የአርበኞች ግንቦት 7 አባል የነበሩ ናቸው። በእስር ተሰቃይተው በቅርቡ ተፈትተዋል። የሆነ ሰው ከኤርትራ ደውሎላቸዋል። ለእኔም ደውሎልኝ ነበር። ከእስር ለተፈቱት ገንዘብ እንድሰጥለት ነው። ተፈችዎችን ወደ ቤተሰቦቻቸው የላከ፣ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ወጫቸውን የሸፈነ ኮሚቴ እንዳለና እና በእነሱ በኩል ቢያደርስ እንደሚሻል ነገርኩት።
በነጋታው ከእስረኞች የሰማሁት ግን በእጅጉ የሚያበሳጭ ነው። የወንድሞቻችን መስዋዕትነት ያረከሰ ብቻ አይደለም። ከኢህአዴግ የባሰ። የወረደ ተግባር እንደተፈፀመ ከተፈችዎቹ አረጋገጥኩ።
ለእኔ የደወለልኝ ሰው ለእስረኞቹ ይደውላል። የአርበኞች ግንቦት 7 ክስ ተመስርቶባቸው ከእስር የተፈቱትን ስም ዝርዝር ፃፍልኝ ይለዋል። ተፈችው ይፅፍለታል። 31 ሰው። ሌላውም እንዲሁ።
ተፈችዎቹን “እናቋቁማችኋለን!” ብለዋቸዋል። ተፈችዎችም ተስማምተዋል። ዘግይቶ ነው ብልግናው የመጣው። ለድርጅቱ ብዙ ነገር ከፍለው፣ በእስር ተሰቃይተው የተፈቱትን ወንድሞች በገንዘብ ሊገዟቸው ሞከሩ። “ገንዘቡን ስትሰጣቸው ግን እንደ አዲስ አባል እያደረክ እያስፈረምክ ነው!” እንዳለው ነገረኝ ከኤርትራ የደወለው ሰው። “በገንዘብ ነው እንዴ የምትገዙኝ” ብሎ አሻፈረኝ አለው፣ ተፈችው። ደውሎ ሀዘኑን ነገረኝ!
እነዚህ ወጣቶች ብዙ አመት ትግል ላይ የቆዩ ናቸው። ልብስ እንኳ የላቸውም። ይህን ችግራቸውን ተጠቅመው አባል ሊያደርጉ ነው። አባላቸው ነበሩ፣ እንደከፋቸው ያውቃሉ። አሁን አባል ይሆናሉ ብለው አላመኑም። ገንዘብ ይዘው ብቅ አሉ።
እጅግ ተናድጄ ስለነበር አዲስ አበባ ለሚገኝ ሌላ ሰው ደውዬ ነገርኩት፣ ውጭም ደውዬ ብሶቴን የነገርኩት ሁለት ሶስት ሰው አለ። የአዲስ አበባው ወዳጄ ሌላ አካባቢ ለሚገኙ ተፈችዎች ገንዘብ መላኩንና አባልነት እንደቅድመ ሁኔታ አለመቀመጡን አጫወተኝ። ጎንደር የሚገኙትን ችግራቸውን አይተው፣ እነሱም መከፋታቸውን አይተው በገንዘብ አባል ለማድረግ ሞከሩ!
ኢህአዴግ ስብሰባ ይጠራል። አበል ይሰጥና “አባል መሆን የሚፈልግ!” ይላል። አባል አልሆንም የሚል ካለም ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ ይጠይቀዋል። የእነዚህ ከኢህአዴግ የባሰ ነው!
እድሜ ህሊና ላላቸው ወገኖች እንጅ እነዚህን ወጣቶች ቁሳቁስ አሰባስበው ቤት ተከራይተውላቸዋል። ወንድሞቹ ለሽያጭ ሲቀርቡ ቀርቶ ሕዝቡ አዛኝ ነው። ይህን ጉድ እውነት የማይመስለው ይኖራል፣ እንዲያው ኢሳቶች ድፍረቱን ካገኙ የወጣቶቹን አድራሻ ለመስጠት ፈቃደኛ ነኝ። ይህን ጉድ ለመጋፈጥ የሚፈልግ አመራር ካለም ወጣቶቹ ይነግሩታል!
በሌላ በኩል እነዚህን በገንዘብ አንገዛም ያሉ ወንድሞች በማገዝ ልናቋቁማቸው ይገባል። ለጊዜው የቤትና ትንንሽ ወጭዎች ተሸፍነዋል!
ዋናው ጉዳይ ግን ስንት ዋጋ የከፈሉትን ወንድሞች መስዋዕትና ክብር በገንዘብ ለመግዛት የሚጥር ካለ መታገስ አያስፈልግም! እኔም ይህን ጉዳይ ለሕዝብ ለማድረስ ጥሬ፣ እንደገና ትቼው መታገስ ግን አቃተኝ! ከኢህአዴግ የባሰ መስዋዕትነትን በገንዘብ የሚገዛን አካል መታገስ ተገቢ መስሎ አልታየኝም!
አይ ጌች
በአንድ ወቅት አማረብኝ ብዬ እንደዚህ ዓይነት የሆነ አቃጣሪ ነገር ስነግረው በትዝብት “እባክህ አታስቀኝ” ያለኝን የሠፈሬን ሰው አስታወስከኝ፡፡
ብትታገስ ይሻልህ ነበር፡፡ እስከመታሰር እና መከራ እስከመቀበል የፀኑ ጀግና አባላቶቻቸው ይሄንን አንተ የምትነግረንን ነገር ራሳቸው መናገር እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም፡፡ በቅርቡ የግንቦት ሰባት አመራሮች ሀገር ቤት ሲገቡ ደግሞ እውነታውን ግልፅ ማውጣታቸው አይቀርም ነበር፡፡ ማለቴ ያንተ አፈ ቀላጤነት የሚያስፈልጋቸው ዓይነት ሰዎች አይመስሉኝም ግን አንተ ቸኮልህ፡፡