መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አባቶችንና ምእመናንን አሰቃቂ ግድያ በማስቆም ከደሙ ነጻ መሆኑን በአስቸኳይ ሊያረጋግጥ ይገባል- እናት ፓርቲ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ከተማ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም በታጣቂ ኃይሎች የተፈፀመው አሰቃቂ የገድያ ወንጀል እናት ፓርቲ ማወገዙን ፓርቲው ዛሬ ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ከተማ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ ሶስት ጀምሮ በታጣቂ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት የደብረ ቅዱሳን ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ መርጌታ፣ ሁለት ልጆቻቸው እና ባለቤታቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው የገለፀው መግለጫው ፡፡

እንዲሁም ከሁለት ወራት በፊት ሥርዓተ ጋብቻቸውን የፈጸሙ ሙሽሮች (አንድ ዲያቆን ከባለቤቱ እና ታላቅ እህቱ ጋር) በአጠቃላይ 5 ንጹሐን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ካህናትና ምዕመናን በአሰቃቂ ሁኔታ በታጣቂዎች መገደላቸውን ከአካባቢው ነዋሪዎች ለመረዳት መቻሉን ፓርቲው ከላከው መግለጫ መረዳት ይቻላል፡፡

በተጨማሪም ከደቡብ ክልል አካባቢ መጥተው በከተማው በቀን ሥራ ይተዳደሩ የነበሩ 4 ንጹሐን ዜጎችም በታጣቂ ኃይሎች መገደላቸውንና ሌሎች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው 5 ሰዎችም በዶዶላ አጠቃላይ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ለመረዳት ችለናል ሲል ገልፃል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ምዕመናን ባለፋት ሶስት አስርት ዓመታት እጅግ በጣም አሰቃቂ ጥቃት ደርሶባቸዋል ያለው ፓርቲው በተለይም ደግሞ ባለፉት አምስት ዓመታት በቤተክርስቲያኗ እና ምእመናኗ ላይ እየተፈጸመ የሚገኘው ግፍና አሰቃቂ ግድያዎች ክፉኛ ተጠናክረው ቀጥለዋል ሲል ወቅሷል።

መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አባቶችና ምእመናንን አሰቃቂ ግድያ በማስቆምና መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ከእነዚህ ንጹሐን ደም ነጻ መሆኑን በአስቸኳይ ሊያረጋግጥ ይገባል ሲል ፓርቲው በመግለጫው አንስቷል፡፡

አቤል ደጀኔ
መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply