
መላው የኦርቶዶክስ ልጆች አዲሱን ዓመት በዘፈንና ዳንኪራ ሳይሆን በቤተክርስቲያናቸው በጸሎት ፣ በምህላ፣ የቻለም ደግሞ በመጾም፣ እግዚአብሔርን በመመለመን እንዲቀበሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጥሪ አስተላለፈች። አሻራ ሚዲያ ነሐሴ 30/2015 ቤተክርስቲያን ይህን ጥሪ ያስተላለፈችው የአዲሱን ዓመት አቀባበል በተመለከተ በሰጠችው መግለጫ ነው። በዚህም የጷጉሜን ወር ፮ ቀናት መላው ኦርቶዶክሳዊ በጸሎት እና በምህላ እንዲያሳልፍ ታውጇል። ቤተክርስቲያን ፤ ዘመኑ ከደስታ እና የምስራች ይልቅ ሀዘንን የምንሰማበት ዘመን ስለሆነ ምዕመናን የተቸገሩትን የተራቡትን ፣ የተፈናቀሉትን እና የተጎዱትን እያሰቡ በጾምና በጸሎት እንዲያሳልፉ ስትል ጥሪዋን አቅርባለች። ምዕመናን በዚህ ወቅት ከዘፈን እና ከዳንኪራ እንዲርቁ አሳስባለች። ብፁህ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ እና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቃ ጳጳስ ፤ ” አንዳንድ የዘፈን ግብዣዎችን እየሰማን ነው ፤ ሀገር በሚያልቀስበት፣ የንፁሃን ደም በሚፈስበት ሰቆቃ በበዛበት ረሃብ ችግር በሰፈነበት የዳንኪራ ግብዣ እየሰማን ነው ” ብለዋል። ” ለምንም የማይጠቅሙ ብዙ ነገሮች እየተስተጋቡ ነው ” ያሉት ብፁዕነታቸው ” ይህን እየሰማን ያለነው መደፋፈሩ በዝቶ ፣ ከመጠን በላይ ኑሮ፣ ንቀቱ በዝቶ፣ ማንአለብኝነቱ እንደልብ ተናጋሪው ፣ ፀብ አጫሪው ሃይ የሚለው ጠፍቶ ብዙ ነገሮች እየተደረጉ ነው ” ሲሉ ገልጸዋል። ብፁዕነታቸው አለኝ ባሉት መረጃ ” ቤተክርስቲያን ዘቅዝቆ እሳት ያያያዘ ፣ መስቀል ዘቅዝቆ አንገቱ ላይ ያጠለቀ ኢትዮጵያ ምድር ላይ ሊዘፍን ተዘጋጅቷል፤ ግብዣም ተደርጓል። ” ብለዋል። ” የሰዎችን መብት መንካት ስለማንችል እንደ ኢትዮጵያውያን እገሌ እገሌ ሳይል ከእንዲህ አይነቱ ማንም ተካፋይ ሳይሆን እንደ ኦርቶዶክሳዊያን ዳግሞ የኦርቶዶክስ ልጆች ለፀሎት ታውጇል ፣ ለጾም ለጸሎት እራስን ከማዘጋጀት ውጭ ምንም ትርፍ የሌለው ከሳንቲም ውጭ ትርፍ ለሌለው የሀገርን ገፅታ የሚንድ ድርጊት ላይ ተሳታፊ ከመሆን #እንድትቆጠቡ ” ብለዋል። ” አባቶቻችን ቅድሚያ የሚሰጡት ለጾም ፣ለጸሎት ለፍቅር፣ ለሰላም ነው ፤ ውሃ ሙላት እያሳሳቀ ይወስዳል እንደሚሉት አባቶች በዘፈን እና በዳንኪራ እያሳሳቀ ወደ ሞት፣ ወደ ማዕበሉ የሚገፋ ነገር ላይ ተሳታፊ እንድንሆን ቤተክርስቲያን አትፈቅድም ፣ የሃይማኖት ሰዎችም ድርሻ አይደለም ” ሲሉ አስግዝበዋል። ብፁዕነታቸው ፤ ” እኔ ምን አገባኝ በሚል በዘመናዊ ስሜት እንደልብ ተካፋይ መሆን በእግዚአብሔር ዘንድ ነውር ነው ፤ ወንጀልም ነው ” ያሉ ሲሆን ” ፀብ አጫሪ መሆንም አስፈላጊ ስላልሆነ የኦርቶዶክስ ልጆች በቤታችሁ ሰብሰብ ብላችሁ ተቀመጡ፤ የሚመለከተው እንደፈለገ ይሁን ፤ ኦርቶዶክሳውያን ከቤተክርስቲያናችሁ ተገኝታችሁ ጸልዩ፣ እግዚአብሔርን ለምኑ አብረን ተያይዘን እንዳንጠፋ ” ብለዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፤ በጳጉሜን 6 ቀናት ሁሉም ምዕመናን እግዚአብሔር መጪውን ዘመን የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ የአንድነት፣ ብሶተኛ የማይኖርበት ተራብኩ ተጠማሁ ተፈናቀልኩ ተሰቃየሁ ተንገላታሁ የሚል የማይኖርበት ፣ ኢትዮጵያውያን በፍቅር በአንድነት የምንኖርበት ዘመን እንዲሰጠን ጸሎት በማድረግ እናሳልፍ ስትል አደራ ብላለች። ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- Ashara Tv – https://www.youtube.com/channel/UC2LZu_N0iOJipVUw3RyR4Ng // https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24
Source: Link to the Post