መንግሥት በጊንቢው ጥቃት 338 ሰዎች መገደላቸውን ገለጸ

አርብ ሰኔ 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ከኹለት ሳምንት በፊት በምዕራብ ወለጋ ውስጥ በታጣቂዎች የተገደሉ ሰዎች ብዛት 338 መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ።

ባለፈው ሰኔ 11 ቀን 2014 በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በፈጸመው ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተገደሉ ተዘግቦ ነበር።

በዚህ በአገሪቱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከተፈጸሙ ማንነት ተኮር ጥቃቶች መካከል የከፋው እንደሆነ በተነገረለት ጥቃት የተገደሉት ሰዎች አሃዝን የተለያዩ ወገኖች በተለያየ መጠን ሲገልጹት ቆይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ትናንት ሐሙስ ሰኔ 23 ቀን 2014 ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች 338 መሆኑን ገልጸዋል።

ጨምረውም በጥቃቱ ዙሪያ ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አመልክተው፣ በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጥቃቱ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ የቀረበውን ጥያቄ “ኢትዮጵያ ምርመራ ለማድረግ አቅም ያለው ተቋም የሌላት ያስመስላል” በማለት መንግሥት እንዳልተቀበለው ተናግረዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ተቋም ባሻገር፣ በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ቅዳሜ፣ ሰኔ 11፣ 2014 በምዕራብ ወለጋ፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ በሚገኙት ጉቱ፣ ጨቆርሳ፣ ስልሳው፣ በገኔ፣ ጫካ ሰፈር እና ሀያው በተባሉ መንደሮች (ጎጦች) በታጣቂዎች በተፈጸመ ጭፍጨፋ አሶሽየትድ ፕሬስ በአሜሪካ የአማራ ማኅበርን ጠቅሶ እስካሁን 503 ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል።

ማኅበሩ እንደሚለው በጭፍጨፋው 503 ሰዎች መገደላቸውን ከምንጮቹ ማረጋገጡን አመልክቶ፣ ከእነዚህም መካከል የ399 ሰዎችን በሥም እንደለየና የሞቱት ሰዎች ብዛት ግን ወደ 600 መቶ እንደሚጠጋ ለቢቢሲ ገልጿል።

አብዛኞቹ ሴቶችና ህጻናት የሆኑ የአማራ ብሔር አባላት ላይ የተፈጸመውን ይህንን ጭፍጨፋ በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የሚነገርለት መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መፈጸሙን ከጥቃቱ የተረፉ እና መንግሥት መግለጻቸው ይታወቃል።

ታጣቂ ቡድኑ ግን ድርጊቱን አለመፈጸሙንና ጥቃቱ መንግሥት ባደራጀው ሚሊሻ የተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ በጥቃቱ ዙሪያ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንም በምዕራብ ወለጋው ጭፍጨፋ ወቅት ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች በታጣቂዎቹ ታግተው መወሰዳቸውን አመልክቶ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በጥቃቱ ዙሪያ ፈጣን፣ ገለልተኛና ዝርዝር ምርመራ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ኮሚሽኑ በአብዛኛው የአማራ ብሔር አባላት በሚኖሩበት ቶሌ ቀበሌ ላይ ተፈጽሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ በዋናነት ሴቶችና ህጻናት ስለተገደሉበት ጥቃት እማኞችን ማናገሩን አመልክቶ፣ ታጣቂዎቹ በርካታ ቤቶችን በማቃጠላቸው ቢያንስ 2000 ሰዎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል ብሏል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply