ነው፡፡ የአዲስ አበባው ማለቴ የፊንፊኔው ምን የሚሉት ምክትል ከንቲባ ነው? ስላልገባኝ ነው፡፡ … ብዙ ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በትግርኛና በኦሮምኛ ካማርኛ በቀር በሌላም ሲናገሩ ሌሎች ሰዎች የሚረዷዋቸው አይመስላቸውም፡፡ ሞኝነት ነው፡፡ የቋንቋን ባሕርይ ካለመረዳት የሚመነጭ ሞኝነት፡፡ በቋንቋ ምክንያት የዘረኝነት ልምሻ የሚጠናወታቸው ሰዎች ቋንቋ በዘር ሐረግ የሚተላለፍ ይመስላቸዋልና እነሱ ሲናገሩ የሚያዳምጡና የሚረዱ የነሱ “ወገኖች” ብቻ ይመስሏቸዋል – ይህ ነገር ጥናት የማያስፈልገው ጠቅላላ እውነት ነው፡፡…

አቶ ማነው እቴ ዶ/ር ደብረፅዮን ገረሚቻኤል የትግራይ ም/ፕሬዝደንት፤ ኢንጂኔር ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ መባል ከተጀመረ ዓመት ሊደፍን ምንም ያህል አልቀረውም – በለውጡ ሰሞን ከተሾሙ፡፡ የነዚህን ቦታዎች ዋና ሰው ለማግኘት ስባዝን እኔም ዓመት ሊሞላኝ ነው፡፡ እንታይ እዩ ጉዱ! ስለምታይ ነው እንዴ እንደዚህ የሚያጩቦረቡሩን በሌለ ባለሥልጣን? በውነት ምን ማለት ነው? ነው ሁላችንንም ገሪባ ‹ባላገር› አደረጉን? እንዴት ያለ ክፉ አዚም፣ ምን ዓይነት ፀላዔ-ሠናያት ይሆን የታዘዘብን!

እውቴን ነው – ዱሮ ሹመት እንደገና ዳቦ ለማንም ከበር መልስና ከበር ውጪ የሚታደል አልነበረም፡፡ በቆዬው ሲገርመኝ የሰሞኑ ደግሞ ከማስገረም አልፎ በጅልነት እያሳቀኝ ነው፡፡ ክፋቱ ከሚሾሙት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹን በሚገባ አውቃቸዋለሁ፡፡ እናም እንደመጥፎ ዕድል ሆኖብኝ ሳጤናቸው አንዳቸውም ለሹመት የሚበቁ አይደለም፤ ግን ግን “አንተ የምታውቃቸው ሰዎች ሁሉ እንዴት ወልጋዳ ሊሆኑ ቻሉ?” ብላችሁ ደግሞ መመለስ የሚያቅተኝን ጥያቄ እንዳትጠይቁኝ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው እውነተኛው ጽንስ ተወልዶም በሆድ ውስጥም እየጨነገፈ እንግዴ ልጁ ስለሚያድግ አሁን አሁን ሰው ብናጣ አይፈረድብንም፡፡ በክፋት አምባሳደርነታቸው ምክንያት ጥሎባቸውና የክፋት ሥራው በነሱ ስለሚብስ በወያኔዎች እንፈርዳለን እንጂ እኛም እኮ የለየልን ሟደድ ጅቦች ሆነናል፡፡ እስኪ በየመሥሪያ ቤቱ ሂዱ – በሙስናው መስፋፋትና በዜጎች እምብርት የለሽነት ትደነግጣላችሁ፡፡ ለእውነት መቆም ፋራነት ነው፤ለሀገር ማሰብ ጅልነት ነው፤ ለወገን ማሰብ ዕርም ሆኗል፤ በተገኘው መንገድ ሁሉ ራስን በገንዘብና በሥልጣን መካብ የሥልጡንነትና የዘመናዊነት መለኪያ ከሆነ ሰንብቷል፤ የብዙዎቻችን የዘመኑ ፋሽን “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” ከሆነ ዋል አደር አለ፡፡ አዲዮስ ኢትዮጵያ! አዲዮስ ሰብኣዊነት! አዲዮስ ብሔራዊ የሀገር ፍቅር ስሜት!

