
#መረጃ ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተወረወረ አስለቃሽ ጭስ በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክያን የነበረው ክብረ በዓል ሳይጠናቀቅ መቋረጡ ተገለጸ! የአማራ ሚዲያ ማእከል… የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ዓመታዊውን የሊቀ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና 127ኛውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ ክብረ በዓል ለማክበር በርካታ ሕዝበ ክርስቲያን ከየአቅጣጫው ተሰብስቦ እንደነበረ ተገልጿል። ታቦታተ ሕጉ ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው የዑደት ሥነ ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ክብረ በዓሉ እየተከናወነ ባለበት ወቅት ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወደ ቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑ በተወረወረ አስለቃሽ ጭስ የበዓሉ ሥነ-ሥርዓት ሳይጠነቀቅ ታቦታተ ሕጉ ወደ መንበረ ክብራቸው ተመልሰዋል ተብሏል። ወደቅጽረ ቤተክርስቲያኑ በሚያስገቡ ሁለቱም መግቢያ በሮች በተወረወረው አስለቃሽ ጭስ በርካታ ምዕመናን በመጎዳታቸው ራሳቸውን ስተው ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ ከቦታው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በተፈጸመው ክስተት ዙሪያ አጠቃላይ የማጣራት ሥራ በመሥራት የተደራጀ መረጃ ይዘን እንደምንመለስ እየገለጽን ቤተክርስቲያኒቱም መግለጫ እንደምትሰጥ እንጠብቃለን። ምንጭ ተሚማ
Source: Link to the Post