You are currently viewing መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ላይ ብሎም በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው በደል የከፋ ከመሆኑ ባሻገር የቤተክርስቲያንን ህልውና አደጋ ፤ላይ የሚጥል ነው ስለሆነም ጉዳዩን ለዐለም ማህበረሰብ…

መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ላይ ብሎም በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው በደል የከፋ ከመሆኑ ባሻገር የቤተክርስቲያንን ህልውና አደጋ ፤ላይ የሚጥል ነው ስለሆነም ጉዳዩን ለዐለም ማህበረሰብ…

መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ላይ ብሎም በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው በደል የከፋ ከመሆኑ ባሻገር የቤተክርስቲያንን ህልውና አደጋ ፤ላይ የሚጥል ነው ስለሆነም ጉዳዩን ለዐለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ በቅርቡ ዐለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ የምንጠራ ይሆናል ሲል በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምዕመናን ኅብረት አስታወቀደ ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” ሐዋ 20፡28 በመንግሥት ጣልቃ ገብነት እና አቀናባሪነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ በጥር ወር የተከሰተው የሕገ ወጥ ሹመት ችግሩ ያ ያልተቀረፈ ከመሆኑም ባለፈ መንግሥት ስልቱን በመቀያየር ያቀደውን ትልም ለማስፈጸም በትጋት እየሰራ ይገኛል። አሁንም መንግሥት በቀጥታ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል ለራሱ አጀንዳ አስፈጻሚ ሊሆኑ የሚችሉ ሊቃነ ጳጳሳትን በመመልመል ዓላማውን ለማስፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስን የመክፈል ሥራ እየሠራ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ለዚህም ዐቢይ ማሳያው በቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ የርክበ ካህናት ስብሰባ ላይ “ሊቃነ ጳጳሳት ለአንድ ብሔር ብቻ” ይሾሙ በማለት መንፈሳዊነት የሌለው፤ ከሐዋርያት አስተምህሮና ቀኖና ውጭ ለተግባራዊነቱም ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑ ነው። ይህ አካሄድ ሐዋርያዊት ብለን የምናምንባትን ቤተ ክርስቲያን የፖለቲካ ሃሳብ ማስፈጸሚያ ከማድረግ አልፎ ቤተ ክርስቲያኒቱን እና ሃገራችንን የሚያጠፋ አካሄድ ጅምር ነው።ስለሆነም የሰሜን አሜሪካ የካህናትና የምእመናን ኅብረት ይህንን የመለካውያን አካሄድ በጽኑ የሚያውግዝ ሲሆን፣ መንግሥት ቤተ ክርስቲያኒቱ በሰላም እንዳትተዳደር በቅዱስ ሲኖዶስ መንፈሳዊ አስተዳድር ውስጥ ጣልቃ በመግባት፣ አገልጋይ ካህናቷን፣ ሊቃውንቷን እና ምእመናኗን በመግደል፣ በማሰር እና በማሰቃየት መከራ እያጸናባት ሲሆን የመጨራሻ ግቡም ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንን ከምድሪቱ ላይ ማጥፋት ብሎም ኢትዮጵያ የምትባል ሃገርን መበተን ነው። ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ እንዲሁም አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ ቤተ ክርስቲያን ከተመሰረትችበት ጊዜ ጀምሮ በውስጥ በመናፍቃን እና ለዚህ ዓለም ባደሩ ምንደኞች፤ በውጭ ደግሞ በአላውያን ነገሥታት ስትፈተን የኖርች ወደ ፊትም በፈተና ውስጥ የምትኖር ናት። ሆኖም በየዘመናቱ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን ይመሩ ዘንድ ጳጳሳት አድርጎ የሾማቸው ቀደምት አበው “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” በማለት የአላውያንን እና የሰንፎችን ትእዛዝ ወደ ጎን በመተው ራሳቸውን በሰማእትነት አሳልፈው በመስጠት ይህችን ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዘምን ለተገኘነው አስረክበዋል። ሁላችሁም እንደምታሳትውሱት ዛሬ ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከፋፍላ አንድነቷን አጥታ የተለያየችው በ451 ዓ.ም በኬልቄዶኑን ጉባኤ መለካውያን የሊዮንን ትእዛዝ በማስፈጸማቸው ነው። በዚህ ጉባኤ እነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ መከራን ተቀብለው መከራቸው የሃይማኖት ፍሬአቸው እንደሆነ በማመን “ዝንቱ ውእቱ ፍሬ ሃይማኖት” በማለት በመጽናታቸው ቅድስቲቱ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ተዋረድን ጠብቃ እንድትኖር የብኩላቸውን መስዋእትነት በመክፈል መንፈሳዊ ተጋድሎን ፈጽመዋል። ብፁዓን አባቶች እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ፤ምናልባትም እግዚአብሔር እንደ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በእውነት መሠረት ላይ በመቆም የዚህችን ንጽህት ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንድትጠብቁና ዋጋ እንድትከፍሉ በመንበሩ ተቀምጣችኋል። እድሉን ሰጥቶአችሁ እንደሆነ ማን ያውቃል። እድሉን ተጠቅማችሁ ይህችን ቤተክርስቲያን ብታድኑ ሃገራችሁን ብሎም ትውልዱን አዳናችሁ ማለት ነው። ታሪካችሁም በሰማይም በምድርም በቀለመ ወርቅ ተጽፎ ይኖራል። ነገር ግን አላውያንን በመፍራት ቤተ ክርስቲያንን የሚያጠፋ ጥቁር የታሪክ አሻራ ካኖራችሁ በሰማይም በምድርም ታሪካችሁ ተበልሽቶ በታሪክ ስትወቀሱ ትኖራላችሁ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ኅብረት በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተደረገ ያለውን እያንዳንዱን ተጽእኖ በአትኩሮት እየተከታተል ሲሆን ከላይ ያነሳነው ብሔር ተኮር እካሂድን አስመልክቶ እና በመሰል ጉድዮች ዙርያ በተደጋጋሚ የአቋም መግለጫዎችን ስናወጣ የቆየን ሲሆን አሁንም በተፈጠረው የኤጲስ ቆጶሳት አሿሿም ዙርያ ኅብረቱ የሚከተለውን ባለ 4 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፦ የአቋም መግለጫ 1- በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ መልኩ “ለአንድ ብሔር ብቻ” “ከአንድ ብሔር ብቻ” ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ የቀረበው አጀንዳ እጅግ ልብ ሰባሪ ከመሆኑ ባሻገር ቤተ ክርስቲያኒቱ የክርስቶስን ወንጌል የማትሰብክ፤ ከአምላኳ ይልቅ ለአላውያኑ ታዛዥ አድርጎ እንድትታይ የሚያሳይ ገጽታን የሚፈጥር ሆኖ አግኝተነዋል። ከላይ በመግቢያችን ላይ እንደጠቀስነው የሊዮንን ሃሳብ ሊያስተገብሩ በሞከሩ ግለሰቦች ምክንያት “ጉባኤ ከለባት” ተብሎ የቀረው የኬልቄዶኑ ጉባኤ ዛሬ ዓለም ላለበት የተፋለሰ እምነት መሰረት ጥሎለታል። አላውያን ያልፋሉ ነገር ግን እነሱን ደስ ለማሰኘት ወይንም የተሸከሙትን የጦር መሣሪያ በመፍራት ቤተ ክርስቲያንን የማይሆን አዘቅት ውስጥ መወርወር፣ ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ ከመሆኑም ባሻገር በታሪክ የማይረሳ ጠባሳን መጣል ነው። ሐዋርያትም “ከሰው ይልቅ እግዚአብሔርን ደስ ልናሰኝ ይገባል” በማለት ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ሃይማኖትን አጽንተዋል። በመሆኑም በዘመናት የማይለወጠውን እግዚአብሔርን ደስ እናሰኘው። እኛ ክርስቲያኖች አግልግሎታችንም ሆነ ሹመታችን እንደ ብሉይ ኪዳን በዘር ሐረግ ሳይሆን በጥምቀት “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም” ከቅድስት ሥላሴ በመወለድ ባገኘነው ልጅነት እና ከክርስቶስ ጋር ባለን ኅብረት ነው። ስለሆነም በእናንተ መካከል የዘረኝነትን ሃሳብ ያመጣውን አባት እንዲታረም ግስጻችሁ፤ “ከአንድ ብሔር ብቻ ፤ለአንድ ብሔር ብቻ” የሚለውን የአሿሿም አካሄድ ከእኛ ከልጆቻችሁ ጋር በአንድነት በመሆን እንድታወግዙት ብሎም ነቅላችሁ እንድትጥሉት በቤተ ክርስቲያን አምላክ ስም እንጠይቃለን። ይልቁንም ታሪካችሁ በቀለመ ወርቅ የሚጻፍበትን እና ለቤተ ክርስቲያን በዘላቂነት የሚጠቅም ከዘረኝነት የጸዳ፤ በእውነት ላይ የተመሰረተ አሰራርን ትተክሉ ዘንድ በትህትና እንጠይቃለን። ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት የቤተ ክርስትያንን ጥያቄ ብቻ ሊመልስ የሚችል እና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ቀኖና በጠበቀ መልኩ መደረግ አለበት ብሎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ኅብረት እንዲሁም መላው ህዝበ ክርስቲያን ያምናል። ስለሆነም ሲመቱ ቤተ ክርስቲያን በየሃገረ ስብከቱ ያለውን ክፍተትን በመጥናት፣ ተደርበው የተያዙ ሃገረ ስብከቶችን ለአገልግሎት ቅልጥፍና በሚረዳ መልኩ ለማከፋፈል እና የስራጫናን ለመቀነስ ብሎም ተመሳሳይ መንፈስዊ እገልግሎቶችን ታሳቢ በማድረግ መሾም የሚገባ ሲሆን። በዚህም ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸውን በሃይማኖት የጸኑትን በምግባራቸው አርአያ ክህነት ያላቸውን ለመንጋው የሚራሩና መልካም እረኛ ሊሆኑ የሚጋባቸውን ቤተ ክርስቲያን ባወጣችው መመርያ መሠረት ብቻ መስፈርቱን የሚያሟሉትን ሊሆን ይገባል እንጂ የዘር ኮታን መሰረት ያደረገን ሊሆን አይገባም። 3- በዚህ ወቅት በመንግሥት ጫና የቅዱስ ሲኖዶሱን አባላት አቋም በመከፋፈል ሲመተ ኤጴስ ቆጶሳት ተግባራዊ ከተደረገ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሉዓላዊት፣ ኩላዊትት፣ ቅድስትና አንዲት መሆኑዋን ቀርቶ ሁለት እና ከዚያ በላይ ሲኖዶስ፣ ሁለት እና ከዚያ በላይ ፖትርያርክ የተወሰነ ጎሳ ብሔረሰብ ወኪሎች የፌዴሬሽን የጳጳሳት ምክር ቤት፣ ጥገኛ እና መለካዊት፣ የተከፋፈለች በስም ብቻ የምትጠራ ቤተክርያን በመፍጠር በመንፈሣዊ መሪዎቿ እና ተከታዮቿ ምዕመናን መካከል ልዩነት በመፍጠር የጦርነት አውድማ አበጅቶ ሲናቆር ኦርቶዶክሳዊን ማጥፉትና ሀገረ ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው፣ የታሪክ ጠባሳ እንዳይፈጠር ፣ሁሉም አባቶች እውነትን ይዘው አቋማቸውን በአንድነት በማሳውቅ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ያሉ አጽራረ ቤተ ክርስቲያናት እና ፖለቲካው ጭምር ያጠመደውን የሴራ ወጥመድ ሰባብረው በመጣል ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳትን ላልተወሰነ ጊዜ በማራዘም ትውልዱን ከነፍስ ከስጋ ጥፋት እንድትታደጉ እንማጸናለን። 4- የሃገሪቱ የፌደራል መንግሥት ብሎም የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ያለ አግባብ በቤተ ክርስቲያኒቱ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ላይ ግልጽ ጣልቃ ገብነትን እያሳየ የእምነትን ነጻነት እየተጋፋ መሆኑ ይታወቃል። ከላይ እንደተጠቀሰው በጥር ወር በተካሄደው ሕገ ወጥ ሹመት ባስከተለው ሁከት ምክንያት ብዙ የእምነቱ ተከታዮች እና አገልጋዮች የሕይወት መጥፋት፣ የአካል መጉደል፣ እስራት እና እንግልት ደርሶባቸዋል እያደረሰባቸውም ነው። ከዚህ በፊት በጠየቅነው መሠረት የመንግሥት አካላት የጉዳዩ አቀናባሪዎች በመሆናቸው ጥፋቱን ባደረሱት አካላት ላይ ምንም አይነት የሕግ ተጠያቂነት ያላደረጉ ከመሆኑ ባለፈ ሕገ ወጥ ተሿሚዎቹ ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያንን እያወኳት ነው። ከዚህም ባሻገር በተለያዩ የትግራይ ከዚህም ባሻገር በተለያዩ የትግራይ ሃገረ ስብከቶች የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት ደግሞ ግንባር በመፍጠር “መንበረ ሰላማ” በሚል ስያሜ “የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነትን” (መሥርተናል ከማለት) አልፎ ተርፎ ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ከሃገር ውጭ ያሉ አህጉራትን በመከፋፈል ራሳቸውን የተለያዩ አህጉረ ስብከቶች ሊቃነ ጳጳሳት አድርገው መሾማቸው እና ከቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት የተለየ አካሄድ መከተላቸው እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ ችግር ሳይፈታና እንድነት ሳይመጣ ሹመት ማስቀደሙ ከድጡ ወድ ማጡ ከመሸጋገር ውጭ ቤተ ክርስቲያንን አይጠቅምም። በሌላ እንጻር አሁን እየትካሄደ ባለው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ገና ከጅምሩ ሹመቱ ዘር ተኮር እንዲሆን በመንግሥት የተሰጠውን ቀጭን ትእዛዝ ለማስፈጸም በሚደረገው ውክቢያ ቤተ ክርስቲያን የከበደ ፈተና ውስጥ እያስገባት ነው። በእነዚህና መሰል ምክን ያቶች በዚህ ወቅት ሊደረግ የታሰበው ሹመት፦ ሀ. መንግሥት ሙሉ ለሙሉ እጁን ከቤተ ክርስቲያን ላይ እስኪያነሳ ድረስ፤ ለ. በቅዱስ ሲኖዶስም ውስጥ ከዛህም ውጭ ያሉ አባቶች ከዘረኝ ነት አባዜ ወጥተው እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ነገሮችን ማከናወን የሚችሉበትን አመለካከት እስኪያመጡ ድረስ ሐ. በትግራይ ከሚገኙ አባቶች ጋር በቅርበት አስፈላጊ ውይይት ተደርጎ የቤተ ክርስቲያን አንድነት እስኪጠናከር ድረስ የቅዱስ ሲኖዶስ ትኩረት ከኤጴስ ቆጳሳት ሾመት ይልቅ በሰላም እና የቅዱስ ሲኖዶስ አንድነት ላይ አጥብቆ መስራት ሊሆን ይገባል ብለን እናምናለን። ስለሆነም በአሁኑ ወቅት ሊከናወን የታቀደው የኤጴስ ቆጳሳት ሹመት ከዚህ በላይ (ሀ-ሐ) የዘረዘርናቸው ነገሮች እስኪሟሉ ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም በአጽኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ኅብረት አጥብቆ ይጠይቃል። ኅብረቱ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እያደረገ ያለውና በቀጣይ ሊያደርግ ያቀደው ተግባራት 1- መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ላይ ብሎም በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው በደል የከፋ ከመሆኑ ባሻገር ይህ ተጽ እኖ የቤተክርስቲያንን ህልውና አደጋ ፤ላይ የሚጥል ነው ስለሆነም ጉዳዩን ለዐለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ በቅርቡ ዐለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ የምንጠራ ይሆናል። 2- መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን በመከፋፈል ሃይማኖትን የማጥፋት ሃገርንም የመበተን ስራ በከፍተኛ ደረጃ እየሰራ ነው። ይህ ደግሞ በቀጣይነት የማያቋርጥ የእርስ በእርስ ግጭት ፤የደም መፍሰስ እና ግድያ የሚያመጣ፤ ምስራቅ አፍሪካን ብሎም መላው ዓለምን ከፍተኛ ሥጋት ላይ የሚጥል በመሆኑ ይህንን ጉዳይ ለዐለም አቀፍ ተቋማት (የዐለም ባንክ /World Bank፣ የዐለም የገንዘብ ብድር ድርጅት/International Monetary Fund፣ ለአውሮፓ ኅብረት/European Union፣ እና ለመሰል ድርጅቶች) በማሳወቅ ሊደርጉ በሚገባቸው ተግባራት ላይም አብሮ ይመክራል። 3- ከአሜሪካን የሕግ አውጪ አካላት ጋር በሃገሪቱ ባለ ስልጣኖች ላይ የመጓጓዝ ማእቀብ (Travel banning) እንዲጣል ብሎም በዐለም አቀፍ ፍርድ ቤት (International Court) ሃገሪቱ ውስጥ በመንግሥት እየተካሄደ ላለው ግፍ ግድያ እና እንግልት የመንግሥት ባለስልጣናት እንዲጠየቁ እና ለፍርድ እንዲቀርቡ የማድረግ ሥራው የተጀመረ ሲሆን ይህንኑ ከፍጻሜ ለማድረስ ይሰራል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ዋሺንግተን ዲሲ “ውድ የአሻራ ሚዲያ ቤተሰቦች የአሻራ ሚዲያ ቻናልን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችሁን ታሳዩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።” ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw // Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24

Source: Link to the Post

Leave a Reply