ወያኔ በረጨብን የዘረኝነት ዲዲቲ ምክንያት ልንወጣውና ልናባርረውም ያልቻልነው ችግር ውስጥ መዘፈቃችንን የታወቀ ነው፡፡ እኔም በበኩሌ ለ20 እና 30 ዓመታት ላያችን ላይ ተከምሮ እንደዛር ሲያስጨፍረን የነበረ የዘረኝነት ልክፍት በአንድ አዳር እንደማይለቀን አውቃለሁ፡፡ ግን ግን እንዲህ ማድረግ የምንችል ይመስለኛል፤ እንዲህ – ከዘረኝነት አረንቋ ተዘፍቀን መንጠራወዛችን የማይቀርልን ዕዳ ከሆነ በዘራችን ውስጥ የሚገኙ የተማሩና ከሙስና የፀዱ፣ በዕድሜም ሆነ በተሞክሮ የበሰሉ፣ ቀናነትና ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያላቸው የራሳችን ጎሣ አባላትን እናፈላልግና እንሹም፡፡ በቃ፡፡ ይሄ ትልቅ መፍትሔ ነው፡፡ እርግጥ ነው – ድብቅ ዓላማና ፍላጎት ካለን እነዚህን መሰል የኛ ጎሣ አባላት ነገር ሊያበላሹብን፣ ሕዝብንም ሊያነቁብን  ይችላሉ ብለን እንፈራቸዋለንና ማስጠጋቱንና መሾሙን አንፈልገው ይሆናል፡፡ ይሁንና ለልጆቻችን ቀጣይ የወደፊት ሕይወት ስንል በዚህች መንገድ ጥቂት ለመጓዝ እንሞክር፡፡ እንዲህም ስል ከፍ ሲል የተናገርኩትን በመርሳት አይደለም – እንዲያው ከንፍሮም ጥሬ ይወጣልና በመጠኑ የተበላሹና በቀላሉ ሊስተካከሉ የሚችሉ ዜጎች ከሀገር ውስጥም ከውጪም ከተገኙ በሚል ተስፋ ነው፡፡ እንጂ እደግመዋለሁ – ዘመናችን አበለሻሽቶናል፡፡ ካህኑና ሼካው ሳይቀሩ አይደሉም እንዴ ከላይኛው የፈጣሪ መንገድ ይልቅ የታችኛውን ሰው-ሠራሸ ገንዘብ መርጠው እንደ ሙሤ ጽላትና እንደመሀመድ ካባ ብርንና ዶላርን የሚያመልኩት?… አንተዋወቅም?… እ?

ወደ አስቂኙ ሹመታችን ልመልሳችሁ፡፡ ለምሣሌ ማንትስ የተባለችውን ካብ አይገባ ድንጋይ አምባሳደር አድርጎ ከመሾም ስንትና ስንት በሳልና ፖለቲካ ዐዋቂ የኦሮሞ ምሁራን ሞልተዋል፡፡ የአዲስ አበባን አካባቢ ሙልጭ አድርጎ በሙስና ዘረፈ የተባለን ሰው በአዲስ የወይን ጠጅ አቅማዳ ውስጥ ጨምሮ ሥራን ከማበላሸትና ትዝብት ውስጥ ከመግባት ስንትና ስንት ኦሮሞ ኢንጂኔሮች በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም አሉ፡፡ ብዙ ጥፋቶች ሲፈጸሙ እናያለን፡፡ እንናገርማለን – ግን አሁንም ሰሚ የለም፡፡ ይሄ የአራት ኪሎ ወንበር በአሲድ ካልታጠበ ወይም በሸንኮራና በለብቃየሱስ ፍቱን ፀበሎች ለ21 ዓመታት በተከታታይ ካልተጠበለ ምድረ ጆሮ-አልባ እየተሰገሰገበት የሕዝብና የሀገር ዋይታና ልቅሶ መቀጠሉ ነው፡፡ እኔስ የምሥራች ቀኔ ቀርባለች ልገላገል ነው፡፡ የዚህችን ሀገር ነገር ከ’ንዳለመስማት የበለጠ ፀጋና ቡራኬ ደግሞ የለም፡፡ የሰዎች ‹ሬዚስታንስ›ና ‹ፊውዝ› ደግሞ ይገርመኛል፡፡ ምነው እኔንም ኬሬዳሽ ባደረገኝ!

በነገራችን ላይ የዚህች ሀገር አንዱና ዋናው በሽታ አንድን ሰው ስንወድና ስናፈቅር ለከት የሌለን መሆናችን ነው፡፡ በልክና በምክንያት ማፍቀርና መጥላት አናውቅበትም፡፡ ስናሳዝን! አንድን ሰው ስናፈቅር ወዲያውኑ – በልሣነ እንግልጣር ልናገር እባክህን – ወዲያውኑ immaculate and/or omnipotent and/or omniscient and/or omnipresent … እናደርገውና ከፍ ሲል ከእግዚአብሔር ዝቅ ሲል ደግሞ ከመላእክት ጎን እናስቀምጠዋለን፡፡ ያንን ሰው ሲነኩብን እናብዳለን፤በዚያም ምንያት ሰውን አለ ኃጢኣቱ እናሳድዳለን – ይህን ዓይነቱን የሚያነበርር “ፍቅር” infatuation ይሉታል ፊደል የቆጠሩቱ፡፡ ብሃፂሩ እንታወርና እናርፋለን፡፡ እሱም ፍቅራችንን ወይም ጥላቻችንን በአግባቡና በአመክንዮ manage ማድረግ አይችልም ወይም ያቅተዋል፡፡ ስለሆነም ስናፈቅረው ክንፍ አውጥቶ አየር ላይ እስኪንሳፈፍ ያብጥብናል፤ ከኛም ከመሬትም ይርቃል፡፡ ሲወርድ ግን አይጣል ነው – እየተምዘገዘገ ወርዶ ይፈጠፈጣል – ኮድኩዶ የያዘን ቋሚ ባህላችን፡፡ ያን መሰሉን ሰው ካስቀመጥንበት እግዚአብሔራዊ መንበር ስናጣው ደግሞ በተቃራኒው ጨርቃችንን እንጥላለን፡፡ ለዚህ ነው ፍቅራችንም ጠባችንም ሳያምር ቀርቶ ለዘመናት ስንወዛገብ በመኖራችን ምክንያት በመጨረሻው መጨረሻ እንደዚህ ያገር ቂጥ ሆነን የቀረነው – “ያገር መቀመጫ” ብለው ስለማያምር ነው፡፡ ብታምንም ባታምንም ችግራችን ሁሉ የሚሽከረከረው እዚህ አካባቢ በምናገረውና አንተም አንቺም ጠንቅቃችሁ በምታውቁት ነገር ዙሪያ ነው፡፡ እኛ ያላሳዘንንን ታዲያ ማን ያሳዝን? “እያደሩ ማነስ” በሚል አዝማች ዘፈን ወጥቶ ይሆን? I do not really know if I have become a little bit pessimist. It is good, of course, to be optimist, when situations allow. But do they allow now? It may depend upon our perspective.

ታከለ ኡማን ዕጥፍ ድርብ የሚያስከነዱ ኦሮሞዎች ጠፍተው አይደለም፤ እነእንትናን በሰማይና በምድር የርቀት ልዩነት የሚበልጡ ኦሮሞዎች ታጥተው አይደለም፡፡

  ኤዲያ ምን አስለፈለፈኝ ግን … ምንስ ጥልቅ አደረገኝ፡፡ ስደተኛ በመሸበት አድሮ መሄድ እንጂ በሰው ቤት ምን ያገባዋል? ግን አንዱ በአንዱ ሲስቅ በምናባክነው ወርቃማ ጊዜ እየጠለቀች ያለችዋን ጀምበር እጅግ ከመሸም ቢሆን ለመጠቀም ሁሉም ብልኅና አስተዋይ ቢሆን ይሻለዋል፡፡ ባዶ እግሩን የሚሄድ ሕዝብ መሀል፣ በውኃ ጥም እየሞተ ያለ ሕዝብ መሀል፣ ሊያውም ለማይረባ ህክምና ሲባል በወሳንሳ ሸክም ብዙ ኪሎ ሜትሮችን የሚጓዝ ሕዝብ መሀል፣ በቀን አንዴ እንኳን ከደረጃ በታች የሆነ ምግብ መቅመስ የማይችል ሕዝብ መሀል፣ በትምህርት ዕጦት በደነቆረ ሕዝብ መሀል፣ ስደትና ሞት ርስተ ጉልቱ በሆነ ሕዝብ መሀል፣ ድህነት ቤቱን በሠራበት ህዝብ መሀል፣ ጎጠኝነትና ዘረኝነት ያሰከረው ወጣትና ጎልማሣ በወያኔ ከንቱ ልፋፌ-ጽድቅ ተማርኮ እርስ በርሱ ሊጨራረስ ያሰፈሰፈ ውሪ መሀል፣ በጥላቻና ቂም በቀል አብደው ወገንን ከወገን ለማፋጀት የቋመጡ አክቲቪስት ተብዬዎች በሚርመሰመሱበት ሕዝብ መሀል፣ ዕድሜ የማይገድባቸው ዶን ኪሾቶች በሞሉባት ሀገር ውስጥ  …. ከድሃው በተሰበሰበ የግብር ገንዘብ በአውሮፓ ሊሞዝንና በአውሮፓ ስታይል በተሠራ ቤት እየኖሩ በፖለቲካ ሰበብ ሕዝብ ላይ መሽናትና ማስታወክ የሚቀርበት ዘመን እንዲመጣ በተለይ እኔን መሰል ጭቁኖች ሌት ከቀን እንጸልይ፡፡ … ብቸኛ መድሓኒታችን ፈጣሪ ነው፡ የሰውን እስኪያንገሸግሸንና እስኪያቅረን አየነው፡፡ አጎቴ በርሀብ እየሞተ በከፈለው የግብር ገንዘብ ጡረታ ለወጣ ፕሬዝደንት ለቤት ኪራይ ብቻ በወር ከ400 ሽህ ብር በላይ ሲከፈል እንደማየት የትውልድና የመንግሥት መረገም የለም፡፡ ብዙ ጉድ ነው ያለው፡፡….ብቻ እሱ ይፍረድ! ግን ምን አገባኝ!!…..

ቀጣይዋን ግጥም ከሰው ጽሐፍ አንብቤ በቃሌ ጭምር ይዣታለለሁ – ተፅዕኖዋ ቀላል አይደለም፡፡

“ ‹እኔ ምን አገባኝ!› የምትሏት ሐረግ፤

እሱ ነው ሀገሬን ያረዳት እንደበግ፤”

በሚል ግጥም ልጽፍ ብድግ አልኩኝና፤

“ምን አገባኝ!” ብዬ ተውኩት እንደገና፡፡ (ደስ አትልም?)

[email protected]

Leave a Reply