“መሬታችን በመንግስት እየተወሰደብን ነው”- የምዕራብ ሸዋ ዞን ናኑ ወረዳ ነዋሪዎች

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ናኑ ወረዳ ልዩ ስሙ ናኑ ጉዲና ቀበሌ 01 ‘መዳሎ’ አካባቢ የግለሰብ መሬቶች “በአካባቢው ሚሊሻ እና ፖሊሶች እየተወሰደ” ለወጣቶች እየተሰጠ ነው ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግሩ።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት “ግብር የምንከፍልበት እና ሕጋዊ ካርታ ያለውን ንብረታችንን ከ2 ሄክታር መሬት በላይ መያዝ አትችሉም በማለት የተቀረውን ሰብስበው ላመጧቸው ወጣቶች እየሰጡ መሆኑን” ጠቁመዋል።

ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን የገለጹ በምዕራብ ሸዋ ዞን የ’መዳሎ’ አካባቢ ነዋሪዎች እንደገለጹት የጸጥታ አካላቱ አምስትም ሆነ አስር ሄክታር መሬት ያለው ግለሰብ ከሁለት ሄክታር በላይ መያዝ አይችልም በማለት፤ “የሚያስተዳድሩት የቤተሰብ ብዛት እና የኢኮኖሚ አቅም እንኳን ሳይታይ ወጣቶችን ለመጥቀም በሚል መሬታችን እየተወሰደብን ነው” ብለዋል። 

“ከአካባቢው ፖሊስ፣ ልዩ ሀይል እና ከወረዳ አስተዳደር ነው የመጣነው በማለት ከተለያዩ አካባቢዎች መልምለው ያመጧቸውን ወጣቶች በማስከተል ከሰበሰቡን በኋላ ወጣቱን ለማሰማራት በማለት መሬቱ መከፋፈል አለበት ብለው መንጠቅ ጀመሩ” ሲሉም የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ በምሬት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። 

ነዋሪዎቹ ከምዕራብ ሸዋ ዞን ስለጉዳዩ ሲጠይቁ ከዞኑ ያገኙት ምላሽ በአካባቢው “ጥግ ጥግ ቦታዎች የማይታረሱ እና ሕገ ወጥ የሆኑ መሬቶች አሉ፤ እነሱን እንዲወስዱ ነው የታዘዙት” የሚል እንደሆነ የሚገልጹት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ ነገር ግን በተቃራኒው የአርሶ አደሩን እና ሕጋዊውን መሬት እያከፋፈሉ ስለመሆኑ ምንም እውቅና እንደሌላቸው ዞኖ ገልጾልናል ብለዋል። 

ናኑ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ በርካታ ቀበሌዎች መካከል 30 የሚሆኑ ቀበሌዎች “በኦነግ ሸኔ” ቁጥጥር ስር የሚገኙ ስለመሆናቸውም ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል። 

አንጻራዊ ሠላም ያለባቸው ወደ 5 የሚሆኑ ቀበሌዎች ሲሆኑ አንዱ በሆነው መዳሎ ቀበሌ 01 ውስጥ መሬታቸው የተወሰደ አንድ ግለሰብ እንደገለጹልን “በሌሎቹ ቀበሌዎች በተመሳሳይ መሬታችው መከፋፈል አለበት በማለት ከወሰዱ በኋላ መሬቱ የሚሰጣቸው ግለሰቦች ቆይተው ነዋሪዎቹን በማጥቃት እንዳፈናቀሉዋቸው” ተናግረዋል። 

የእነሱ ስጋትም ይህ እንደሆነና “ለማፈናቀል ሆን ተብሎ የሚደረግ ስለመሆኑ” ጥርጣሬ እንዳለባቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። 

እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ፤ የአካባቢው ሚሊሻዎች ከባድ መሳሪያ በመታጠቅ አጅበው ያመጧቸው ወጣቶች ደግሞ “ስለት እና መሰል መሳሪያዎችን በማስያዝ ማህበረሰቡን እያስፈራሩ እና ባስ ሲልም መሬቱን እያቃጠሉ በግድ መሬቶቹን እየወሰዱ ስለመሆኑ” አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

በተመሳሳይ መሬት በኮንትራት ኪራይ በመውሰድ እያረሱ የሚተዳደሩ የአካባቢው አርሶ አደሮችም መሬት እንደተወሰደባቸው ተናግረዋል። 

በናኑ ጉዲና መዳሎ ከ295 እስከ 300 የሚደርሱ አባወራዎች ያሉ ሲሆን በሕጋዊ መንገድ ከመንግስት እውቅና አግኝተው ከ1987 ጀምሮ በቦታው እንደሚኖሩ የገለጹት ነዋሪዎች፤ “ያለአግበብ ግፍ እየተሰራብን በመሆኑ ፍትህ እንዲሰጠን እና ለማፈናቀል የሚደረገው ተግባር እንዲቆም” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። 

አዲስ ማለዳ የቅሬታ አቅራቢዎችን ሃሳብ ይዛ ከነዋሪዎቹ ጋር ከዞኑ አስተዳደር ተወክሎ መጥቶ ሲነጋገር እንደቆየ የተገለጸውን አመራር ለማነጋገር ያደረገችው ጥረት ስለጉዳዩ “ምንም አይነት ምላሽ” ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። አዲስ ማለዳ ከሚመለከተው የመንግስት አካል የሚሰጥ ምላሽን ለማስተናገድ ዝግጁ ናት።

Source: Link to the Post

Leave a Reply