
መንግሥት ሕገወጥነትን ከመደገፍ እና የቤተክርስቲያን አባቶችን ከማዋከብ እጁን እንዲሰበስብ እናት ፓርቲ አሳሰበ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 20 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ:_ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሀገር የዋለችው ውለታ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ የከፈለቸው ዋጋ ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ከሰሞኑ በተፈጠረው ክስተት የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ሕገወጦች አቋቁመናል ያሉትን ሲኖዶስ ከቀኖና ቤተክርስቲያን ውጭ የሆነና ሕገወጥ ነው በማለት መንግሥት ሥርዓት የማስከበር ሓላፊነቱን እንዲወጣ ብትጠይቅም በተቃራኒው ሕገወጥነትንና ሕገወጦችን የመደገፍ ተግባር ውስጥ እየገባ እየተመለከትን ነው፡፡ ጥር 20 ቀን 2015 ዓ.ም:_ 1) የጂማ፣ የም፣ ኮንታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አረጋዊ አባት ብጹዕ አቡነ እስጢፋኖስ በጂማ ከተማ ታሥረው መዋላቸውን፤ 2) ሌሎች ብጹዓን አባቶችና የሚመለከታቸው የሥራ ሓላፊዎች ቤተክርስቲያን ባርከው እንዲመርቁ ወደ ጂማ እንዳይጓዙ መታገዳቸውን፤ 3) በይቅርታ የተመለሱት አባ ጸጋ ዘአብ አዱኛም ባልታወቁ ኃይሎች አዲስ አበባ ከሚገኘው መንበረ ፓትርያርክ ታፍነው መወሰዳቸውንና የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ቤተክርስቲያኗ ከሰጠችው መግለጫ ለመረዳት ችለናል፡፡ 4) ይህም ሳይበቃ ቤተክርስቲያኗ በሕገወጥነት ፈርጃ ያወገዘቻቸውን ግለሰቦች ከለላ ለመሰጠቱ መረጃዎች ደርሰውናል፡፡ ሕግ ያስከብራል ያልነው መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ይህን ያህል ስህተት ውስጥ ይገባል የሚል ዕምነት ፍጹም አድሮብን አያውቅም ነበር፡፡ ሆኖም እያየን ያለነው “አውራውን ምታ መንጋው ይበተናል” የሚለውን ለመተግበር ቆርጦ እንደተነሳ፣ ምን አልባትም ከሕገ ወጥነቱ ጀርባም እጁ ረጂም እንደነበር ጉልህ ማሳያ አድርገን እንወስደዋለን፡፡ በዕምነት ውስጥ የሚነሳ እሳት በቀላሉ እንደማይጠፋ እየታወቀ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ እሳቱን አስነስቶ ቤንዚን ማርከፍከፉን ቀጥሎበታል፡፡ እውነታው ግን መንፈሳዊውን እርግማን ትተነው የሚነሳው ቋያ ቀድሞ የሚለበልበው ራሱን መንግሥትን ለመሆኑ ከታሪክ መማር ይጠቅም ነበር፡፡ ስለሆነም፡- 1. መንግሥት አባቶችን ማዋከቡንና ሕገወጥነትን መደገፉን በአፋጣኝ እንዲያቆምና ሕግን ብቻ እንዲያስከብር እናሳስባለን፡፡ 2. የብልጽግና መንግሥት የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያንን በተመለከተ ጥፋት ውስጥ እየተሳተፈ በመሆኑ ሕዝብ ይህን እኩይ ድርጊቱን እንዲያስቆመው ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
Source: Link to the Post